1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል ሁለት ዞኖች ከ85 ሺህ በላይ እንስሳት በድርቅ መሞታቸውን ባለሥልጣናት ገለጹ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 15 2016

በአማራ ክልል በዋግሕምራ ብሔረሰብ አስተዳደር እና በሰሜን ጎንደር ዞኖች በተከሰተ ድርቅ ከ85 ሺሕ በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸውን የየአካባቢዎቹ ባለሥልጣናት ገለጹ። በሁለቱ ዞኖች ብቻ 878 ሺህ እርዳታ ፈላጊዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል እርዳታ ያገኙት 352 ሺህ የሚሆኑት ብቻ ናቸው።

https://p.dw.com/p/4aZA3
የእርዳታ ጭነት
በዋግኽምራ እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች ብቻ ብቻ 878 ሺህ እርዳታ ፈላጊዎች ይገኛሉ።ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል ሁለት ዞኖች ከ85 ሺህ በላይ እንስሳት በድርቅ መሞታቸውን ባለሥልጣናት ገለጹ

ባሳለፍነው ዓመት የክረምት ወቅት በቂ ዝናብ ባለመዝነቡ በአማራ ክልል ሰፋ ባሉ አካባቢዎች ከፍተኛ ድርቅ መከሰቱን ነዋሪዎችና ባለስልጣናት እየተናገሩ ነው፡፡ ተክሊት እንደሻው የተባሉ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሳህላ ሰየምት ወረዳ ነዋሪ ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት፣ በድርቅ ለተጎዱ ሰዎች የሚሰጠው እርዳታ በቂ አይደለም፣ ለሁሉም አይበቃም ነው ያሉት፡፡

“የሐይማኖት አባቶች፣ ... ለተወሰኑ ሰዎች 15 ኪሎ ሰጥተዋል፣ የደረሳቸው ሰዎች አሉ፣ ይህም ሁሉንም ተረጂ ያካተተ አይደለም፣ በባለሀብቶች... እየተባለ ጥቃቅን እርዳታ እየመጣ የተወሰኑ ሰዎች እየተጠቀሙ ነው፣ አሁን እርዳታ መጥቷል እየተባለ ነው፣ ምዝገባ አለ ፡፡” ብለዋል፡፡

ነጋሽ ጎበዙ የተባሉ ሌላ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ነዋሪም በተመሳሳይ ድርቁን ህብረተሰቡ መቋቋም አልቻለም መንግስትም በቂ ድጋፍ አላደረገም ሲሉ ከስሰዋል፡፡
“ችግሩ ባለበት ነው፣ ምንም የተሻሻለ ነገር የለም በተወሰኑ ባለሀብቶች እየተሰጠ ነው ያለው፣  ሁሉንም ያካተተ እርዳታ ግን የለም፣ ለአብዛኛው ተረጂ “ጠብ” ያለ ነገር የለም” ሲሉ አክለዋል፡፡

በእንስሳት ሀብት በኩል ያለው ጉዳት መጠኑ የሰፋና ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ ለእንስሳቱ የሚሆን መኖም ማቅረብ እንዳልተቻለ አመልክተዋል፣ እንስሳቱ ድርቁን መቋቋም አቅቷቸው እየሞቱና እየተሰደዱ እንደሆነ ነው ነዋሪዎቹ የሚናገሩት፡፡

ትግራይ ድርቅ
ጦርነት እና ግጭት የከፋ ተጽዕኖ ባሳደረባቸው የትግራይ እና የአማራ ክልሎች በተከሰተው ድርቅ የሰዎች ሕይወት አልፏል።ምስል Million Haileselassie Brhane/DW

ከችግር ያልተላቀቁት የአበርገሌ ወረዳ አካባቢዎች

ድርቁን ሸሽተው ወደ ሌላ አካባቢ የተሰደዱ እንስሳትም ቢሆ በሄዱበት አካባቢ በቂ ምግብ ማግኘት ባለመቻላቸው “አልቀዋል” ሲሉ ነው ነዋሪዎቹ የችግሩን ጥልቀት የሚገልፁት፡፡

በአማራ ክልል የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ ኃላፊ አቶ ምህረት መላኩ እስካሁን መረዳት ካለበት የህብረተሰብ ክፍል መካከል 42 ከመቶ የሚሆኑት ብቻ የአንድ ዙር እርዳተ አግኝተዋል ብለዋል፡፡

“ለዝቋላ፣ አበርገሌና ሳህላ በድርቅ ለተጋለጡ ለ112 ሺህ ወገኖች የአንድ ዙር እርዳታ ሰጥተናል፣ ይህም መረዳት ካለበት መካከል 44 ከመቶ ብቻ ተደራሽ አድርገናል፣ ቀጥታ በድርቅ ተጠቂ ናቸው ተብለው የተለዩ ሰዎች ወደ 180 ሺህ 580 ናቸው፣ ከድርቁ ጋር ተያያዥ በሆኑ መልኩ ደግሞ አጠቃላይ በሰብል ግምገማ ተጋላጭ ብለን የለየናቸው፣ በዘጠን ወረዳዎችና በሶስት የከተማ አስተዳደሮች 425 ሺህ 130 ናቸው፡፡”

ግጭት የጋረደው ድርቅና የርሃብ አደጋ

የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋትና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰላም ይሁን ሙላት በበኩላቸው፣በዞኑ 453 ሺህ ሰዎች በድርቅ እንደተጠቁ ጠቁመው ለ240 ሽህ እርዳታ ፈላጊዎች የአንድ ዙር እርዳታ ቀርቧል ብለዋል፡፡

“አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ወደ 452 ሺህ 882 ነው፣ ከዚህ ውስጥ ... ከዚህ ውስጥ ወደ 240 ሺህ ለሚሆኑት የመጀመሪያ ዙር እርዳታ አድርሰናል” ነው ያሉት፡፡

ድርቁ በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የሚገልፁት አቶ ምህረት፣ 10 ሺህ እንስሳት ሞተዋል፣ ለ170ሺህ በላይ የሚሆት ደግሞ እንደተሰደዱ ተናግረዋል፡፡
“በሳህላና አበርገሌ ወረዳዎች የተለያየ የእንስሳት ዝርያ ያላቸው 10ሺህ እንስሳት “በድርቁ ምክንት ሞተዋል” የሚል ሪፖርት ደርሶናል፣ ትክክል ነው፣ ወደ 171 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ወደ አጎራባች ወረዳዎች ተሰድደዋል፡፡”ብለዋል፡፡

የአማራ መልሶ ማቋቋምና የልማት ድርጅት (አመልድ)
የአማራ መልሶ ማቋቋምና የልማት ድርጅት (አመልድ) እርዳታ የማሰባሰብ ሥራ መጀመሩንና ከተለያዩ 3 ተቋማት በተገኘ 70 ሚሊዮን ብር የምግብ እህል ገዝቶ ለስርጭት ማዘጋጀቱን አመልክቷል፡፡ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በሰሜን ጎንደር ደግሞ ከ75 ሺህ በላይ እንስሳት በድርቁና ተያያዥ በሽታዎች መሞታቸው መረጋገጡን አቶ ሰላምይሁን አረጋግጠዋል፡፡“በዞኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለው እንሳሳት ጉዳት ደርሶበታል፣ በቴክኒክ ኮሚቴና ጉዳዩን በሚከታተለው ግብረኃይል በተረጋገጠው መሰረት በውሀ እጦትና  በድርቁ ምክንያት በአጠቃላይ ወደ 75 ሺህ የሚሆኑ እንስሳት ሞተዋል፡፡”

በአማራ ክልል ድርቅ ያስከተለዉ ቀዉስ

በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ የአማራ መልሶ ማቋቋምና የልማት ድርጅት (አመልድ) እርዳታ የማሰባሰብ ሥራ መጀመሩንና ከተለያዩ 3 ተቋማት በተገኘ 70 ሚሊዮን ብር የምግብ እህል ገዝቶ ለስርጭት ማዘጋጀቱን አመልክቷል፡፡

ሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶች፣ ባንኮች፣ ባለሀብቶችና ግለሰቦች ተመሳሳ ድጋፍ እንዲያደርጉ የአመልድ ምክትል ዋና ሠራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሽብሬ ጆርጋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአማራ ክልል በአጠቃላይ በ9 ዞኖችና በ43 ወረዳዎች በተከሰተው ድርቅ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች ለርሀብ መዳረጋቸው ታውቋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ