1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ባንኮች የውጪ ምንዛሪ መሸጫና መግዣ ተመን ልዩነት ቢያጠቡም የሚያስከፍሉትን ኮሚሽን አላሳወቁም

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ጥቅምት 6 2017

የኢትዮጵያ ባንኮች የውጪ ምንዛሪ መግዣ እና መሸጫ ተመኖቻቸውን ልዩነት የብሔራዊ ባንክን የፖሊሲ ለውጥ ተከትሎ ወደ 2 በመቶ ዝቅ አድርገዋል። በእርምጃው በባንኮች የዶላር መሸጫ ከ6-10 ብር ቀንሷል። ባንኮቹ በተቆጣጣሪው እንደታዘዙት ለደንበኞቻቸው ከውጪ ምንዛሪ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች ሲያቀርቡ የሚጠይቁትን ክፍያ እና ኮሚሽን ይፋ አላደረጉም።

https://p.dw.com/p/4lsiL
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ሜክሲኮ የባንኮች ሕንጻ
የኢትዮጵያ ባንኮች በውጪ ምንዛሪ መግዣ እና መሸጫ ተመኖቻቸው መካከል ያለውን ልዩነት ወደ 2 በመቶ ዝቅ አድርገዋል። ምስል Eshete Bekele/DW

የኢትዮጵያ ባንኮች የውጪ ምንዛሪ መሸጫ እና መግዣ ተመን ልዩነት ወደ 2% ቢያጠቡም የሚያስከፍሉትን ኮሚሽን አላሳወቁም

የኢትዮጵያ ባንኮች በውጪ ምንዛሪ የመግዣ እና የመሸጫ ተመናቸው መካከል ያለውን ልዩነት ተቆጣጣሪው ብሔራዊ ባንክ ይፋ ባደረገው የፖሊሲ ለውጥ መሠረት ወደ 2% ዝቅ አድርገዋል። ትላንት ማክሰኞ ይፋ የሆነው የውጪ ምንዛሪ ግብይትን የተመለከተ ፖሊሲ አስገዳጅ ባይሆንም በባንኮች የውጪ ምንዛሪ መግዣ እና መሸጫ ተመኖች መካከል ያለው ልዩነት በዓለም አቀፍ ልምዶች መሠረት ከ2 በመቶ መብለጥ እንደማይኖርበት ጥቆማ የሰጠ ነው።

ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ለውጡን ይፋ ከማድረጉ በፊት የአብዛኞቹ ባንኮች የውጪ ምንዛሪ የመግዣ እና የመሸጫ ተመን ከ10 በመቶ በላይ ልዩነት ነበረው። ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ለውጡን ይፋ ሲያደርግ ጥቅምት 5 ቀን 2017 አንድ የአሜሪካ ዶላር በ112 ብር ከ39 ሣንቲም ገደማ ገዝቶ በ123 ብር ከ60 ሣንቲም ገደማ የሸጠው መንግሥታዊው ንግድ ባንክ እርምጃ በመውሰድ ቀዳሚ ነበር።

ንግድ ባንክ  የዶላር መግዣውን በ73 ሣንቲም ከፍ አድርጎ መሸጫውን በ8 ብር ከ20 ሣንቲም ገደማ በመቀነስ በሁለቱ ተመኖች መካከል ያለውን ልዩነት ከ10 በመቶ ወደ 2 በመቶ ገደማ ዝቅ አደረገ። የግል ባንኮች ለዶላር መግዣም ሆነ መሸጫ የሰጡት ተመን የተለያየ ቢሆንም በሒደት ልዩነቱን በማጥበብ መንግሥታዊውን ንግድ ባንክ ተከተሉ። ባንኮቹ ልዩነቱን ዝቅ ለማድረግ የውጪ ምንዛሪ መሸጫ ተመናቸውን ከ6 ብር እስከ 10 ብር ቀንሰዋል።

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ “ብሔራዊ ባንክ በቀጥታ ባያስገድድም በንግድ ባንክ በኩል የሚፈልገውን ያስፈጽማል” ሲሉ ይናገራሉ። መንግሥታዊው ባንክ በገበያው ዋጋ የመተመን ሚና እንዳለው የሚያስረዱት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው “ብሔራዊ ባንክ በንግድ ባንክ በኩል ዝቅ ሲያደርግ ሁሉም ተከትለው ወደ 2% አመጡ” ሲሉ የገበያውን አካሔድ አስረድተዋል።

ባንኮች በገበያው ሁኔታ እና ከደንበኞቻቸው ጋር በሚያደርጉት ድርድር የውጪ ምንዛሪ የመግዣ እና የመሸጫ ተመናቸውን የመወሰን ነጻነታቸው እንደተጠበቀ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል። ይሁንና ከውጪ ምንዛሪ ግብይት ጋር በተያያዘ ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች ከደንበኞቻቸው የሚጠይቋቸውን ክፍያዎች እና ኮሚሽኖች በተናጠል በግልጽ ማሳወቅ አለባቸው።

“የውጪ ምንዛሪ ግብይት መሸጫ እና መግዣው ግልጽ መሆን አለበት” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ “በውስጡ ሌሎች ክፍያዎች መካተት የለባቸውም። ሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎች ራሳቸውን ችለው ግልጽ መሆን አለባቸው” ሲሉ ይናገራሉ። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው እንደሚሉት ባንኮች ከውጪ ምንዛሪ ግብይት የሚያገኙት “ትርፍ ጠባብ ሲሆንባቸው ሌሎች ተደራራቢ [ክፍያዎች] ለማካካሻ ይጨምራሉ።”

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን የፖሊሲ ለውጥ ተከትሎ መንግሥታዊው ንግድ ባንክ  የዶላር መግዣውን በ73 ሣንቲም ከፍ አድርጎ መሸጫውን በ8 ብር ከ20 ሣንቲም ገደማ በመቀነስ በሁለቱ ተመኖች መካከል ያለውን ልዩነት ከ10 በመቶ ወደ 2 በመቶ ገደማ ዝቅ አድርጓል።ምስል Eshete Bekele/DW

በውጪ ምንዛሪ መግዣ እና መሸጫ የባንኮች ተመኖች መካከል ያለው ልዩነት ከ12 እስከ 16 በመቶ ይደርስ እንደነበር አብዱልመናን ይጠቅሳሉ። ባንኮች የውጪ ምንዛሪ የመሸጫ ዋጋቸው ሲቀንስ “ከውጪ የሚመጡ ዕቃዎች ላይ ዋጋቸው ቀነስ እንዲል ያደርጋል። የመግዣ ዋጋቸው ከፍ ሲል ደግሞ የውጪ ምንዛሪ እንዲመጣ ያበረታታል” ሲሉ ፋይዳውን አስረድተዋል።

ዶክተር አብዱልመናን እንደሚሉት “ጠባብ የመግዣ እና የመሸጫ ተመን ልዩነት በጣም ቀልጣፋ የሆነ የውጪ ምንዛሪ ግብይት እንዲኖር ያደርጋል።”

ባንኮች ከውጪ ምንዛሪ ግብይት ጋር በተያያዘ በተለይ ዕቃ ከዓለም ገበያ ሸምተው ወደ ኢትዮጵያ ከሚያስገቡ ነጋዴዎች የሚጠይቋቸው ክፍያዎች እና ኮሚሽኖች በውጪ ምንዛሪ መግዣ እና መሸጫ ተመኖች ልዩነት ውስጥ ተካተው ቆይተዋል። ከፍተኛ የባንክ ባለሙያ የሆኑት አቶ ወርቁ ለማ የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ ከመደረጉ በፊት ባንኮች ከደንበኞቻቸው የሚጠይቁት የአገልግሎት ክፍያ እና ኮሚሽን ብዛት “በጣም አስቸጋሪ” ሲሉ ይገልጹታል።

“ከ10 እስከ 15 በመቶ ድረስ የሚያስከፍሉ ባንኮች ነበሩ” የሚሉት አቶ ወርቁ የመተማመኛ ሰነድ (Letter of Credit) መክፈቻ፣ የመተማመኛ ሰነድ ማረጋገጫ፣ አንዳንድ ጊዜ ከፊል ጭነት ሲኖር የከፊል ጭነት ማመቻቺያ (partial shipment arrangement fee) ባንኮች ከደንበኞቻቸው ከሚጠይቋቸው የክፍያ አይነቶች መካከል እንደሆኑ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ባንኮች የውጪ ምንዛሪ ግብይት ተመኖቻቸውን አዘውትረው በሚያሳውቁባቸው ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ወይም በድረ ገፆቻቸው ከደንበኞቻቸው የሚጠይቁትን ክፍያ እና ኮሚሽን እስከ ዛሬ ድረስ በብሔራዊ ባንክ በታዘዙት መሠረት ይፋ አላደረጉም። መሠል ክፍያዎች ባንኮች ሲተምኑ ዓለም አቀፍ አሠራሮችን እንዲመለከቱ የመከረው ብሔራዊ ባንክ ምን ያክል ማስከፈል እንዳለባቸው ገደብ አላኖረም።

ባንኮች የውጪ ምንዛሪ መሸጫ ተመናቸውን ቢቀንሱም አቶ ወርቁ ከደንበኞቻቸው የሚጠይቋቸው የአገልግሎት ክፍያዎች እና ኮሚሽኖች “በሌላ መንገድ” ማስከፈላቸው እንደማይቀር ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት የሎጂስቲክስ ትራንስፎርሜሽን ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት አቶ ወርቁ “ሙሉ በሙሉ ልቅ ተደርጎ ባንኮቹ 15% ወይም 20% እንደፈለጋቸው የሚያስከፍሉ ከሆነ ነገሩን ዝብርቅርቅ ስለሚያደርገው ገደብ ሊቀመጥ ይገባል” የሚል አቋም አላቸው።  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከውጪ ምንዛሪ ግብይት ጋር በተያያዘ ባንኮች ከደንበኞቻቸው የሚጠይቋቸውን የአገልግሎት ክፍያዎች እና ኮሚሽኖች በተናጠል በግልጽ እንዲያሳውቁ አዟል። ምስል Eshete Bekele/DW

“ባንኮቹ ትርፋቸውን ለማሳደግ ነው የሚጣጣሩት። [የውጪ ምንዛሪ] ደግሞ እኔ እንደሚገባኝ የባንክ ጥሪት አይደለም። ብሔራዊ ሀብት ነው” የሚሉት አቶ ወርቁ “ባንኮች የሚያገኙት ትርፍ ምክንያታዊ ሆኖ የሀገር ኤኮኖሚን የማይጎዳ መሆን አለበት፤ ልቅ መሆን የለበትም” ሲሉ ይሞግታሉ።

ባንኮች በሚጠይቁት የአገልግሎት ክፍያ እና ኮሚሽን ላይ ገደብ ካልተደረገ “በውድ ዋጋ የምናገኘው የውጪ ምንዛሪ ሔዶ ሔዶ ኢምፖርት በሚደረጉ ሸቀጦች ላይ ዋጋው ተጨምሮ የዋጋ ግሽበትን ከፍ” ሊያደርግ ሸቀጦች ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገቡ ነጋዴዎችን “የገንዘብ አቅም የሚፈታተን” ሊሆን እንደሚችል አቶ ወርቁ ይሰጋሉ።  

“ብሔራዊ ባንክ እና ባንኮች የተረጋጋ የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት እንዲኖር የሚያስችል በቂ እና አስተማማኝ የውጪ ምንዛሪ ግኝት” እንዳላቸው የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ተናግረዋል። ማሞ “ቁልፍ” ያሏቸውን ስኬቶች ዘርዘር አድርገው ያቀረቡት የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና በዓለም ባንክ ብድር እና ርዳታ ተግባራዊ እያደረገ የሚገኘውን የኤኮኖሚ ማሻሻያ የሁለት ወራት አፈጻጸም ከገመገመ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ ነው።

በዚህ ማብራሪያቸው ኢትዮጵያ ከወርቅ ያገኘችው ገቢ በ2017 የመጀመሪያዎቹ ሦስት ገደማ ወራት ብቻ 500 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንደደረሰ ሲናገሩ ተደምጧል።

የኤኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ከነበረው ወር አኳያ የብሔራዊ ባንክ የውጪ ምንዛሪ ክምችት በ153% የግል ባንኮች በአንጻሩ በ29% እንዳደገ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አስረድተዋል። በማሻሻያው ላይ ከአበዳሪ ተቋማት ጋር በሚደረጉ ድርድሮች በቀዳሚነት ከሚሳተፉ የመንግሥት ሹማምንት አንዱ የሆኑት ማሞ “በትይዩ ገበያው እና በባንክ ገበያው መካከል የነበረው ልዩነት (premium) ከማሻሻያው በፊት ከነበረበት 100% አሁን ከ3% በታች ወርዷል” ሲሉ ተደምጠዋል።

“የትይዩ ገበያው እና የባንክ ገበያው ከሞላ ጎደል ተገናኝቷል” ያሉት ማሞ “በእንደዚህ አይነት የውጪ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያ ውስጥ [ልዩነቱ] ከ10% በታች ከሆነ የተሳካ ነው የሚባለው። የእኛ ከ3% በታች ነው” በማለት “ቁልፍ ስኬት” አድርገው አቅርበውታል።

ዶይቼ ቬለ ባደረገው ማጣራት አንድ የአሜሪካ ዶላር በተለምዶ ጥቁር በሚባለው የጎንዮሽ ገበያ ከ134 እስከ 142 ብር እየተመነዘረ እንደሚገኝ ለመገንዘብ ችሏል። አንድ ዩሮ  ከቦታ ቦታ ቢለያይም በውጪ ሀገራት በሚገኘው ትይዩ ገበያ ከ135 እስከ 142 ብር ይመነዘራል። ማክሰኞ በኢትዮጵያ ባንኮች ከ128 እስከ144 ብር ሲመነዘር የዋለው ፓውንድ በአንጻሩ በትይዩው ገበያ ከ175 ብር በላይ ይከፈልበታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ “በትይዩ ገበያው እና በባንክ ገበያው መካከል የነበረው ልዩነት (premium) ከማሻሻያው በፊት ከነበረበት 100% አሁን ከ3% በታች ወርዷል” ብለው ነበር። ምስል CC BY 2.0/U.S. Institute of Peace

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ “ምን ያህል የተሟላ መረጃ እንዳላቸው አላውቅም” ሲሉ የብሔራዊ ባንክ መረጃ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ። ከውጪ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ በሚላከው ሐዋላ በባንኮች የምንዛሪ ተመን እና በትይዩው ገበያ መካከል ያለው ልዩነት “ከ20 በመቶ በላይ” መድረሱን ዶክተር አብዱልመናን ታዝበዋል። ባለ ብዙ ፈርጆች የሆነው እና በተለምዶ ጥቁር የሚባለው ገበያ ጠባይ ከባንኮች የምንዛሪ ተመን ጋር ያለውን ልዩነት ለማግኘት ፈታኝ ያደርገዋል።

ዶክተር አብዱልመናን ልዩነቱ ወደ 3 በመቶ ዝቅ ብሏል የሚለው የብሔራዊ ባንክ መረጃ “ከየት እንደተገኘም አላውቅም” ሲሉ ይናገራሉ። “የቱ ገበያ ነው? ምን ያህልስ ማጣራት አድርገው?” እያሉ የሚጠይቁት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው “በፍጹም የሚታመን አይደለም” የሚል አቋም አላቸው። አብዱልመናን እንደሚሉት “ከአዲስ ዓመት በኋላ በውጪ ሀገር የትይዩው ገበያ በሚያስገርም ሁኔታ እየጨመረ ነው።”

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሐምሌ 22 ቀን 2016 እስከ መስከረም 30 ቀን 2017 ድረስ በአራት ዙር 282 ሚሊዮን 459 ሺሕ ዶላር ለደንበኞቹ እንደመደበ አስታውቋል። ይሁንና በአራት መደቦች ማለትም ለመድኃኒት እና መገልገያ ቁሣቁሶች፣ ለማሽነሪዎች፣ ለመለዋወጫ መግዣ እና ለአገልግሎት እና የተለያዩ ክፍያዎች ከተመደበው ውስጥ ባንኩ እንደሚለው “እስከ አሁን ያለዉ አማካይ አጠቃቀም 28% ብቻ ነዉ።”

ግሎባል ኢትዮጵያ ባንክ እና ኦሮሚያ ባንክን በፕሬዝደንትነት የመሩት አቶ ወርቁ ግን “ሀገራችን በውጪ ምንዛሪ አቅርቦት ተንበሽብሻ ነው? ወይስ ሌላ ጉዳይ ኖሮ ነው?” የሚል ጥያቄ ፈጥሮባቸዋል። ጉዳዩ “አጠራጣሪ” የሆነባቸው ጉምቱው የባንክ ባለሙያ “እኔ የማውቀው የውጪ ምንዛሪ ግኝታችን እና ፍላጎታችን ያልተጣጣመ መሆኑን እና ፍላጎታችን ከግኝታችን በጣም የሚበልጥ መሆኑን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ