በብሔራዊ ባንክ መመሪያ ላይ የባለሙያዎች አስተያየት
ሐሙስ፣ ጥቅምት 7 2017
ባንኮች የውጭ ምንዛሪ የሚገዙበትእና የሚሸጡበት የዋጋ ልዩነት ከ2 በመቶ እንዳይበልጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን ያወጣው አዲስ መመሪያ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።በዚህም የንግድ በንኮች የውጭ ምንዛሪ የሚገዙበትን ዋጋ ከፍ እያደረጉ የሚሸጡበትን ደግሞ እየቀነሱ መሆኑ ተስተውሏል።
ብሔራዊ ቤንክ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው በሌሎች ሀገሮች ያለውን ተጨባጭ እውነታ እና አሠራር ተንተርሶ መሆኑን ገልጿል።በዚህ ጉዳይ ላይ ሦስት የገንዘብ አስተዳደር እና የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎችን አስተያየት ጠይቀናል ።
"መግዣ እና መሸጫ ዋጋ ስናይ የትም ዓለም ትንሽ ልዩነት ነው ያለው። የገንዘቡን ውጣ ውረድ እሱን ለመቆጣጠር ብሎ ነው [መንግሥት] እና.... አንደኛው ሸማቹን ለመከላከል ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ባንኮቹ ራሳቸው የጥቁር ገበያ ሥርዓት ውስጥ እንዳይገቡ በሚል ይመስለኛል"። ይህ እርምጃ የተወሰደው ብለዋል - ዶክተር ቄስጠንጢኖስ በርኸ ተስፋ።
"የኢትዮጵያ መንግሥት በሁለት የፖሊሲ አጣብቂኝ ውስጥ ያለ ይመስላል። አንድ ጊዜ ነፃ ገበያ አድርገህ ሌላ ጊዜ ደግሞ የብር ዝውውርን በአንድ በኩል ገድበህ በዚያ መካከል የነፃ ገበያ ምህዳራዊ ሁኔታውን እንዴት እንደሚያስኬድ ግራ የሚገባ ነው። ሁለተኛ በነፃ ገበያ ይወሰን ነው የተባለው የውጭ ምንዛሪ ሁኔታው ግን አሁን ደግሞ ብሔራዊ ባንክ ጣልቃ ገብቶ የዋጋ ተመን አስቀምጧል። ይህ ከመጀመርያው ከተነገረን ምክረ ሀሳብ አንፃር እርስ በርሱ የሚጣረስ ነው።..... ቁጥጥር ነው በተዘዋዋሪ"። የፋይናንስና የኢኮኖሚ አማካሪና መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት ታደሰ።
"መንግሥት ጣልቃ በመግባቱ መቃወሜ አይደለም። ግን መርሁ ስለተጣረሰብኝ ነው። በእርግጥ ጣልቃ መግባቱ - መንግሥት ለሕብረተሰቡ ጠቀሜታ ሊኖረው እንደሚችል ነው የሚታሰበው። ለሸማቹ የዋጋ ፋታ ለማግኘት ዕድል እንደሚሰጠው ነው የሚታየኝ"። ሽዋፈራሁ ሽታሁን የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኝ
የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ መግዣ እና መሸጫ ዋጋቸውን ገበያ መር በሆነ መንገድ መተመናቸውን ይቀጥላሉ ይላል።
ሰለሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሰ