1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ለአፍሪቃ የምታደርገዉ ድጋፍ መተቸቱ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 21 2011

ጀርመን «ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ» በሚል ለተወሰኑ የአፍሪቃ ሀገራት የምታደርገዉ የኢኮኖሚ ድጋፍ የሰብዓዊ መብትን፣ የህግ የበላይነትና  የዲሞክራሲ ጉዳዮችን ችላ ያለ ነዉ ሲል መቀመጫዉን ጀርመን ያደረገዉና ለተጨቆኑ ሰዎች መብት የሚሟገተዉ »ጌዘልሻፍት ፎር በድህሮተ ፎልከር» የተባለዉ  የሰብዓዊ መብት ድርጅት ተቸ።

https://p.dw.com/p/37RGu
Deutschland Gesellschaft für bedrohte Völker Logo

«የሲቪሉን ማህበረሰብ በመደገፍ ረገድ ዕቅዱ ያለበትን እጥረት እንተቻለን።»

ዕቅዱ  በግጭት ዉስጥ የቆዩና ኢኮኖሚያቸዉ የተጎዳ የአፍሪቃ ሀገራትን፣ እንዲሁም፣  የሲቪሉን ማህበረሰብ ያገለለ ነዉ ሲል  የድርጅቱ ሊቀመንበር ኡልሪኽ ዴልዩስ  ገልጸዋል።

»ጌዘልሻፍት ፎር በድህሮተ ፎልከር» የተባለዉ  የሰብዓዊ መብት ድርጅት  ድርጅቱ በትናንትናዉ ዕለት በበርሊን ከተማ ጀርመን የተጀመረዉን  የአፍሪቃ መሪዎች ጉባኤ አስመልክቶ  ባወጣዉ ዘገባ »ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ» በሚል ጀርመን ከዓንድ ዓመት በፊት ለ11 የአፍሪቃ ሀገራት የጀመረችዉ  የኢኮኖሚ ድጋፍ ድሃ ሀገራትን በቅጡ ያላካተተና ለሰብዓዊ መብትም ቅድሚያ ያልሰጠ ነዉ ። 
የድርጅቱ ሊቀመንበር ሚስተር ኦሊሪሽ ዴሉስ ለDW እንደገለፁት የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለኢኮኖሚ እድገት ላይ የሚሳድሩት ተፅዕኖ ቀላል ባለመሆኑ በትናንትናዉ ዕለት  በበርሊን  የተጀመረዉ የ12ቱ የአፍሪቃ ሀገራት ጉባኤም፤ ይህንን ሊመረምር ይገባል ብለዋል።በሌላ በኩልም በአንድ ሀገር ዉስጥ የሚካሄድ  ሙስናን ለመዋጋትና ዲሞክራሲን ለማጎልበት የስቪሉ ማህበረሰብ ሚና ወሳኝ ሚና ቢሆንም፤ የተወሰኑ የአፍሪቃ ሀገራት ብቻ የተካተቱበት  ይህ የኢኮኖሚ ስምምነት ግን ይህንን ያገለለ ነዉ ሲል የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ወቅሷል።

"Compact with Africa"-Konferenz in Berlin
ምስል picture-alliance/dpa/B. von Jutrczenka

«የሲቪሉን ማህበረሰብ በመደገፍ ረገድ ዕቅዱ ያለበትን እጥረት እንተቻለን።ለምሳሌ በኢትዮጵያ በአሁኑ ስዓት የሲቪሉን ማህበረሰብ አስፈላጊነት ማጠናከር ይገባል።ምክንያቱም ዲሞክራሲንና የህግ የበላይነትን ለማጠናከር ሚዛናዊ ትችት አስፈላጊ ነዉና።»
ዕቅዱ  የቀጥታ የዉጭ መዋዕለንዋይ ፍሰት ላይ  በማተኮር  የሰብዓዊ መብትንና የሲቪሉን  ማህበረሰብ ከማግለሉ በተጨማሪ በግጭት ዉስጥ የቆዩ እንደ ደቡብ ሱዳንና መካከለኛዉ አፍሪቃ ሪተብሊክ  የመሳሰሉ ሀገሮችን አለማካተቱም  ተገቢ አይደለም ነዉ ያሉት።
ዕቅዱ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በዲሞክራሲ፣ በህግ የበላይነትና በሰብዓዊ መብት አያያዝ ረገድ መሻሻል እያሳዩ ያሉ ሀገሮችን ለመደገፍም የካተተዉ ነገር የለም ሲሉ ተችተዋል።
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተጀመረዉ የሰላም ግንኙነትም ለምስራቅ አፍሪቃ ሰላምና የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተዉ አስተዋፅኦ በጀርመን ሊበረታታ ይገባል ብለዋል።
»አሁን በአፍሪቃ ቀንድ በአለፉት ሁለት አስርተ አመታትት በቀጠናዉ ያላየነዉ የተለዬ ጥሩ ሁኔታ ነዉ ያለዉ።እናም ይህንን ዕድል ሰላምን ዲሞክራሲንና  የሀራትን  የጋራ መከባበር ልናጠናክርበት ይገባል ብዬ አስባለሁ።ሁሉም ነገር ባለፉት 30 እና 40 አመታት በቀጠናዉ ያላየነዉ ነዉ።እናም ይህንን ሂደት ለመደገፍ ዕድሉን ልንጠቀምበት ይገባል።ይህንን የሰላም ሂደት ማጠናከር የአካባቢዉን ሀገራት ኢኮኖሚ ለማጠናከርም በጣም ጠቃሚ ነዉ።»
እንደ ኡሊሪሽ ዴልዩስ ፤በኢትዮጵያ እየታዬ ያለዉ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት መከበር ጅምር በኤርትራ እንዲሰፍንም ሀገሪቱን ከማግለል ይልቅ የተፈጠረዉን የሰላም ዕድል በመጠቀም ሀገሪቱን  ማገዝ  የተሻለ ነዉ ብለዋል።በዚህም ከሀገሪቱ በየ ዓመቱ የሚሰደዱ በርካታ ሰዎችን በሀገራቸዉ ተስፋ እንዲኖራቸዉ ያደርጋል ሲሉ ገልፀዋል።
«ኤርትራን በሚመለከት ብዙ ጥያቄዎችና ተግዳሮቶች አሉ።ነገር ግን ይህንን ዕድል ባለፉት 20 ዓመታት ያስተዋልነዉን ችግር ለመፍታት ልንጠቀምበት ይገባል።ያካልሆነ ግን ስደት ይጨምራል።ሰዎች ሀገራቸዉን ለቀዉ ይሰደዳሉ።ምክንያቱም ሁኔታዉ ካልተሻሻለ ሰዎች በሀገራቸዉ ተስፋ አይኖራቸዉም።ስለዚህ ጉዳዩን ችላ ማለት የለብንም።»
ጀርመን የስደተኞችን ቁጥር መቀነስ ዓላማዋ ከሆነም በተወሰኑ ሀገራት ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከማተኮር ይልቅ  በነዚህ ሀገራት የሚካሄዱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማስወገድና የአካባቢዉን ኢኮኖሚ ለማሳደግ  ከሀገራቱ ጋር አብራ ልትሰራ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
በጀርመን 75 ሺህ የሚጠጉ ኤርትራዉያን ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን በተያዘዉ የጎርጎሮሳዊዉ 2018 ብቻ 15 ያህል ኤርትራዉያን ጥገኝነት ጠይቀዋል።

Ulrich Delius Afrikareferent der Gesellschaft für bedrohte Völker
ኡሊሪሽ ዴልዩስምስል GfbV

ጸሐይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ