1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እገታዎች ፤ የተፈጠረው ሥጋት እና መፍትሔዎቹ

ረቡዕ፣ ሰኔ 28 2015

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ አካባቢ ሕፃናትን በማገት ለማስለቀቂያ የሚሆን ገንዘብ ወይም ቤዛ የሚጠይቁ ሰዎች መኖራቸው ተደጋግሞ ታይቷል። ለትምህርት የወጡ ሴቶችም በታጣቂዎች ታግተው አንደነበርም የማይዘነጋ የቅርብ ጊዜ ድርጊት ነው።

https://p.dw.com/p/4TSc3
Dschibuti Tankwagen
ምስል Getty Images/S. Gallup

እገታዎች ፤ የተፈጠረው ሥጋት እና መፍትሔዎቹ

 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተለይ በኢትዮ - ጅቡቲ መስመር ሀገር አቋራጭ ከባድ መኪናዎችን የሚያሽከረክሩ  «ማንነታቸው ባልታወቀ» ሰዎች ወይም በትጥቅ አንጋቾች እየተያዙ ቤዛ እየተጠየቀባቸው ለችግር መዳረጋቸውን ፣ መገደላቸውን፣ ለአካል መጉደል መዳረጋቸውን ባልደረቦቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ሲናገሩ ተደምጧል። 

ይሄው ችግር አሁን ደግሞ ከአዲስ አበባ ወደ ባህርዳር በሚወስደው አውራ ጎዳና በተለይም ዓባይ በረሃ የተባለው አካባቢ ተደጋግሞ በታጣቂዎች እየተፈፀመ መሆኑን አሽከርካሪዎች ተናግረዋል። በጉዳዩ ላይ ተጠይቆ ምላሽ የሰጠው የፌዴራል ፓሊስ እገታ ተፈፀመብን የሚሉት ሰዎች ወይም ዘመዶቻቸው "የትኛው ፖሊስ ጣቢያ ላይ ነው ያመለከቱት" በማለት የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጄላን አብዲ "ፌክ ኒውስ - ሀሰተኛ ዜና እያሰራጩ ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። አክለውም "ሆን ተብሎ ሰላም እንደሌለ አገሪቷን ለማስመሰል ፌክ ኒውስ እየተሰራጨ ነው ያለው ሰው ታግቷል ተብሎ" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የሕዝብ አስተያየቶች 
«እኔ እንደተረዳሁት ሦስት ዓይነት ምክንያቶች አሉ። የመጀመርያዎቹ ራሳቸው ሰዎቹ ሳይታገቱ ታገትን በሚል ለፖለቲካ ተልእኮ ይሁን ለሌላ በዚህ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ አሉ። ሌላኞቹ ደግሞ የገንዘብ ፍላጎት ኖሯቸው የሚንቀሳቀሱ አሉ። ሌላኞቹ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎችን የሚያግቱ አሉ። እነዚያን ገንዘብ የሚጠይቁ አሉ።»
«መንግሥት ባለበት ሀገር ሌባ እንደዚሁ እየጠለፈ ይወስድሃል። እያስገደደ ይቀበልሃል። ምንድን ነው ? ወደ የት ነው የምንሄደው ? እንደዚህ ተኹኖ ወዴት ሊዘለቅ ነው ? በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ቀላል ነገር አይደለም። ይሄ የአመራር ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። አመራሩ ምን እንደሚሠራ እኔ አይገባኝም። ከዚህ በፊት ሰምተነው የማናውቅ ነገር ነው።»
«በየቦታው ላይ ሾፌሮች ይገደላሉ፣ ይታገዳሉ። እሱ እሱ መስተካከል አለበት። ሰው ሁሉ በየሻይ ቤቱ ያወራል። ወሬው ሁሉ በአንድ በኩል ውሸትም አለ ፣ እውነትም አለ።»
የአሽከርካሪ አስተያየት 
«ጅቡቲ መስመር ባለው እስከዛሬ ከነበረው አሁን እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት ሰዓት ነው። መንግሥትም ከፍተኛ የሆነ ሠራዊት በየ ቦታው ላይ አፍስሷል። ከወለንጭቲ ጀምሮ እስከ መተሃራ በፌዴራል ፖሊስ እና በመከላከያ እየተጠበቀ ነው ያለው። አሁን ትልቁ ችግር ያለው ከፍቼ ጀምሮ እስከ ጎሃ ጽዮን የዓባይ በረሃ መጀመርያ ድረስ እሱ ላይ ነው አሁን ትልቅ ተጽእኖ እየተፈጠረ ያለው።» 
የፌዴራል ፖሊስ ምላሽ 
«የትኛው ፖሊስ ጋር ነው ያምለከቱት ? ሀሰተኛ ዜና በጣም እያሰራጩ ነው ያሉት። ፌዴራል ፖሊስ መንገድ ላይ አለ እዛው። አመልክተዋል ወይ ? ሆን ተብሎ [ፌክ ኒውስ] ሰላም እንደሌለ ሀገሪቱን ለማስመሰል እየተሰራጨ ነው ያለው። ሰው ታግቷል ተብሎ። በአስሩም ቀናት ውስጥ አሁን ሰሞኑን ምንም የደረሰን ነገር የለም" በማለት የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጄላን አብዲ ገልፀዋል።
እሳቸው ይህንን ይበሉ እንጂ በጅቡቲውም ሆነ በባህርዳሩ መስመር ከፍተኛ ገንዘብ «ለአጋቾች» ከፍለው የተለቀቁ ሰዎች ስለመኖራቸው የአሽከርካሪዎቹ ባልደረቦች እና የወንጀሉ ሰለባ ሰዎች ለመገናኛ ብዙኃን ቃላቸውን ሰጥተዋል። በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ምክንያቱ ሳይጠቀስ ጠፋ የተባለ ሰው እንደገና ተገኘ እየተባለ በማህበራዊ መገናኛ ዐውታሮች መረጃዎች ይንሸራሸራሉ። እንዲህ ያሉ ዜጎችን ለፍርሃት የሚዳርጉ ክስተቶች ተደጋግሞ ይደመጣሉ። ቤተሰቦቻቸውን ገንዘብ ለመቀበል ሲባል ሳይታገቱ እገታ እንደተፈፀመባቸው ያስመሰሉ ሰዎች ስለመያዛቸውም የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሰሞኑ አስታውቋል።


ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ