ሁለተኛ ቀኑን የያዘዉ ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ ጉባዔ በበርሊን
ማክሰኞ፣ ኅዳር 11 2016
ጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ላይ የተሰየመዉ እና ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን የያዘዉ የቡድን 20 “ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ” ከ12 በላይ የአፍሪቃ ሀገራት መሪዎችን እንዳሰባሰበ ዛሬም ዉይይቱን ቀጥሏል። ቡድን 20 ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ ጀርመን ለአፍሪቃ የምታደርገዉ አንዱ የጋራ ትብብር ሥራ ነዉ። ስብስቡ የአፍሪቃን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ተጨማሪ የግል መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾችን ለማግኘት ያለመም እንደሆን ተነግሯል።
በጀርመን አዘጋጅነት በሚካሄደዉ በዚህ ጉባኤ ከአፍሪቃውያን መሪዎች በተጨማሪ የአውሮጳ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርሱላ ፎን ደርላየን፣ የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ የኔዘርላንድስ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩተ ተሳታፊ ናቸዉ። የቡድን 20 “ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ” በጎርጎሮሳዊው 2017 ጀርመን የቡድን 20 ፕሬዝደንት ሳለች የተጀመረ ነው። ኢትዮጵያን ወክለዉ በጉባኤዉ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ ባለፈዉ እሁድ ምሽት በጀርመኑ መራሄ መንግሥት ኦላቭ ሾልዝ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በርሊን ጀርመን መምጣትን ተከትሎ፤ ከጀርመን እና ከሌሎች አዉሮጳ ሃገራት የተሰባሰቡ ኢትዮጵያዉያን ጉባዔዉ ከሚካሄድበት አዳራሽ አቅራብያ ካለፈዉ እሁድ ጀምሮ ተቃዉሞዋቸዉን ያሰሙ የነበሩት ኢትዮጵያዉያን ዛሬ እቦታዉ ላይ እንዳልነበሩ የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለሚካኤል ነግሮናል። ሙሉዉን ቃለ ምልልስ የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ!
ይልማ ኃይለ ሚካኤል
አዜብ ታደሰ
ዮኃንስ ገብረግዚአብሔር