1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምዕራብ ጎንደር ውስጥ በትንሹ 5 ሰዎች በታጣቂዎች ታግተዋል

ረቡዕ፣ ሐምሌ 5 2015

ታጣቂዎች በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ከቋራ ወረዳ ወደ ገንዳ ውሀ የሚጓዝ መኪናን አስቁመው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ማገታቸውን የአካባቢው አስተዳደርና ከእገታ ያመለጠ አሽከርካሪ ተናገሩ። ከታገቱ ሰዎች መካከል አንዱ መገደሉን አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል። ታጣቂዎቹ ያገቷቸውን ሰዎች ለመልቀቅ ከፍተኛ ገንዘብ እየጠየቁ ነው።

https://p.dw.com/p/4TmZB
Äthiopien Entführung in Gonder
ምስል Lemnew Mekonnen/DW

«ታጣቂዎቹ ካገቷቸው ሰዎች ውስጥ አንዱን ገድለዋል» ፤የምዕዕራብ ጎንደር ባለስልጣናት

ታጣቂዎች በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ከቋራ ወረዳ ወደ ገንዳ ውሀ የሚጓዝ መኪናን አስቁመው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ማገታቸውን  የአካባቢው አስተዳደርና ከእገታ ያመለጠ አሽከርካሪ ተናገሩ። አጋቾች ካገቷቸው ሰዎች መካከል አንዱን መግደላቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል። ታጣቂዎቹ ያገቷቸውን ሰዎች ለመልቀቅ ከፍተኛ ገንዘብ እየጠየቁ እንደሆነም ታውቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል «አንድ ዜጋዬ በሰሜን ኢትዮጵያ ጎንደር አካባቢ ታግቶብኛል» ማለቷ ተሰምቷል፡፡

እገታዎች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተበራከቱ መጥተዋል፣ ዋናው የእገታ መነሻም ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቅ ሆኗል፡፡ ሐምሌ አንድ ቀን 2015 ዓም ከቋራ ወረዳ  ደለጎ ከተማ ወደ  ሽንፋና ገንዳውሀ ይጓዝ የነበረን ተሸከርካሪን አስቁመው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎችን ታጣቂዎች አግተው ወስደዋል፡፡ በእለቱ የመኪናው አሽከርካሪ የነበረ ግለሰብ ከመኪናው ወርዶ ጉድጓድ ውስጥ በመግባት ከእገታው እንዳመለጠ አመልክቷል፣ እረዳቱንና ሌሎች ቁጥራቸውን የማያውቃቸው ሰዎች አሁም እንደታገቱ መሆናቸውንም ገልጧል፡፡

Äthiopien Entführung in Gonder
ምስል Lemnew Mekonnen/DW

ከታጋቾቹ መካከል የሌላ አገር ዜጋ ስለመኖሩና የታጋቶችን ቁጥርን በተመለከተ የተጠየቁት እኝህ አሽከርካሪ  በሁለቱም ጉዳዮች ላይ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

እገታዎች ፤ የተፈጠረው ሥጋት እና መፍትሔዎቹእገታው በተፈፀመበት ለምለም ተራራ “ኩሊት” ከተባለ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ አንድ ነዋሪ የታጋቾች ቁጥር በትክክል ባይታወቅም እስከ 9 ሊደርሱ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው ብለዋል፣ አጋቾቹ አንድን ታጋች ወዲያውኑ ከእገታው ቦታ ላይ እንደገደሉትም አስረድተዋል፡፡

የአጋቾቹ መሰረታዊ ትያቄ ገንዘብ መሆኑን ነው አኚሁ አስተያየት ሰጪ ያመለከቱት፣ ከ300 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ብር የማስለቀቂያ ገንዘብ እየተጠየቀ መሆኑን አክለዋል፡፡

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቄ በበኩላቸው እገታውን የፈፀሙት የተለያዩ ኃይሎች ተቀናጅተው መሆኑን ጠቅሰው የአካባቢው የፀጥታ ኃይል ታጋቾችን ለማስለቀቅ እየሰራ እንደሆነ ገልጠዋል፡፡ የታጋቾችን ቁጥር በተመለከተ የተለያየ መረጃ ቢኖርም ለእርሳቸው ቢሮ የደረሰው 5 መሆኑንና አንዱ በታጣቂዎች መገደሉን አረጋግጠዋል፡፡ለእገታ የሚዳረጉት አገር አቋራጭ ሾፌሮች አቤቱታ

ከሰሞኑ እገታ ጋር ይያያዝ አይያያዝ ባይታወቅም የእስራኤል መንግስት አንድ ዜጋዋ በሰሜን ኢትዮጵያ አማራ ክልል “ጎንደር” አካባቢ እንደታገተባት የአገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡

ስለጉዳዩ የተጠየቁት የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቁ ይህን በተመለከተ መረጃ እንደሌላቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አጠቃላይ በአማራ ክልል እየተፈፀመ ላለው እገታ ከአማራ ክልል የፀጥታ ኃላፊዎች ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ያደረግሀት ጥረት አልተሳካም፡፡

ዓለምነው መኮንን 

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ