የኢትዮጵያ መንግሥትና የህወሓት መወቃቀስ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 27 2016
የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት እና ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) አምና የተፈራረሙትን ግጭት የማስቆም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ገቢር ላለመሆኑ አንዱ ሌላዉን እየወቀሱ ነዉ።የፌደራሉ መንግስት ስምምነቱ የተፈረመበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባወጣዉ መግለጫ «ያኛዉ ወገን» ያለዉን ህወሓትን «እግር የመጎተት አዝማሚያ ይታያል" በማለት ሲወቅስ፣ ሕወሓት በፊናው "በኢትዮጵያ መንግሥት መፈፀም ያለባቸው ወሳኝ መሠረታዊ ጉዳዮች በአግባቡ አልተፈፀሙም" በማለት ከሷል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ስለጉዳዩ በአማርኛ ቋንቋ ካወጣው መግለጫ ያልተካተተ ነገር ግን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ባወጣው መግለጫ "ትጥቅ የማስፈታቱ ሂደት በክልሉ [ትግራይ] አሁንም ተስፋፍቶ የሚገኘውን የከባድ ትጥቅ ክምችት እና ጥቃቅን እና ቀላል መሳሪያዎችን ሙሉ በሙሉ ማስረከብን ይጠይቃል" ሲል አስታውቋል።
መግለጫ ከፌዴራል መንግሥቱ ቀድሞ ያወጣው ሕወሓት በበኩሉ "ወራሪዎች" ያላቸው አካላት ከክልሉ አካባቢዎች አለመውጣታቸው እና ሕወሓት የነበረውን ሕጋዊ ሕልውና ይዞ እንዳይቀጥል መደረጉ የወቀሳው መነሻ መሆኑን አመልክቷል።
ውዝግብ የተፈጠረባቸውንና የይገባኛል ጥያቄ ያለባቸውን አካባቢዎች በተመለከተ የፌደራል መንግስት ለችግሩ ሰላማዊና ሕጋዊ ብሎም ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን በመግለጫው አመልክቷል።
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት የፕሪቶሪያውን ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት አስመልክቶ ትናንት በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ባወጣቸው መግለጫዎች የፌዴራሉ መንግሥት እና ተቋማት ስምምነቱን ከሚጠበቀው በላይ እየፈጸሙ እንደሚገኙ ነገር ግን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ስምምነቱን በተሟላ ሁኔታ እየፈጸመ እንዳልሆነ "በዚያኛው ወገን እግር የመጎተት አዝማሚያ ይታያል" በማለት ገልጿል።
የስምምነቱ አካል የሆነውንና በትግራይ እና በአማራ ክልሎች በኩል የይገባኛል ጥያቄ ያለባቸው አከራካሪ ቦታዎች በተመለከተ "ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጥ እና ሁሉንም ወገኖች ሊጠቅም የሚችል" ሲል ያስቀመጣቸው "ክረምት ደርሶ የእርሻ ሥራ ከመጀመሩ በፊት ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ የማድረግ ፣ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች በመረጧቸው አካላት እንዲተዳደሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እና ቀስ በቀስ ለአካባቢዎቹ ዘላቂ ሰላም የሚሆን ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ማድረግ" የሚሉ የመፍትሔ አማራጮች መቀመጣቸውን ጠቅሷል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በአማርኛው ከወጣው ይያልተካተተና በእንግሊዝኛ ቃንቋ ባወጣው መግለጫ ከላይ ከተጠቀሱት የመፍትሔ አማራጮች በተጨማሪ "በነዚህ አካባቢዎች ያሉ የጸጥታና የሕግ ማስከበር ኃላፊነቶች ሙሉ በሙሉ ለፌደራል ኃይሎች እንዲተላለፉ ማድረግ" የሚለውን ጭብጥም በመፍትሔነት አካቶታል።
የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ፈራሚው ሕወሓት በፊናው ባለፈው አንድ አመት ውስጥ በትግራይ ክልል በኩል እንዲፈጸሙ የተቀመጡት ጉዳዮች በሚገባ ተፈጽመዋል ያለ ሲሆን በፌዴራል መንግሥቱ "መፈፀም ያለባቸው ወሳኝ መሠረታዊ ጉዳዮች በአግባቡ አልተፈጸሙም" ሲል ወቅሷል። "ወራሪዎች ያላቸው አካላት "በኃይል ከያዟቸው የትግራይ መሬቶች መውጣት የነበረባቸው ቢሆንም እስካሁን እንዲወጡ አልተደረገም" ሲልም የፌዴራል መንግሥቱን ከሷል።
ስማቸው እንዲጠቀስ የማይፈልጉ አንድ የአለም አቀፍ ሕግና የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ተኩስ እንዲቆም የተፈለገው ዋናው ግብ ቢሳካም ሌሎች የስምምነቱ ጭብጦች ሙሉ በሙሉ አልተተገበሩም።
ግጭትን በዘላቂነት የማቆሙ ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባለመሆኑ በሚሊዮን የምሚቆጠር የትግራይ ሕዝብ ተበታትኖ እንደሚገኝ ያስታወቀው የሕወሓት መግለጫ ስምምነቱ በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበር ሰላማዊ ትግሉ ይቀጥላል ይላል። ሕወሓት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተገፈፈው ሕጋዊ ሕልውናውን ይዞ እንዳይቀጥል መደረጉ የስምምነቱን ሙሉ በሙሉ አለመተግበር አንዱ ማሳያ አድርጎ ያቀረበው ሲሆን ይህ ለስምምነቱ አተገባበር እንቅፋት መሆኑንም ጠቅሷል።
ከቀጣናው አስፈላጊነት እና ስልታዊ ጠቀሜታ አንፃር የላቀ ተፈላጊ የሆነውና ሰፊ የሰሊጥ፣ የማሽላ እንዲሁም የጥጥ ምርት የሚገኝበት ፣ ኢትዮጵያ ከሱዳንና ኤርትራ የምትዋሰንበት ይህ አከራካሪ ስፍራ ጉዳዩ በዘላቂነት በሕዝበ ውሳኔ መፍትሔ እንዲያገኙ አቅጣጫ ስለመቀመጡ ብሎም "በነዚህ አካባቢዎች ያሉ የጸጥታና የሕግ ማስከበር ኃላፊነቶች ሙሉ በሙሉ ለፌደራል ኃይሎች እንዲተላለፉ ማድረግ" የሚለው በመንግሥት ኮሙኒኬሽን መግለጫ መካተቱን በተመለከተ ከሁለቱ ክልሎች አስተያየት ለማካተት የተደረገው ጥረት አልተሰካም።
ለሁለት አመታት ቀጥሎ ፕሪቶርያው ውስጥ ለአሥር ቀናት ከተደረገ ዝግ ንግግር እና ድርድር በኋላ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ. ም በግጭት ማቆም ስምምነት የተቋጨው ጦርነት ለብዙዎች እፎይታ ቢያመጣም ኢትዮጵያ አሁንም በአማራ ክልል እየቀጠለ ባለ ተመሳሳይ አውዳሚ የግጭት አዙሪት ውስጥ መሆኗ ብዙዎችን አሳስቧል።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ