የኢትዮጵያ መንግሥት ታክስ ሳይጨምር ከዘርፉ የሚሰበስበውን ገቢ 4 በመቶ ማሳደግ ይችላል?
ረቡዕ፣ ነሐሴ 15 2016የኢትዮጵያ መንግሥት በመጪዎቹ አራት ዓመታት ከታክስ የሚሰበስበውን ገቢ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) አኳያ በአራት በመቶ የማሳደግ ዕቅድ አለው። በዕቅዱ መሠረት በተያዘው ዓመት መንግሥት ከታክስ የሚሰበስበው ገቢ በአንድ በመቶ እንደሚጨምር የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል።
ባለፈው ሰኔ መጨረሻ በጸደቀው የ2017 በጀት መንግሥት 502 ቢሊዮን ብር ከታክስ ገቢ ሊሰበሰብ ዕቅድ ነበረው። መንግሥት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርበዋል ተብሎ በሚጠበቀው የበጀት ማሻሻያ በዓመቱ ከታክስ የሚሰበስበው ገቢ ወደ 850 ቢሊዮን ብር ገደማ ከፍ ብሎ እንደሚከለስ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ ጥቆማ ሰጥተዋል። ይኸ ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ጭማሪ ይኖረዋል።
የመንግሥት ዕቅድ ካለፉት ዓመታት የገቢ እና የታክስ አሰባሰብ አኳያ ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ ዕድገት አለው። ለምሳሌ ያክል መንግሥት በ2016 በጀት ዓመት ከታክስ 440.2 ቢሊዮን ብር የመሰብሰብ ዕቅድ ነበረው። ይሁንና ማሳካት የሚችለው 92.5 በመቶ ወይም 407 ቢሊዮን ብር ብቻ እንደሆነ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የዘንድሮው በጀት ይጠቁማል። መንግሥት ከያዘው ዕቅድ 33 ቢሊዮን ብር የታክስ ገቢ ሳይሰበሰብ ይቀራል ማለት ነው።
የኤኮኖሚ ባለሙያው አቶ ኢድሪስ ሰዒድ “ያገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብ በተለይ ደግሞ የታክስ ገቢ አሰባሰብ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ሲነጻጸር ከዓመት ዓመት ቀንሶ ከ7 በመቶ በታች ደርሷል” ሲሉ ይናገራሉ። የኢትዮጵያ የታክስ ገቢ ከጎረቤቶቿም ሆነ ከቀጠናው ሲነጻጸር እጅግ ዝተኛ የሚባል ነው። ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ ሀገራት የሚሰበስቡት ታክስ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት አኳያ በአማካይ 13.2 በመቶ አካባቢ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ከዓለም ባንክ በተፈራረማቸው የብድር እና ዕርዳታ ሥምምነቶች ተግባራዊ ከሚያደርጋቸው ማሻሻያዎች መካከል የገቢ አሰባሰብን ማሻሻል የሚለው ይገኝበታል። የዐቢይ መንግሥት የውጪ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና ፍላጎት እንዲከወን ከወሰነ በኋላ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና የባንክ ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት ላይ የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ የመንግሥትን ገቢ በ4 በመቶ ለማሳደግ የተያዘው ዕቅድ “ድሕነት ተኮር” ሥራዎችን ለማከናወን ላቅ ያለ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
በውይይቱ “የመንግሥት ገቢ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት በ4 በመቶ ለመጨመር” ዕቅድ መያዙን ያብራሩት ዶክተር ፍጹም “በተለይ ድሕነት ተኮር የሆኑ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ መሠረተ ልማት እና ግብርና ዘርፎች ላይ የምናደርገው ኢንቨስትመንት የተሻለ አድርጎ ለመቀጠል ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የ2017ን በጀት ሲያዘጋጅ በዓመቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የሚጸድቁ የታክስ ህጎች “በቀጣዮቹ ዓመታት ለታክስ ገቢ አሰባሰብ ተጨማሪ አቅም” እንደሚኖራቸው ተስፋ አድርጓል። በሰኔ የጸደቀው የበጀት ሰነድ እንደሚለው በማሻሻያዎቹ ብቻ “92.5 ቢሊዮን ተጨማሪ የታክስ ገቢ መሰብሰብ ይቻላል።”
ታክስ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከመንግሥት ገቢ በአማካይ 82.3 በመቶ ድርሻ ነበረው። ይሁንና በ2007 ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት 12.7 በመቶ ደርሶ የነበረው የታክስ ገቢ በ2015 ወደ 6.8 በመቶ አሽቆልቁሏል። አቶ ኢድሪስ “ባለፉት ጥቂት ዓመታት እየቀነሰ የመጣን trend ቀልብሶ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት በ4 በመቶ መጨመር ትልቅ ፈተና እንደሚሆን ይሰማኛል” ይበሉ እንጂ ተግባራዊ የተደረጉ ማሻሻያዎች ቀጥተኛ ያልሆነ አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ይጠብቃሉ።
ኢትዮጵያ ተግባራዊ ባደረገችው የውጪ ምንዛሪ ግብይት ማሻሻያ ምክንያት ከውጪ የምትሸምታቸው ሸቀጦች ዋጋ በብር በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምር የገለጹት የኤኮኖሚ ባለሙያው “በዚህ ምክንያት ምንም አይነት የታክስ ወይም የጉምሩክ ሪፎርም ሳይደረግ ከገቢ ንግዳችን የሚሰበሰበው ታክስ እየጨመረ ይመጣል” ሲሉ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያን የኤኮኖሚ ማሻሻያ ከሚደግፉ ዓለም አቀፍ ተቋማት አንዱ የሆነው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት “ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው” የሚባሉት ደሐ ሀገራት ከታክስ የሚሰበስቡትን ገቢ እንዲያሳድጉ ግፊት የሚያደርግ ነው። ኬንያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ብድር እንድታገኝ የፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ መንግሥት የሚሰበስበውን ገቢ በታክስ ለማሳደግ ያዘጋጀው ዕቅድ ኃይለኛ ተቃውሞ ቀስቅሷል።
ሀገራት የኤኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ እንዲያደርግ የሚጠቁሙ ተቋማት “ገቢ እንዲጨምር ታክስ ጨምሩ” የሚል ግፊት እንደሚያሳድሩ የገለጹት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ የኢትዮጵያ መንግሥት “አንድም የታክስ ምጣኔ” ሳይጨምር ከታክስ የሚሰበስበውን ገቢ የማሳደግ ዕቅድ እንዳለው አስረድተዋል።
በ2017 በጀት ዓመት መንግሥት ከታክስ የሚሰበስበው ገቢ ወደ 851 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሎ እንደሚከለስ የገለጹት ዶክተር ኢዮብ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ከሚቆጣጠረው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ “በነበረው የኤኮኖሚ distortion ያልተሰበሰበ በርካታ ታክስ እንዳለ አይተናል። ይኸን ስናስተካክል የታክስ አቅማችንን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር ነው ያየንው” ሲሉ ተደምጠዋል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ሰነዶች የኢትዮጵያ መንግሥት ገቢ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት 4.5 በመቶ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይጠቁማሉ። የተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያ፣ ኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ፣ የኤክሳይዝ ቴምብር፣ የገቢ ግብር ማሻሻያ፣ የታክስ ማበረታቻ ማሻሻያ፣ የተሽከርካሪ ዝውውር አመታዊ ታክ እና የንብረት ታክስ (Property Tax) ህግ በዓመቱ መንግሥት ከፍተኛ ገቢ ሊሰበስብ ያቀደባቸው ናቸው።
መንግሥት ከፍተኛ ተስፋ ከጣለባቸው መካከል ባለፈው ሰኔ 27 ቀን 2016 የጸደቀው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቀዳሚው ነው። “ምንም አይነት የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ ጭማሪ አልተደረገበትም” የሚሉት የኤኮኖሚ ባለሙያው አቶ ኢድሪስ “በታክስ ፖሊሲ ወይም በታክስ ሕጋችን ምክንያት የተፈጠሩ ክፍተቶችን መዝጋት እና በታክስ አስተዳደሩ ደካማ አፈጻጸም ምክንያት የማይሰበሰቡ ታክሶችን ወደ ታክስ መረቡ ማስገባት” በማሻሻያው ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።
የታክስ አሰባሰብ ሥርዓቱን በማዘመን “ካሁን በፊት በታክስ ስወራ እና ማጭበርበር ምክንያት እየታጣ የነበረውን ገቢ” ወደ ሥርዓቱ ለማስገባት ታቅዷል። ኢ-መደበኛውን ኤኮኖሚ ወደ ታክስ ሥርዓቱ ማስገባት፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ውጪ የሆኑ ዕቃዎችን ብዛት ማጥበብ እንዲሁም “በተለያዩ ጊዜዎች እና በተለያዩ ተቋማት በተለያዩ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ሲሰጡ የነበሩ የነጻ መብቶችን” ማንሳት ማሻሻያው ያተኮረባቸው ጉዳዮች ናቸው። “መሠረታዊ የሚባሉ የምግብ አይነቶች አሁንም ከተጨማሪ እሴት ታክስ ውጪ ናቸው” ሲሉ አቶ ኢድሪስ ገልጸዋል።
በተሻሻለው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ከዚህ ቀደም ቀረጥ የማይከፈልባቸው በርካታ ሸቀጦች እና አገልግሎቶች እንዲካተቱ ተደርጓል። በአዋጁ ውኃ እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት በፍጆታ ገደብ ታክስ ይከፈልባቸዋል። የምግብ ማብሰያ ዘይትን የመሳሰሉ ሸቀጦች ተጨማሪ እሴት ታክስ ከማይከፈልባቸው ጎራ አለመደባቸው በኢንዱስትሪው ዘንድ ቅሬታ አሳድሯል። የቴሌኮም፣ የኢንሹራንስ እና የቱሪዝም ዘርፎች አዋጁ ከመጽደቁ በፊት ቅሬታ ነበራቸው።
የኢትዮጵያ መንግሥት በአራት ዓመታት ከታክስ የሚሰበሰበውን ገቢ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) በአራት በመቶ ለማሳደግ የወጠነው ዕቅድ “ፈታኝ” እንደሆነ አቶ ኢድሪስ ቢስማሙም የተቀመጡ ግቦች ግን “ሊሳኩ የሚችሉ” እንደሆኑ ያምናሉ። ግቦቹን ለማሳካት ግን በፌድራል መንግሥት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በክልሎችም ማሻሻያዎቹን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።
“በአንዳንድ አካባቢዎች ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት እነዚህን ፖሊሲዎች ወይም ደግሞ እነዚህን ማሻሻያዎች በተባለው ፍጥነት ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል ወይ? የሚለው ትልቅ ሥጋት ነው” የሚሉት አቶ ኢድሪስ “ይኸንን ዓላማ እንዳናሳካ ሊያደርጉን ከሚችሉ ትልቁ መሰናክል እሱ ይመስለኛል” ሲሉ አስረድተዋል።
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማሕበረሰብ ክፍሎች የኤኮኖሚ ማሻሻያው ከሚያስከትላቸው ጫናዎች ለመታደግ ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት መንግሥት የማሕበራዊ ዋስትና መርሐ-ግብሮች (social safety nets) ስፋት እና ውጤታማነት እንዲያጠናክር ይመክራሉ። ከማሻሻያዎቹ በኋላ የዐቢይ መንግሥት 1,500 ብር የሚከፈላቸው ሠራተኞችን ደመወዝ በ300 ፐርሰንት ለመጨመር 90 ቢሊዮን ብር እንደመደበ አስታውቋል። የአፈር ማዳበሪያ፣ መድሐኒት እና ነዳጅ የመሠሉ ሸቀጦችንም ይደጉማል።
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር