«የትግራይ ነፃነት ፓርቲ» በህወሓት ላይ ያቀረበው ክስ
ሐሙስ፣ ነሐሴ 11 2015በትግራይ በህወሓት እና ጊዚያዊ አስተዳደሩ ውድቀት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ችግሮች ተባብሰው መቀጠላቸውን ተቃዋሚው የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ገለፀ። በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አሁንም ወደቀያቸው አለመመለሳቸው ያነሳው ተቃዋሚው ፓርቲ ይህ በትግራይ ያለው ማሕበራዊ ቀውስ በሂደት እንዲባባስ እንዳደረገው አንስቷል። ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ህዝብ በማስገደድ ለህወሓት የገንዘብ መዋጮ እየተደረገ ነው ያለው የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ይህ ተግባር በሕብረተሰብ ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫና የሚፈጥር ብሎታል። "የአራት ኪሎ ምስለኔ" ያለው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በትግራይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ አይደለም በሚል ወቅሷል።
በትግራይ አሉ ያላቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያነሳበት ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ መቐለ በሚገኘው ፅሕፈት ቤቱ የሰጠው በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው የትግራይ ነፃነት ፓርቲ በህወሓት እና በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ውድቀቶች የትግራይ ህዝብ ለከፋ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ችግር ተጋልጦ እንዳለ አንስቷል።
የትግራይ ነፃነት ፓርቲ እንዳለው በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሰረት በጦርነቱ ምክንያት ቀዬአቸው የለቀቁ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደቀድሞ መኖርያቸው ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም፣ ከሰላም ስምምነቱ አስር ወራት በኃላም ቢሆን እነዚህ ዜጎች በመጠልያዎች እየኖሩ፥ ከሰብአዊ እርዳታ ውጭ ሆነው ለከፋ የኑሮ ሁኔታ መዳረጋቸው ገልጿል።
ለዚህም የሚገባውን ሐላፊነት ባለመወጣት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደርን ወቅሷል። የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ቃል አቀባይ አቶ ገብረስላሴ ካሕሳይ "በፕሪቶሪያው ውል መሰረት የትግራይ ግዛታዊ አንድነት ይረጋገጥ፣ የተፈናቀለው ህዝባችን ወደቀዬው ይመለስ ቢባልም፣ ይሁንና ይህ በተግባር ሳይውል ቀርቶ፣ ህዝባችን በችግር ላይ ችግር እየተደራረበበት የሞት ሞት እየሞተ ነው። ሌላው ይቅርና የነበረው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንኳን በህወሓት ካድሬዎች ተፈርፎ የሚበላው አጥቷል። የህዝብ ችግር ከቁብ የማይቆጥረው የአራት ኪሎ ምስለኔ የሆነው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ከተቋቋመ በኃላ እንኳን በሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን በረሀብ እና በሽታ እንደቅጠል እየረገፉ ነው" ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ፖለቲካዊ ውድቀት ገጥሞታል ብሎ የፈረጀው ህወሓትን የወቀሰው የትግራይ ነፃነት ፓርቲ፥ ህወሓት ከቀድሞ ጥፋቱ ሳይማር አሁንም በተሳሳተ መንገድ መሄዱ ቀጥሎበታ፣ የህወሓት ካድሬዎች በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ህዝቡን በማስገደድ የገንዘብ መዋጮ እንዲያወጣ እያደረጉ ነው ሲል ከሷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁንም የትግራይ የፀጥታ እና ድህንነት ሁኔታ በአስጊ ደረጃ ላይ መሆኑ በፓርቲው የተገለፀ ሲሆን በየቀኑ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ወንበዴዎች ዘረፋ እንደሚፈፅሙ፣ ከግለሰቦች በዘለለ በቅርቡ በሆስፒታሎች ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት ላይ ዘረፋ መከወኑ አስታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪ ድንበሮች ተገቢው ጥበቃ እየተደረገላቸው ባለመሆኑም ከኤርትራ በኩል የሚፈፀም እገታና ዝርፍያ አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል ብሏል። በትግራይ ነፃነት ፓርቲ በኩል በተነሱ ክሶች ዙርያ ከህወሓት እና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምላሽ ለማካተት ያደረግነው ጥረት ለግዜው አልተሳካም። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ እየሰራ መሆኑ በተደጋጋሚ ግዜ ይገልፃል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ