ግጭት የጋረደው ድርቅና የርሃብ አደጋ
እሑድ፣ ታኅሣሥ 7 2016ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ በረሀብ ካስጠራው የ1960ዎቹ ዓም ድርቅ ወዲህ የዝናብ መታጣት ያስከተላቸው የረሀብ ክስተቶች ዓመታትን እያሰለሱ ተከስተዋል። ምንም እንኳን የድርቅ እና የርሃቡ ክስተት በኢትዮጵያ ከ50 ዓመታት በላይ ቢያስቆጥርም ዘላቂ መፍትሄ ባለመፈለጉ አሁንም ዜጎች ለረሀብ ተጋልጠው የድረሱልን ድምፅ እያሰሙ ነው። ሰሜን ኢትዮጵያ ላይ የድርቅ የርሀብ ወሬ መሰማት ከጀመረ ሰነባበተ። በጦርነት ድባብ በከረመችው ትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መረጃ በአሁኑ ወቅት በክልሉ 2 ሚልዮን ዜጎች ለረሃብ ተጋልጠዋል። ቀደም ሲል ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት፤ አሁን ደግሞ በመንግሥት እና በፋኖ ኃይሎች መካከል በሚካሄደው ውጊያ በሚደቀው አማራ ክልልም የድርቅና ረሀብ አደጋው በርካቶችን ለችግር መዳረጉ እየተነገረ ነው። ይኽ ብቻም አይደለም፤ በየቦታው የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችም የሰብአዊ እርዳታ ለማግኘት መቸገራቸን ይገልጻሉ። የእርሻ ምርት ተትረፍርፎባት ስንዴ ወደ ውጪ ለመላክ መብቃቷ እየተወራ፤ ስለቅንጡ ፕሮጀክቶችም ብዙ እየተነገረ ባለበት ሀገር በግጭት ድባብ ውስጥ የተከለለው ርሀብ እያደረሰ ያለው ጉዳት ትኩረት ያገኘ አይመስልም። የረድኤት ድርጅቶች እጃቸውን መሰብሰባቸውም ለረሀብ አደጋው መባባስ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው የሚገልጹም አሉ። ለድርቅና ረሀቡ መፍትሄ ጠፋ? በረሀብ ለሚሰቃዩትስ እንዴት ይደረስ? «ግጭት የጋረደው ድርቅና የርሃብ አደጋ በኢትዮጵያ» የዶቼ ቬለ የዚህ ሳምንት መወያያ ርዕሳችን ነው። በውይይቱየሚከተሉት ነጥቦች ተነስተዋል።
ሸዋዬ ለገሠ