1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃውሞ በአዲሱ የኦሮሚያ ክልል አስተዳደራዊ ወሰን

ዓርብ፣ የካቲት 24 2015

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ ያደርጋል ያለውን አስተዳደራዊ አደረጃጀቶችን እና አሠራሮችን በመዘርጋት ላይ መሆኑን በማስረዳት 21ኛ የክልሉ ዞን እንዲመሰረት ውሳኔ ማሳለፉ የተሰማው በዚሁ ሳምንት ነበር ። ይህንን ውሳኔ ተከትሎ በጉጂ ዞን በዚህ ሳምንት የሰው ሕይወትም ያለፈበት የተቃውሞ ሰልፍም መደረጉ ይታወሳል፡፡

https://p.dw.com/p/4OEIr
Äthiopien | Oromiya Region
ምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

በተቃውሞው የሰው ሕይወት ጠፍቷል

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ ያደርጋል ያለውን አስተዳደራዊ አደረጃጀቶችን እና አሠራሮችን በመዘርጋት ላይ መሆኑን በማስረዳት 21ኛ የክልሉ ዞን እንዲመሰረት ውሳኔ ማሳለፉ የተሰማው በዚሁ ሳምንት ነበር ። የክልሉ መንግስት ምክር ቤት አደረግሁ ባለው 6ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ጉባኤ ምስራቅ ቦረና የተባለውን 21ኛ ዞን ከቦረና፣ ጉጂ እና ባሌ ዞኖች የተወሰኑ ወረዳዎችን በማገኛነት መሰረትኩ ማለቱ በተለይም በጉጂ ዞን ውስጥ ቅሬታ እያስነሳ ነው ፡፡ በተለይም አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ነዋሪዎች ውሳኔው ከዚህ በፊትም ቅሬታ ሲነሳበት በቆየ አከባቢ ያለ ሕዝብ ውይይት የተላለፈ በመሆኑ በአከባቢው የሰላም ጠንቅ ሊሆን ይችላል ብለዋል ። 

“ቅሬታ የፈጠረው ትልቁ ጉዳይ አንድ ዞን አንስቶ በሌላ መተካቱ ነው፡፡ ይህ የህዝብ ውይይትን በመሰረታዊነት ያስፈልገው ነበር፡፡ ህዝብን ሳያወያዩ በጉጂ ስትጠራ የነበረችውን ታሪካዊት ቦታ የዞኑን ማህበረሰብ በየደረጃው ሳያወያዩ እንዴት ነው ለሌላ ዞን ተላለፎ የሚሰጠው ብለን ነው የጠየቅነው፡፡ ይህ ጥያቄ የሁለቱን የኦሮሞ ጎሳ የመለየት አይደለም፡፡ ህዝቡ አንድ ነው፡፡ በአንድነትም አብሮ እየኖረ ይገኛል፡፡ አንዳንድ ከተሞች ደረጃቸው አድጎ ተጠሪነታቸው ለክልሉ ይሆናል መባሉም አልጎረበጠንም፡፡ እያልን ያለነው አይደለም ዞን አንድ ቀበሌ ሌላ ወረዳ ስር ለማስገባትም ነዋሪውን ህዝብ በማወያየት መወሰን አለበት የሚል እምነት ነው ያለን፡፡ ይህ አውቅልሃለው የሚለው ቅሬታ ፈጥሮ ህዝብ እንዳያጋጭ ሰግተናል፡፡”

ይህን አስተያየት የሰጡን በሰሞነኛው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የአዲስ ዞን ምስረታ ቅሬታ የገባቸው የጉጂ ዞን አዶላ ሬዴ ወረዳ ነዋሪ ናቸው ፡፡ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲቆይ ጠይቀው አስተያየቱን የሰጡን እኚህ ነዋሪ፤ ውሳኔው ህዝብን ካለማወያየትም ባለፈ አድሎአዊ አሰራር የታየበት ነው ይላሉ፡፡ 

መልክዓ መድር በኦሮሚያ ክልል
መልክዓ መድር በኦሮሚያ ክልልምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

“ይህ ውሳኔ ከተላለፈበት ቀን ጀምሮ እስካሁን ሰው ሁሉ ፊቱን ቋጥሯል ፡፡ እርሰበራሱም ሳይነጋገር ዝም ብሎ እየተያየ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም ባለው የአስተዳደር ወሰን ችግር አንድ ቋንቋ የሚናገረውና የሚጎራረሰውን ህዝብ ሲያጋችጭ ቆይቷል፡፡ ጉጂ ቦረና ውስጥ፤ ቦረናም ጉጂ ውስጥ ነው ያለው፡፡ አይደለም ኦሮሞና ኦሮሞ ብሔር ብሔረሰብ ነው እዚህ ሞልቶ ያለው፡፡ ማንም ማንንም የመግፋት ፍላጎት የለውም፡፡ በአውቅልሃለሁ መደረጉ ግን መፍትሄ ሆኖ የህዝቡን ቅሬታ የሚመልስ አይመስልም፡፡”

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ባለፈው ሰኞ አደረኩ ባለው 6ኛ የስራ ዘመን 2ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ጉባኤ ምስራቅ ቦረና የተባለውን 21ኛ ዞን ከቦረና፣ ጉጂ እና ባሌ ዞኖች የተወሰኑ ወረዳዎችን በማገኛነት እንዲመሰረት ያስተላለፈውን ውሳኔ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት የ21ኛው የኦሮሚያ ዞንከቦረና ሞያሌ፣ ጉቺ እና ዋችሌ ወረዳዎችን፤ ከጉጂ ጉሚ የልደሎ እና ሊበን ወረዳዎች እንዲሁም ነጌሌ ቦረና ከተማን፤ እንዲሁም ከባሌ ዞን መደወላቡ፣ ኦቦርሶ እና ሀረና ቡሉቅ ወረዳዎችን ያካትታል፡፡ በውሳኔው መሰረት ከዚህ በፊት የጉጂ ዞን ዋና ከተማ ሆና ስታገለግል የነበረችው ነገሌ፤ ነጌሌ ቦረና በሚል መጠሪያ የምስራቅ ቦረና ዞን መቀመጫ ትሆናለች፡፡ አዶላ ሬዴ ደግሞ የጉጂ ዞን ዋና ከተማ እንድትሆን ነው የተወሰነው፡፡ 

ይህንን ውሳኔ ተከትሎ በጉጂ ዞን በዚህ ሳምንት የሰው ሕይወትም ያለፈበት የተቃውሞ ሰልፍም መደረጉ ይታወሳል፡፡ በዞኑ ከቦሬ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁን ነዋሪም ውሳኔው ተቃውሞ የገጠመው በህዝብ ውይይት ያልዳበረ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡

“ሰሞኑን ምስራቅ ቦረና ተብሎ በሰየመው ዞን በጣም አዝነናል፡፡ ተግባሩ ጉጂ ላይ የተሸረበ ሴራ አድርገን ነው የተረዳነው፡፡ ከዚህ በፊትም ሁለቱን ህዝብ ሳያማክሩ በተወሰኑ ውሳኔዎች ትልቅ ትንሹ ያለቀበት ግጭት ተፈጥሮ መስዋዕትነት ተከፍሎበታል፡፡ አሁንም ያለ ህዝብ ግንዛቤ እና ይሁንታ የተወሰነ ውሳኔ በመሆኑ ችግር ይፈጥራል፤ እውነትን ያላገናዘበ ሴራም ነው ብለን እንድንረዳ አድርጎናል፡፡” 

ጎጆ ቤቶች በኦሮሚያ ክልል
ጎጆ ቤቶች በኦሮሚያ ክልልምስል Fischer/Bildagentur-online/picture alliance

መንግስት የአዲሱ ዞን አስተዳደር መዋቀር ከሰላምና ፀጥታ እንዲሁም ከህዝብ የመልማት ፍላጎት ጋር አይነተኛ ሚና ይኖረዋል ብልም ቅሬታ ተሰምቶናል ያሉት ነዋሪ ግን አይመስልም ሲሉ በአስተያየታቸው ይሞግታሉ፡፡ 
“ልማትና ሰላምን ማዕከል አድርጎ የተወሰነ ውሳኔ የሚለው እራሱ መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር የማይስማማበት በርካታ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡ ለአብነትም በምስራቅ ቦረና ከተከለሉት ወረዳዎች ሆነው ሞያለ ከነጌሌ የሙሉ ቀን ጉዞ ሲሆን በምስራቅ ጉጂ የተከለለው ጎሮዶላ የተባለ ወረዳ ከዚህች ከተማ የ15 ኪ.ሜ. ርቀት ብቻ ያለው መሆኑ ግራ አጋቢ ነው፡፡ ከባሌ መደወላቡ ወደዚህ ከተማ መካለሉም ቅሬታ ያስነሳው ከርቀቱ በመነሳት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቅርበትን በማማከል ልማትን ለማፋጠን የተሰራ ስራ ነው ብለን ለመቀበል አላስደፈረንም፡፡” 
ስለነዋሪዎቹ ቅሬታ የጉጂ ዞን እና ኦረሚያ ክልላዊ መንግስት፤ በተለይም ለዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ እና ለክልሉ ኮሚዩኒኬሽ ኃላፊዎች በመደወል አስተያየታቸውን ለማካተት ጥረት ብናደርግም ስልካቸው ባለመነሳቱ አልተሳካልንም፡፡ ሰሞነኛው የኦሮሚያ ክልል አስተዳደራዊ መዋቅር ክለሳ ለከተሞች እድገትና የከተሜነት ኑሮን ያሳድጋል በሚል በርካታ ከተሞች እንደየቅርበታቸው እንዲጣመሩም አዳዲስ መዋቅሮችን ይፋ ያደረገ ነበር፡፡