የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደረሰኝ ቁጥጥር ለምን ከመርካቶ ተቃውሞ ገጠመው?
ረቡዕ፣ ኅዳር 11 2017የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2017 የመጀመሪያ መንፈቅ 54.9 ቢሊዮን ብር ገቢ የመሰብሰብ ዕቅድ ነበረው። ይሁንና የተሰበሰው 45.6 ቢሊዮን ብር ነው። የተሰበሰው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያ በ12 ቢሊዮን ብር ከፍ ቢልም ከዕቅዱ ግን በ10 ቢሊዮን ብር ገደማ ዝቅ ያለ ነው።
ከንቲባዋ አዳነች አቤቤ “የከተማውን አጠቃላይ የገቢ አቅም መነሻ አድርገን ነው ያቀድንው። ዕቅዳችንን ደግሞ ማሳካት አለብን” ሲሉ የከተማ አስተዳደሩ ባለፈው ማክሰኞ ሕዳር 3 ቀን 2017 የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ሲያካሒድ ተናግረዋል። አዳነች በስብሰባው ለታደሙ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ፈርጠም ብለው “በዚህ ሩብ ዓመት የታየው የገቢ እጥረት መሟላት መቻል አለበት” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
ለ2017 አዲስ አበባ 230.3 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ በጀት ስታጸድቅ የከተማው አስተዳደር ኃላፊዎች “የታክስ መሰረቱን እናሰፋለን” ብለው ነው። የ2017 በጀት ከቀደመው ዓመት ዋና እና ተጨማሪ በጀት በ68.3 ቢሊዮን ብር የላቀ ነው። ከንቲባዋ አዳነች አቤቤ ዕቅዱን ለማሳካት “የግብር ሥወራን ማስቀረት ላይ እንረባረባለን” ሲሉ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ “የኮሪደር ልማት” በዚህ ወቅት አስፈላጊ ነው ወይስ አንገብጋቢ?
አዳነች አቤቤ የሚመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢውን ለማሳደግ እርምጃ መውሰድ ከጀመረባቸው የከተማዋ ክፍሎች ቀዳሚው የሀገሪቱ ዋንኛ የግብይት ማዕከል የሆነው የመርካቶ አካባቢ ነው። ባለፉት ሦስት ገደማ ሣምንታት አስመጪዎች፣ አከፋፋዮች እና ቸርቻሪዎች በሚያደርጉት ግብይት ደረሰኝ መቁረጣቸውን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ “ከዚህ ቀደም ግብር የማይከፈልባቸውን አካባቢዎች” በመለየት አስተዳደሩ “ወደ ሥርዓት በማስገባት” ላይ እንደሚገኝ የከተማው ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ስብሰባ ላይ አስረድተዋል።
ባለፉት ሁለት ወራት አስመጪዎችን እና አከፋፋዮች በዝርዝር ተለይተው “ያስገቡት ምርት ምን ምን እንደሆነ፤ አከፋፋዮች ከየትኛው ፋብሪካ ምን ያክል ምርት እንደተረከቡ፤ በስንት ብር እንደተረከቡ ከፋብሪካዎቹ መረጃ ወስደን ተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) በዚያ መሠረት እንዲያሳውቁ” እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው አብራርተዋል።
አስመጪዎች፣ አከፋፋዮች፣ ቸርቻሪዎች እና “የክልል ንግድ ፈቃድ ያላቸው ተዋንያንም ጭምር ወደ ግብር ሥርዓቱ እንዲገቡ ግፊት እያደረግን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
በመርካቶ እየተደረገ የሚገኘው ቁጥጥር ቀድሞም በገቢዎች ባለሥልጣናት እና በነጋዴዎች መካከል የነበረውን ያለመተማመን የበለጠ አባብሶታል። ነጋዴዎች ባለፉት ሣምንታት መደብሮቻቸውን በመዝጋት ለአስተዳደሩ ቁጥጥር ተቃውሟቸውን አሳይተዋል።
የሞባይል ስልኮች እና ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች የሚሸጡበት ይርጋ ኃይሌ ሕንጻ አካባቢ፣ በተለምዶ ሚሊተሪ ተራ እና አመዴ ማዞሪያ ተብለው የሚጠሩ አካባቢዎች የንግድ መደብሮች ከተዘጉባቸው የመርካቶ ክፍሎች መካከል እንደሚገኙበት ዶይቼ ቬለ ለመረዳት ችሏል። በአብዛኞቹ የመርካቶ አካባቢዎች የገቢዎች መሥሪያ ቤት ሠራተኞች እና የጸጥታ አስከባሪዎች ጥብቅ ቁጥጥር ሲያደርጉ መሰንበታቸውን ዶይቼ ቬለ ተገንዝቧል።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች 845.3 ቢሊዮን ብር ዕዳ ክፍያ በኢትዮጵያውያን ትከሻ ላይ ተጫነ?
ከመርካቶ ሸቀጥ ወደ አሰላ ወስደው የሚያከፋፍሉ ነጋዴ ባለፈው ሣምንት ከረዥም ጊዜ ደንበኛቸው “ሰሞኑን ዕቃ የለም” የሚል መልስ አግኝተዋል። ሌላ የአዲስ አበባ ነጋዴ በበኩላቸው ወደ መርካቶ ሲያቀኑ ደንበኞቻቸው መደብሮቻቸውን ዘግተው በመድረሳቸው የፈለጉትን እንዳላገኙ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው በመርካቶ የአመዴ ማዞሪያ እና ዱባይ ተራ አካባቢ ነጋዴዎች እና በአስመጪዎች እና በአከፋፋዮች መካከል የሚገኙ ደላላዎች ዋንኛው ቅሬታ የተፈጠረው “በደረሰኝ ግዙ፣ በደረሰኝ ሽጡ” በመባሉ መሆኑን ይስማማሉ።
“በደረሰኝ አንሸጥም አላልንም። ችግሩ ሊፈታ እንደሚገባ እናምናለን” የሚሉ አንድ የመርካቶ ነጋዴ መንግሥት የጀመረው እርምጃ ለውጥ ያመጣል የሚል ዕምነት የላቸውም። ነጋዴው ጉዳዩ “ከላይ መጀመር አለበት” የሚል አቋም አላቸው። “ከላይ” ሲባል “ከማን?” ተብለው ሲጠየቁ “እነሱ ያውቁታል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ዶይቼ ቬለ ካነጋገራቸው ነጋዴዎች በገበያው ከፍተኛ መጠን ያለው ሸቀጥ ያለ ደረሰኝ እየተሸጠ የሚገኝ መሆኑን ለመረዳት ችሏል። ቸርቻሪዎች ከአከፋፋዮች የተረከቧቸው ሸቀጦች ከትክክለኛ ዋጋቸው በታች ደረሰኝ የተቆረጠባቸው በመሆኑ የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) አከፋፈል ጉዳይ ሌላው በነጋዴዎች የሚጠቀስ ልዩነት ነው። በኮንትሮባንድ ወደ ገበያ የገቡ ሸቀጦች ሲሸጡ እንዴት ደረሰኝ ይቆረጥ የሚለውንም አጣብቂኝ ያነሳሉ።
የከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጀው ውይይት ላይ የተሳተፉ አንድ ነጋዴ ችግራቸውን ቢያስረዱም “ደረሰኝ ትቆርጣለላችሁ” ከሚል ማሳሰቢያ የዘለለ መፍትሔ አለማግኘታቸውን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። ትላንት ማክሰኞ በተካሔደው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ከንቲባዋ አዳነች አቤቤ “ግብር መክፈል የለብንም የሚል ሙግት አላጋጠመንም” ሲሉ ተናግረዋል። የከተማ አስተዳደሩ የታክስ አሰባሰብ እና የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከነጋዴዎች ቅሬታ እንደሚነሳ ያረጋገጡት ከንቲባዋ “ግብር መክፈል አለብን የሚል ጽኑ አቋም ነው የሚያንጸባርቁት” ሲሉ ተደምጠዋል።
ይሁንና የከተማ አስተዳደሩ ባለሙያዎች ግብር ለማስከፈል ሲሞክሩ “ዕቃ ሊወረስ ነው፤ ሊዘረፍ ነው የሚል ውዥንብር ተነሳ” ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ “በአንድ በኩል ይኸ ውዥንብር እንዲሔድ ይደረጋል። በሌላ በኩል ደግሞ በለሊት ዕቃ ይጫናል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ዶይቼ ቬለ ከመደብሮቻቸው ዕቃዎች ወደ መጋዘኖች፤ ከመጋዘኖች ወደ ሌሎች አካባቢዎች ያሸሹ ነጋዴዎች መኖራቸውን ከመርካቶ ነጋዴዎች ለመገንዘብ ችሏል። በተለይ ከፍ ያለ አቅም ያላቸው ነጋዴዎች ከመደብሮቻቸው ራቅ ባሉ አካባቢዎች መጋዘኖች እንዳሏቸው የገለጹ አንድ የመርካቶ ሰው በደፈናው መናገር እንደሚቸግር ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። የከተማ አስተዳደሩ የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ በግብይቱ ሒደት ውስጥ ደረሰኝ መቆረጡን ለማረጋገጥ ቁጥጥር ሲደረግ “ነጋዴው ሱቁን የመዝጋት፤ ንብረቱን በለሊት እየጫነ የማውጣት እንቅስቃሴዎች ታይተዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ታክስ ሳይጨምር ከዘርፉ የሚሰበስበውን ገቢ 4 በመቶ ማሳደግ ይችላል?
ደረሰኝ የሌለው ንብረት ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀስ ከተገኘ እንደ ኮንትሮባንድ ተቆጥሮ “መወረስ አለበት” ያሉት ኃላፊው “ከዚያ በተረፈ የንግድ መደብር ውስጥ ሔደን ደረሰኝ አለው የለውም እያልን የመውረስ እንቅስቃሴ አልተሰራም” ሲሉ አብራርተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤም ሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ባለሥልጣናት የመርካቶ የንግድ እንቅስቃሴ የከተማዋን ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የኢትዮጵያን “የንግድ ሥርዓት ፍትኃዊነት እያዛባ ነው” የሚል አቋም አላቸው። ከንቲባዋ አስተዳደራቸውን ከመርካቶ ነጋዴዎች ያቃቃረው የታክስ አከፋፈል ጉዳይ “ዘመን የተሻገረ፣ ውዝፍ ” ሲሉ ይገልጹታል። “መርካቶ ከተማችን ውስጥ ብቻ ሳይሆን ሀገራችን ውስጥ ትልቅ የንግድ ማዕከላችን ነው” ያሉት አዳነች “ከመርካቶ የሚወጣው ብልሽት እንዳለ ሀገራችን ላይ ነው እየተንጸባረቀ ያለው። የከተማ አስተዳደሩ ላይ ብቻ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ብቻ ሳትሆን የፌድራል መንግሥቱም በመጪዎቹ ዓመታት ከታክስ የሚሰበሰበውን ገንዘብ በከፍተኛ መጠን የመጨመር ዕቅድ አለው። የኢትዮጵያ መንግሥት በመጪዎቹ አራት ዓመታት ከታክስ የሚሰበስበውን ገቢ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) አኳያ በአራት በመቶ ማሳደግ ይፈልጋል።
እሸቴ በቀለ
ታምራት ዲንሳ