በመቀሌ በሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ ላይ የነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ታሰሩ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 30 2015በመቐለ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ቅስቀሳ ላይ የነበሩ 6 የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ጨምሮ ሌሎች በፖሊስ ተይዘው ታሰሩ። "ኪዳን ለስር ነቀል ለውጥ" በሚል መሪ ቃል በመቐለ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያካሂዱ ሲገልፁ የቆዩት በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሱ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ እና ባይቶና የተባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፥ ህወሓት ሰልፍ ለማደናቀፍ እየሰራ ነው በማለት ከሰዋል። ከሰልፉ ጋር በተገናኘ የመቐለ ከተማ አስተዳደር ለፖርቲዎቹ በላከው ደብዳቤ ፀጥታ የሚያስከብርበት አቅም እንደሌለው የገለፀ ቢሆንም ተቃዋሚዎቹ ግን በትግራይ ያሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ችግሮች የሚንፀባረቁበት ሰልፍ በመጪው ሐሙስ ጳጉሜ 2 ቀን 2015 ዓመተምህረት በሮማናት አደባባይ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።የ33 የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እና የሲቪል ማሕበራት ተቃውሞ
በትግራይ ያሉ ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማንፀባረቅ እንዲሁም ዓለም በትግራይ ያለው ሁኔታ እንዲረዳ የተለያዩ መፈክሮች በመያዝ ሰልፍ ለማድረግ ዝግጅት ላይ ያሉት ሶስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ፥ በትግራይ ያለው 'ህወሓት መር አስተዳደር' ሕጋዊ መብት የሆነው ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይካሄድ የተለያዩ እንቅፋቶች እየፈጠረ ነው በማለት ከሰዋል። የፊታችን ጳጉሜ 2 ቀን 2015 ዓመተምህረት ይካሄዳል የተባለው የተቃውሞ ሰልፍ ለህዝብ ለማስተዋወቅ በመቐለ ከተማ ጎዳናዎች በመኪና እየተዘዋወሩ ይሰሩ የነበሩ ስድስ አባላቶቻቸው ጨምሮ ሌሎች መታሰራቸው የገለፁት ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ የታላቋ ትግራይ ብሔራዊ ሸንጎ ባይቶና እና የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ፥ የገዢው ሐይል አፈና እና ማደናቀፍ ቢቀጥልም ሰልፊ እንደሚደረግ ገልፀዋል።አረና ትግራይ የፕሪቶሪያ ስምምነት በአስቸኳይ ይተግበር አለ "ኪዳን ለስር ነቀል ለውጥ" በሚል የተሰባሰቡት እነዚህ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በትግራይ የሚታይ ፖለቲካዊ ውድቀት፣ ሕገወጥነት፣ በሴቶች ላይ የሚደርስ ፆታዊ አመፅ፣ ዓይን ያወጣ ያሉት በመንግስት መዋቅር የሚደገፍ ዝርፍያና ማጭበርበር እንዲሁም ሌሎች ያልተገቡ ተግባራት እንደሚቃወሙ የገለፁ ሲሆን በትግራይ ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት እንደሚታገሉም ዛሬ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል። የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ኮምኒኬሽን ሐላፊ አቶ ገብረስላሴ ካሕሳይ፥ ሰልፉ ለማስቀረት ህወሓት ሕገወጥ ተግባራት በመከወን ላይ በማለት ይከሳሉ።
ዛሬ በመቐለ ሮማናት አደባባይ አካባቢ እንደታዘብነው፥ የተለያዩ የሰልፊ መፈክሮች እያስተዋወቀ ሲንቀሳቀስ የነበረ ተሽከርካሪ፥ የደንብ አስከባሪ እና ሲቪል ልብስ በለበሱ ታጣቂ እንዲቆም ተደርጎ፥ ተሽከርካሪው እዛው ከነበሩ ስዎች ጋር ወደ ቀዳማይ ወያነ ክፍለከተማ ፖሊስ ጣብያ ተወስደዋል። ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ እንደተረዳነውም ስድስት የፖለቲካ ድርጅቶቹ አባላት ጨምሮ ሌሎች የቴክኒክ ስራ ይከውኑ የነበሩ ግለሰቦች ታስረዋል። ህወሓት ሰልፊ ለማደናቀፍ እየሰራ ነው ያሉት የባይቶና ከፍተኛ አመራር አቶ ዮሴፍ በርሃ በበኩላቸው ሰልፊችን ሰላማዊ ነው፣ አስተዳደሩ ግን ከዓመፅ ተግባራት ጋር እያስተሳሰረው ይገኛል በማለት ወቅሰዋል። አቶ ዮሴፍ "ከጠላት የተላከ ሐይል የለም። ዓመፅ እየጠራ ያለ ሐይል የለም። በደቡብና ምዕራብ ትግራይ የነበሩ የአስተዳደር መዋቅሮች ይፈርሳሉ ስለመባሉትግላችን፣ ሰላማዊ ሰልፋችን ወደ ዓመፅ እንዳይሄዱ አግዙን ነው እያልን እየጠየቅን ያለነው። ፀጥታ አናግዝም ስላሉ የሚቀር ሰላማዊ ሰልፍ ግን የለም። እነሱ እጃቸው ከሰበሰቡልን የትግራይ ህዝብ አመፀኛ አይደለም። እኛም ሰላማዊ ሰልፍ እንጂ ዓመፅ አይደለም የምናደርገው። ግልፅ መሆን ያለበት ይህ ሰልፍ ለውጥ ፈላጊ የትግራይ ልጆች የጠሩት ሰላማዊ ሰልፍ መሆኑ ነው" ብለዋል።
ይህ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ፣ ባይቶናና ሳልሳይ ወያነ ትግራይ የጠሩት "ኪዳን ለስር ነቀል ለውጥ" የሚል መፈክር ያለው የተቃውሞ ሰልፍ፥ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችም ድጋፍ ተችሮታል። ዓረና ትግራይ ባወጣው መግለጫ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የማንም ፍቃድ የማያስፈልገው የህዝብ መብት ነው ያለ ሲሆን ከግጭት የፀዳ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉ ይወጣ ብሏል። ዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲም እንዲሁ የተቃውሞው አካል እንደሚሆን በፖርቲው ከፍተኛ አመራር አቶ መሐሪ ገብራይ በኩል ገልጿል።«የትግራይ ነፃነት ፓርቲ» በህወሓት ላይ ያቀረበው ክስ
የመቐለ ከተማ አስተዳደር ሰልፉ አስመልክቶ ለተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶቹ በላከው ደብዴቤ ሰልፊ የሚደረግበት ቀን ከበዓል ጋር የተቀራረበ በመሆኑ እና በቂ የፀጥታ ሐይል ባለመኖሩ ድጋፍ ለማድረግ እንደማይችል ገልፆ ነበር። ዛሬ ከሰልፉ ጋር በተገናኘ በታሰሩት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና ተያያዥ ጉዳዮች ከከተማዋ አስተዳደር እንዲሁም ፖሊስ ምላሽ ለማግኘት ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ግዜ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካም።
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ