1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ህብረት በኢትዮጳያውያን ላይ የጣለው የቪዛ ቁጥጥር

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 22 2016

የአውሮጳ ህብረት ለኢትዮጵያውያን ዜጎች የሚሰጠውን ቪዛ ለመገደብ መወሰኑን አስታወቀ። የኢትዮጵያ መንግስት ህገ ወጥ ስደተኞችን ለመቀበል ከህብረቱ ጋር ባለመተባበሩ የቪዛ ገደብ እንዲጥል ምክንያት እንደሆነው ታዉቋል። የህብረቱ እርምጃ በህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የሚመጡትን ሰዎች ለመግታት ጥረት እያደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት ነዉ።

https://p.dw.com/p/4fMUX
የአዉሮጳ ህብረት ፓርላማ ሽትራስቡርግ
የአዉሮጳ ህብረት ፓርላማ ሽትራስቡርግ ምስል Jean-Francois Badias/AP/picture alliance

የአውሮጳ ህብረት በኢትዮጳያውያን ላይ የጣለው የቪዛ ቁጥጥር

የአውሮጳ ህብረት በኢትዮጳያውያን ላይ የጣለው የቪዛ ቁጥጥር

የአውሮጳ ህብረት ወደ አውሮጳ  ለመጓዝም ሆን ለመግባት በሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ላይ የተለየና ጥብቅ የቪዛ አሰጣጥ ስራት የሚከተል መሆኑን ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ህብረቱ በመግለጫው፤ በስራም ይሁን በሌሎች የተለያዩ ጉዳዮች ወደ ሀያ ሰባቱ የህብረቱ አገሮች ለመጓዝ በሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን አመልካቾች ላይ፤አባል አገሮች ላልተወሰነ ግዜ የህብረቱን የቪዛ አሰጣጥ ደንቦች ላይከተሉና የተለየ ቁጥጥር ሊያደርጉ አንደሚገባ አሳስቧል። 

ቁጥጥሩ እንዴትና በምንስ ላይ ይሆናል?

ይፋ የሆነው የህብረቱ ውሳኔ፤ አባል አገሮች  በኢትዮጵያውያን የቪዛ አመልክቾች ላይ የተለየ የአሰራር ሂደት የሚከተሉ መሆኑን በመግለጽ በተለይ አራት ትኩረት የሚደርግባቸውን ነጥቦች ለይቶ አሰቀምጧል፤ አንደኛ፤ የቪዛ አመልክቾች የሚያቀርቧቸው ማስረጃዎችና ሰነዶች ከዚህ ቀደም ባልነበረ ሁኔታ ጭምር ተቀባይነት ላያገኙ ይችላሉ፤ ሁለተኛ፤ የአንዱ አባል አገር ቪዛ ወደሌሎች የህብረቱ አገሮች ላያስገባ ይችላል ወይም በሸንገን ቪዛ ህግ ተጠቃሚ መሆን  ሊታገድ ይችላል፤ ሦስተኛ የዲፕሎማት ፓስ ፖርት ለያዙ ኢትዮጳያውያን ተጓዦች በነጻ ይሰጥ የነበረው የመግቢያ ቪዛ ከእንግዲህ ሊያስከፍል የሚችል  ሲሆን፤ አራተኛ፤ የቪዛ ማመልከቻ ውሳኔ የሚሰጥበት ግዜ አአስራ አምስት ቀናት እስከ አርባ አምስት ቀናት ሊራዘም  ይችላልም ተብሏል። 

ለምን በኢትዮጵያውያን ላይ

ውሳኔው ግዚያዊ እንደሆነና ላልተወሰነ  ግዜ እንደሚቆይ ቢገለጽም የተወሰነ የግዜ ገደብ ግን አልተቀምጠለትም።  የውሳኔውን ይዘትና ተግባራዊነት እንዲሁም ህብረቱ ለምን በዚህ ወቅት በኢትይጵያውያን ላይ ይህን ውሳኔ ሊያስተላለፍ እንደቻለ ዲደብሊው DW የህብረቱን ቃል አቀባይ  ሚስተር ዮሀንስ  ክሌይስን በካውንስሉ ተግንቶ አነጋግሯል። ሚስተር ክሊይስ ግን መግለጫውን በስልክም ይሁን በኢሜይል ወይም በግምባር እንዲያብራሩ እንጂ ለሜዲያ እንዲናገሩ የተፈቀደላቸው ባለመሆኑ ድምጻቸውን ማካተት አልቻለንም፡፤ በግምባር በሰጡን ማብራሪያ፤ ውሳኔው፤ ባጭሩ የህብረቱ የቪዛ አሰጣጥ ደንብ ቁጥር 810/2009 ላልተወሰነ ግዜ በኢትዮጵያውያን ላይ ተግባራዊ እንዳይሆን የሚያዝ መሆኑን ገልጸዋል። የህብረቱ የቪዛ አሰጣጥ ደንብ  ለሸንገን አገሮችለሚስጥ ቪዛ የተቀመጡ መስፈርቶችንና የትራንሲት ቪዛ ህጎችን ያስቀመጠ ቢሆንም፤ ይህ ውሳኔ ግን ህጉ በኢትዮጵያውያን ላይ ላልተወሰነ ግዜ ተፈጻሚ እንዳያሆን ያዛል ብለዋል ሚስተር ዮሃንስ።

ሚስተር ጆነስ አክለውም ኮሚሽኑ የህጉን አፈጻጸምና ትብብርን በሚመለክት የሶስተኛ አገሮችን በመገምገም ምክረሀሳብ የሚያቀርብ መሆኑን በመግለጽ፤ በኢትዮጵያ ላይ የተላለፈው ውስኔም ኮሚሽኑ ባቀረበው ሪፖርትና ምክረሀስብ መሰረት መሆኑን ገልጸዋል ። ኢትዮጵያን ለዚህ ውስኔ የዳረግትን የኮሚሽኑን የግምገማ ሪፖርትና ምክረ ሀሳብ በሚምለክትም፤ ኢትዮጵያ በተመላሽ ስደተኞች  አቀባበል ላይ ዳተኛ ናት ወይም ተባባሪ አይደለችም  በሚል በቀረበባት ክስና ምክረ ሀስብ ምክኒያት መሆኑን አስርድተዋል። ሚስተ ዮሃንስ አክለውም  እስካሁን ከአፍርቃ የዚህ አይነት ውሳኔ የተላለበፈባት አገር ጋምቢያ ብቻ መሆኗንም አንስተዋል።

የአዉሮጳ ህብረት ባንዲራ
የአዉሮጳ ህብረት ባንዲራ ምስል Pond5 Images/IMAGO

የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በህብረቱ የስደተኞች ፖሊስ ላይ

የአውሮጳ ህብረት በባህርና በልዩ ልዩ መንገዶች ወደ አውሮጳ የሚገብትንና ህገ-ወጥ የሚላቸውንና የተገን ጥያቄያቸው ተቀባየነት ያላገኙትን ስደተኖች አስገድዶ ሲልክ፤ አገሮች እንዲቀበሉ የሚጠይቅ ሲሆን፤ ብዙዎቹ አገሮች ያለፈቃዳቸው ተገደው እንዲመለሱ የሚደረጉ ሰዎችን ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ነው የሚገለጸው። ሆኖም ግን ህብረቱና አባል አገሮቹ  በተለይ ከጥቂት ግዚያት ወዲህ ስደተኖች ክመጡባቸው ብቻ ሳይሆን ከሌሎች አገሮች ጋር ጭምር ትብብር በመፍጠር እንዲመለሱ ለማድረግ ሲጥሩ ነው የሚስተዋለው።

የስደተኞችና ሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ስደተኖችን አስገድዶ ወደ መጡባቸው ወይም ሌሎች አገሮች መልሶ መላክን አጥብቀው የሚይወግዙ ቢሆንም፤  የአውሮጳ አህብረትና አባል አገሮቹ ግን ለጩኸት አቤቱታው ጆሮ የሰጡ አይመስሉም፤ ይልቁንም በማይተባበሯቸው አገሮች ላይ  እርማጃዎችን እየወሰዱ ነው። ኢትዮጵያስ  ህብረቱ በዜጎቿ ላይ የጣለባትን የቪዛ ቁጥጥር፤ ተመላሽ ስደተኞን ለመቀበል በመተባበር   ታስነሳ ይሆን! ወይንስ ሌላ የመደራደሪያ ካርድ አላት?

 

ገበያው ንጉሴ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ