በአውሮጳ የስደተኞች ቁጥር መጨመር በሰኔው የኅብረቱ ምክር ቤት ምርጫ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ
ማክሰኞ፣ የካቲት 26 2016በጎርጎሮሳዊው 2023 ከአንድ ሚሊዮን አንድ መቶ አርባ ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ አውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት መግባታቸውን በአውሮጳ ኅብረት የተገን ጠያቂዎች ጉዳይ የሚመለከተው በምህጻሩ (EUAA) የተባለው ድርጅት አስታውቋል። ይህ አሀዝም ከጎርጎሮሳዊው 2015 እስከ 2016ዓ ም ወደ አውሮጳ በገፍ ከገቡት ስደተኞች የላቀ ነው ተብሏል።ያኔ ስደተኞች በገፍ የገቡት በኅብረቱ አባል ሀገራትና አባል ባልሆኑት ኖርዌይና ስዊዘርላንድም ጭምር ነበር። በ2023 በአውሮጳ ከለላ እንዲሰጣቸው ከጠየቁት ስደተኞች ጀርመን 29 በመቶውን ማለትም ከ330 ሺህ የሚበልጡትን ተገን ጠያቂዎችን ተቀብላለች። ፈረንሳይ 167ሺህ ስፔይን 162 ሺህ ኢጣልያ 136 ሺህ የህዝቧ ቁጥር አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ህዝብ ያላት ቆጵሮስ 12 ሺህ የተገን ጥያቄ ማመልከቻዎችን ተቀብለዋል።
በዓመቱ ጥገኝነት እንዲሰጣቸው ካመለከቱት ውስጥ እንዳለፉት ዓመታት ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ሶሪያውያን ናቸው። 181 ሺህ ሶሪያውን በአውሮጳ ተገን ጠይቀዋል። ሁለተኛውን ደረጃ የሚይዙት ደግሞ የአፍጋኒስታን ዜጎች ናቸው። 114 ሺህ አፍጋናውያን በኅብረቱ ከለላ አንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። በ2023 በአውሮጳ ኅብረት ዓለም አቀፍ ከለላ እንዲሰጣቸው የጠየቁ የቱርክ ዜጎችም ቁጥር በ82 በመቶ ጨምሮ ከ100 ሺህ በልጧል። የቀኝ ጽንፈኛው «አማራጭ ለጀርመን» ፓርቲ መጠናከርና ስጋቱበዚሁ ዓመት አውሮጳ ተገን የጠየቁ ፍልስጤማውያን ስደተኞች ቁጥር ጨምሯል በ2022 ፣ 6700 ነበረ በ2023 ግን ከ11 ሺህ በልጧል። በ2023 ወደ አውሮጳ የገቡ ስደተኞች ቁጥር ይፋ የተደረገው በመጪው ሰኔ ለሚካሄደው የአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት አባላት ምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች የምርጫ ዘመቻ በጀመሩበት ወቅት ነው።
የአውሮጳ ኅብረት ባለፈው ታኅሳስ ቀኝ ጽንፈኞች የመራጩን ድምጽ ለማግኘት አጀንዳ ለሚያደርጉት ሕገ-ወጥ ለሚሉት ስደት መፍትሄ ይሆናል ባሉት የስደት ሕግ ማሻሻያ ተስማምተዋል። ይሁንና በጉዳዩ ላይ በቅርቡ በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት መሠረት በሰኔው ምርጫ ቀኝ ጽንፈኞች ከፍተኛ ድምጽ ያገኛሉ ተብሎ እያሰጋ ነው። በዚህ ላይ አስተያየቱን የሰጠን የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ ቀኝ ጽንፈኞች በአሁኑ ምርጫ ከቀደሙት ዓመታት የላቀ ድምጽ ሊያገኙ ይችላሉ የሚባልባቸውን ምክንያቶች ገልጿል።የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት የተስማሙበት የስደት ሕግ ማሻሻያ አንዱ ዓላማው ቀኝ ጽንፈኞች አጀንዳቸው አድርገው ብዙ የመራጭ ድምጽ ለሚያገኙበት ከስደተኞች ጋር ለሚያያዙ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ነበር። ማሻሻያው ከቀደመው በተለየ ሕገ ወጥ የሚባሉ ስደተኞችን ማመልከቻዎችን በፍጥነት አይቶ ውሳኔ መስጠትን ፣ድንበር ላይ የስደተኞች ማቆያ ማዕከላትን ማዘጋጀትንና ጥያቄአቸው ተቀባይነት ያላገኘ ስደተኞችን በፍጥነት ወደመጡበት ማባረርን ያካትታል።ከዚህ ሌላ የኅብረቱ አባል ሀገራት ተገን ጠያቂዎችን እንዲከፋፈሉ ለመውሰድ ፈቃደኛ ያልሆኑ ደግሞ ስደተኞቹን ለተቀበሉት ሀገራት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ነው።
የሰኔው ምርጫ ውጤት ትንበያ ቀኝ ጽንፈኞች ብዙ ድምጽ እንደሚያገኙ ማመልከቱ የአውሮጳ ኅብረት በቅርቡ የተስማማበት የስደት ሕግ ማሻሻያ ችግሩን ለመፍታት ያለውን አቅም አነጋጋሪ ማድረጉ አልቀረም። ሆኖም ማሻሻያው በሂደት የሚፈጸም መርሃ ግብር በመሆኑ አሁኑ ውጤት ያመጣል ተብሎ አይጠበቅም። በአውሮጳ ኅብረት የተገን ጠያቂዎች ጉዳይ የሚመለከተው ድርጅት እንዳለው ያሰባሰባቸው መረጃዎች በአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ጊዜያዊ መጠለያ የተሰጣቸውን 4.4 ሚሊዮን የዩክሬን ስደተኞችን አላካተተም ። ድርጅቱ እንደሚለው በ2023 ተገን እንዲሰጣቸው ካመለከቱ ስደተኞች ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያገኘው 43 በመቶ ብቻ ናቸው። የቀኝ ጽንፈኞች እንቅስቃሴ በጀርመን
በታኅሳስ ወር የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት የተስማሙበትን የስደት ሕግ ማሻሻያ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ይቃወማሉ ። የተሻሻለው የአውሮጳ ኅብረት የስደተኞች ሕግ ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ ውጤት ያመጣል ብለው አያምኑም። ከዚያ ይልቅ መፍትሄ ይሆናል የሚሉት የስደት መነሻ በሆኑ ሀገራት ለስደት መንስኤ የሆኑ ምክንያቶችን መከላከል ነው።
ምንም እንኳን ኅብረቱ ከቀኝ ጽንፈኞች በኩል የመጣበትን ፈተና ለመቋቋም የስደት ሕጉን ቢያሻሽልም አማራጭ ለጀርመን የተባለው ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ፣ ስደተኞች ጀርመን መግባታቸውን በመቃወም ያገኘው የሕዝብ ድጋፍ ወደ 19 በመቶ አድጓል።
በሰኔው ምርጫ ላይ በቅርቡ የዳሰሳ ጥናት ያካሄደው ዩሮፕ ኤሌክትስ የተባለው ድርጅት ከጥናቱ ውጤት በመነሳት ፓርቲው ጀርመን በምክር ቤቱ ካሏት መቀመጫዎች 22ቱን ያሸንፋል የሚል ትንበያ አውጥቷል። ይህም የክርስቲያን ዴሞክራቶችና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ያገኛሉ ተብሎ ከታሰበው መቀመጫ ብዛት ሁለተኛው ቦታ ነው። ለዶቼቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ የአውሮጳ ፖሊሲ ማዕከል የተባለው የጥናት ተቋም ከፍተኛ የፖሊሲ ተመራማሪ አልቤርቶ ናይድሀርት የጀርመንም ሆነ የሌሎች የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲዎች የተገን ጠያቂዎች ቁጥር መጨመርን አጀንዳቸውን ወደፊት ለማራመድ ይጠቀሙበታል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። ዋነኛዎቹ ፓርቲዎች ማለትም የመሀል ቀኞቹ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረትና የመሀል ግራው የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ስደትን የተመለከተ መርሀቸውን በማሻሻል መራጮቻቸውን ለማሳመን እየሞከሩ ነው። ሆኖም በመጪው የአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት ምርጫ ላይ ቀኝ ጽንፈኞቹ ቀንቷቸው ብዙ ድምጽ ካገኙ ግን በኅብረቱ ፖሊሲዎች ላይ ተጽእኖ ማድረጋቸው አይቀርም።
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ