1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰላም ስምምነቱ «ሽንቁሮች»

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 20 2015

የጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ የፀጥታ አማካሪ ሬድዋን ሁሴይን የፕሪቶሪያዉ ስምምነት በተፈረመ ማግስት ለዉጪ ዲፕሎማቶች በሰጡት መግለጫ ህወሐትን በአሸባሪነት የሚፈርጀዉ ደንብ እንዲነሳ መንግስታቸዉ እንደሚጠይቅ ገልፀዉ ነበር

https://p.dw.com/p/4LXg6
Äthiopien Rgierungsvertreter  Tagesse Chafo
ምስል Million Haileselasie/DW

የሰላም ስምምነቱ ገቢራዊነት የዘነጋዉ ሕግ

             

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስትና ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የተፈራረሙትን የሰላም ስምምነት ገቢር ማድረግ መጀመራቸዉ ከሐገር ዉስጥም ከዉጪም ድጋፍ እየተሰጠዉ ነዉ።የፌደራሉ መንግስት ከፍተኛ የመልዕክተኞች ቡድን ባለፈዉ ሰኞ መቀሌ ዉስጥ ከህወሓት ባለስልጣናት ጋር ከተነጋገረ ወዲሕ ደግሞ ትግራይ ዉስጥ ተቋርጠዉ የነበሩ አገልግሎቶች በከፊል ጀምረዋል።ይሁንና የፌደራሉ መንግስት ባለስልጣናትና የህወሓት መሪዎች ስምምነቱን ገቢር ሲያደርጉ የሕግና የቴክኒክ ጥያቄዎችን ዘንግታዋቸዋል ተብለዉ እየተወቀሱ ነዉ።

«መቼም ሰላምን የማይፈልግ የለም።» ይላሉ ዶክተር ፍፁም አቻም የለሕ።የሕግ ባለሙያ፣በአማራ ላይ የሚደርስ ጥቃት እንዲቆም የሚሟገት ድርጅት የሕግ አማካሪም፣ አሜሪካ ኗሪ ናቸዉ።«ሰላም መስፈኑን አልቃወምም።» አከሉ የሕግ አዋቂዉ።

ባለፈዉ ሕዳር 2 (እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር) የኢትዮጵያ መንግስትና ህወሓት የተፈራረሙት «ግጭትን የማስቆም ስምምነት» በጦርነቱ ወቅት ለደረሰዉ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠያቂዎችን ለሕግ ስለማቅረብ ብዙም አለመጥቀሱ ብዙ የመብት ተሟጋች ድርጅቶችን ቅር አሰኝቷል።አሁንም ተጠያቂዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚጎተጉቱ በርካቶች ናቸዉ ።ዶክተር ፍፁምም ይሕን ሐሳብ ይጋራሉ።
የሰሞቱ ግን ሌላ ነዉ።መነሻዉ ባለፈዉ ሰኞ የኢትዮጵያ መንግስት የመልዕክተኞች ጓድ በመቀሌ ያደረገዉ ጉብኝትና ዉይይት ነዉ።የመልዕክተኞቹን ጓድ የመሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ናቸዉ።የፍትሕ ሚንስትር  ጌድዮን ጢሞቲዎስ ደግሞ አባል ነበሩ።
 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈዉ ዓመት ሚያዚያ ማብቂያ ህወሐትና ኦነግ-ሸኔን በአሸባሪነት ፈርጇል።የኢትዮጵያ ፍትሕ ሚኒስቴር የሚያዘዉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግም የሕወሓት ባለስልጣናትን በአሸባሪነት ከስሷል።
ህወሓትን ባሸባሪነት የፈረጀዉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እንደ ልዑካን መሪ፣የህወሓት መሪዎችን የከሰሰዉ አቃቤ ሕግ የበላይ እንደ አባል ከሕወሐት መሪዎች ጋር ካሜራ ፊት እንደ ጥሩ ወዳጅ ተቃቀፉ።ሰኞ።ሕጉስ? 
«ፓርላማዉ ህወሓትን ሽብር, ፈጣሪ ድርጅት ብሎ ሰይሟል።ወንጅሏል።ያንን ካላቸዉ ግለሰቦች ጋር ነዉ እንግዲሕ አፈ-ጉባኤዉ እየተገናኙ ያሉት ማለት ነዉ።---እንዲያዉ ፓርላማዉ መሳቂያ እንዳይሆን፣’ህወሃት የሽብር ድርጅት’ የሚለዉን ሰርዘናል ብለዉ----መሔድ ይቻል ነበር።አቃቤ ሕጉም ደግሞ ልደታ የሚገኘዉ የፌደራል ፍርድ ቤት፣ክስ የመሰረቱባቸዉ፣ማዘዣ የወጣባቸዉ ሰዎች ጋር ነዉ የሚጨባበጠዉ፣የሐገሪቱን ሕግ የሚጠብቅ ትልቅ ኦፊስ ነዉ የሚመራዉ ስለዚሕ እሱም እንኳን እነዚሕ ግለሰቦች ላይ የጀመርነዉን ክስን ወይ ሰርዘናል ወይ አቋርጠናል----» 
                                              
ይላሉ ዶከተር ፍፁም።
የጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ የፀጥታ አማካሪ ሬድዋን ሁሴይን የፕሪቶሪያዉ ስምምነት በተፈረመ ማግስት ለዉጪ ዲፕሎማቶች በሰጡት መግለጫ ህወሐትን በአሸባሪነት የሚፈርጀዉ ደንብ እንዲነሳ መንግስታቸዉ  እንደሚጠይቅ ገልፀዉ ነበር።«ፓርላማዉ ህወሓትን ባሸባሪነት መፈረጁን ዳግም እንዲያጤነዉ የፌደራሉ መንግስት (ፓርላማዉን) ይጠይቃል።ከዚያ ሕወሓት እንደ ሲቢል የፖለቲካ ፓርቲ መወዳደር ይችላል።»
የፓርላማዉ መሪዎችም፣ የፌደራሉ መንግስትም፣ሚንስትሮቹም፣ሕጉን አንድም ዘንግተዉታል፣አለያም ዶክተር ፍፁም እንደሚሉት «ባቦሰጥ» ሐገር እየመሩ ነዉ።
«እነዚሕ ሰዎች እንዲያዉ ባቦ ሰጥ ነዉ ይሕችን ሐገር የሚመሯት የሚለዉን እሳቤ----ከሳምንት በፊት ይመስለኛል ፍርድ ቤት ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠዉ።ምክንያቱም ይኸ ፕረስደንስ ነዉ የሚፈጥረዉ።የሚቀጥለዉ ትዉልድ፣የሚቀጥለዉ አፈ ጉባኤ፣የሚቀጥለዉ አቶርኒ ጄኔራል----እነሱጋ ሐገሪቱን መሳቂያ የሚያደርጓት።»«ሕግ ኃይለኞች ሲስማሙ የሚዳኙበት፣ ሲጣሉ የሚያፈርሱ፣ የሚደባደቡበት ስምምነት ባዮች እዉነት አላቸዉ ይሆን?» ወይስ «ሰማይ አይታረስ---» እንበል ይሆን እንደ ጥንቱ። 

የህወሓት መሪና የመንግስት መልዕክተኞች
የህወሓት መሪና የመንግስት መልዕክተኞች ምስል Million Haileselasie/DW
ዶ.ር ፍፁም አቻምየለሕ የሕግ ባለሙያ
ዶ.ር ፍፁም አቻምየለሕ የሕግ ባለሙያምስል Privat

ነጋሽ መሐመድ 

እሸቴ በቀለ