1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለው የሱዳን ግጭት

ፀሀይ ጫኔ
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 9 2017

ከጎርጎሪያኑ ሚያዚያ 2023 ዓ/ም ጀምሮ በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ መካከል የሚካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ሱዳንን ለከፋ የሰብአዊ ቀውስ ዳርጓታል። በአስር ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት የሱዳን ጦርነት ሰሞኑን እንደገና ተባብሷል። ይህም የዕርዳታ ስራን በማስተጓጎል ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል።

https://p.dw.com/p/4lzFj
ሱዳን ካርቱም
ሱዳን ካርቱምምስል Stringer/REUTERS

የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለው የሱዳን ግጭት

ከጎርጎሪያኑ ሚያዚያ 2023 ዓ/ም ጀምሮ በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ መካከል የሚካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ሱዳንን ለከፋ የሰብአዊ ቀውስ ዳርጓታል። በአስር ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት የሱዳን ጦርነት ሰሞኑን እንደገና ተባብሷል።
ጦርነቱ ከተባባሰባቸው ቦታዎች ውስጥ የሀገሪቱ ዋና ከተማ ካርቱም አንዱ ሲሆን፤በፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ቁጥጥር ስር ያሉ ቦታዎችን መልሶ ለመያዝ የሱዳን ጦር በከተማዋ ከፍተኛ ጥቃት ከፍቷል። በአካባቢው የሚገኙ ለድንገተኛ አደጋ ድጋፍ የሚያደርጉ ክፍሎች እና ሰላማዊ ዜጎችን በመደገፍ ለዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት ታጭተው የነበሩት  ሲቪል መራሽ ተቋማት እንደገለፁት በቅርቡ በተከሰቱ ግጭቶች በካርቱም ገበያዎች ብዙ ሰዎች ተገድለዋል።

አስከፊ ሁኔታ በኤል ፋሸር

በሱዳን፤ ምዕራብ ዳርፉር ግዛት የምትገኘው ኤል ፋሸር ከተማ  የእርስ በእርስ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሌላዋ ቁልፍ የጦር አውድማ ነች። ሰሞኑን በኤል ፋሸር አቅራቢያ በገበያ ቦታዎች የተኩስ ልውውጦች ተካሂደዋል።
በአቡ ሹክ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩት እና በአካባቢው የድንገተኛ አደጋ  ክፍል  አባል የሆኑት ሳላህ አደም ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ ተኩሱ የበለጠ እየጠነከረ መምጣቱን ለDW ተናግረዋል።
አዳም እንዳሉት ሰኞ እለት አንዳንድ የፍጆታዎችን እቃዎችን ለመግዛት በሄዱበት የገበያ ቦታ የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ የአየር ድብደባ አድርጓል። በአየር ጥቃቱ ሶስት ሰዎች ሲገደሉ 10 ሰዎች ቆስለዋል።  ሸማቾችም ህይወታቸውን ለማዳን ሲሯሯጡ መመልከታቸውን ገልጸዋል።ይህም የሰብዓዊ ሁኔታውን አስቸጋሪ አድርጎታል ይላሉ።«ሁኔታው ​​​​እንዴት እንደ ሆነ መገመት አትችሉም።  ታውቃላችሁ ፣ እኛ በአስከፊ ሁኔታ እያለፍን ነው።  ምክንያቱም አንዳንድ ቤተሰቦች በጭራሽ የሚበሉት ምግብ የላቸውም። ብዙ በሽታዎችም አሉ።በምግብ እጥረት ህፃናት እየሞቱ ነው።በእውነቱ ሁኔታው አስቸጋሪ ነው።»ሲሉ ገልፀዋል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ዘረፋ በማካሄድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ድርጅቶችን ኢላማ አድርገዋል። የኖርዌይ ተራድኦ ድርጅት የሱዳን  ዳይሬክተር ሚሼል ዲአርሲ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ከብዙ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።

የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም
የሱዳን የእርስበእርስ ጦርነት ለሰላማዊ ዜጎች የሚሰጠውን እርዳታ እና ድጋፍ አስተጓጉሏልምስል Volunteer Group South Khartoum Emergency Room/Xinhua/IMAGO

የተረሳ ቀውስ

በቅርቡ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ሃላፊ ፎልከር ቱርክ በኤል ፋሸር የአቡ ሹክ እና በአቅራቢያው በሚገኘው የዘምዘም የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች  ላይ እየደረሰ ያለውን አሰቃቂ አደጋ አስጠንቅቀዋል።
ፎልከር ቱራክ እንዳሉት በእነዚያ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉ ሰዎች በጎሳ ማንነታቸው፤ ይደግፋሉ ተብለው በሚጠረጠሩበት ቡድን እና በሌሎች ምክንያቶች በሁለቱም ተፈላሚ ሀይሎች በኩል በሚደርስባቸው ጥቃት ከፍተኛ አደጋ ላይ ናቸው። 
ቢያንስ 80,000 ሰዎች ባሉበት በዘምዘም መጠለያ ጣቢያም ሰብአዊ ሁኔታው ​​ሊባባስ ይችላል ብለዋል።
ድንበር የለUሹ የሀኪሞች ቡድን  የሱዳን ጦር በማይቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሚደረገውን ዕርዳታ በዘዴ ከከለከለ  ወዲህ በዚህ ሳምንት ስራውን ማቆሙን የቡድኑ፤ የሱዳን አስተባባሪ ክሌር ሳን ፊሊፖ ገልፀዋል። 

በዚህ ሳቢያ 5,000 የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸው እና 2,900  ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸው ህጻናት ድጋፍ ሳያገኙ ቀርተዋል።የሂዩማን ራይትስ ዎች የሱዳን ተመራማሪ ሞሃመድ ኦስማን በበኩላቸው ለተጎጅዎች መድረስ የሚገባው እርዳታ ይዘረፋል ይላሉ።
«ዕርዳታ በሁለቱም ወገኖች ተስተጓጉሏል።የሱዳን መከላከያ ሰራዊት ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች አሁንም ወሳኝ ዕርዳታ እንዲደርስ አልፈቀደም። ፣የፈጥኖ ደራሽ ሀይሎችም በሚቆጣጠሯቸው የአካባቢዎች ለአንዳንድ ሰላማዊ ዜጎች መድረስ የሚገባቸውን አቅርቦቶች እና ዕርዳታዎች እየዘረፉ ይገኛሉ።»
ያም ሆኖ እሳቸው እንደሚሉት ለሁኔታው በቂ ዓለም አቀፍ ትኩረትም የለም። "ይህ በእርግጠኝነት የተረሳ ቀውስ ነው" ሲሉ ለDW ተናግረዋል።
«ስለዚህ ይህ በእርግጠኝነት የተረሳ ቀውስ ነው.።በቂ ዓለማቀፋዊ ትኩረት እያየን አይደለም።ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ እና በመላ ሀገሪቱ የተጎዳውን ህዝብ ያለገደብ እርዳታ እንዲደርሰው ለማድረግም ግፊት የለም።»

ሱዳን ካርቱም
ጦርነቱ ከተባባሰባቸው ቦታዎች ውስጥ የሀገሪቱ ዋና ከተማ ካርቱም አንዱ ሲሆን፤በፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ቁጥጥር ስር ያሉ ቦታዎችን መልሶ ለመያዝ የሱዳን ጦር በከተማዋ ከፍተኛ ጥቃት ከፍቷል።ምስል Lv Yingxu/Xinhua/IMAGO

ግልጽ ያልሆኑ የጦርነት መስመሮች

በጀርመን  ጊጋ  የተባለ የአለም አቀፍ እና የአካባቢ ጥናት ተቋም  የሱዳን አጥኚ  የሆኑት ፤ ሃገ አሊ ሁኔታው ​​ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ መምጣቱን ለDW ተናግረዋል።
ሀገ እንደሚሉት  ከ18 ወራት በፊት ጦርነቱ ሲጀመር የስልጣን ሽኩቻው በሱዳን ጦር  እና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች መካከል ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን በርካታ ቡድኖች እና ፍላጎቶች መኖራቸውን ያስረዳሉ።
«ባለፉት ወራት በተለዬ ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ ከመጣው አዝማሚያ አንዱ ቡድንተኝነት ነው። ማለትም እያንዳንዱ ቡድን በራሱ በተለያዩ ጥያቄዎች ላይ አቋሙ የተለያየ ነው።» ብለዋል።በሱዳን ሰፊ ግዛቶች  በብዙ ግንባሮች  እየተካሄደ ተካሄደ ባለው ጦርነት፣ ማን በትክክል ይሰሰራል፣ ማን ትእዛዝን የፈጽማል በሚል  የማይሰራውን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን አጥኝዋ ገልፀዋል።ከዚህ አንፃር ሁለቱም ተፈላሚ ሀይሎች ከአሁን በኋላ በሀገሪቱ ውስጥ የራሳቸውን ወታደሮች ሙሉ በሙሉ እንደማይቆጣጠሩ ምልክቶች መኖራቸውንም አስረድተዋል። ይህም የሚቆጣጠሯቸውን ግዛት በትክክል ለማስተዳደር  ተግዳሮት እንዳለው አመልክተዋል።

ጦርነትቱ ለሰላማዊ ዜጎች የሚሰጠውን እርዳታ እና ድጋፍ አስተጓጉሏል
የሱዳን የእርስበእርስ ጦርነት ለሰላማዊ ዜጎች የሚሰጠውን እርዳታ እና ድጋፍ አስተጓጉሏልምስል Mohamed Jamal Jebrel/REUTERS

ጦርነቱ እርዳታ እና ድጋፍ አስተጓጉሏል

በጎርጎሪያኑ 2021 ዓ/ም ከተካሄደው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት በኋላ፤ ስልጣን በተጋሩት በጦር ኃይሎች አዛዥ አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን እና በፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ መሪ መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ መካከል በተደረገው የስልጣን ሽኩቻ በተጀመረው የሱዳን የርስ በእርስ ጦርነት፤በሀገሪቱ ቢያንስ 20,000 ሰዎች ተገድለዋል። ነገር ግን እየተካሄደ ባለው ውጊያ እና የጤና  ተቋማት በመጎዳታቸው  የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ መረጃ ማግኘትም ሆነ  ማረጋገጥ ባለመቻሉ የሟቾች ቁጥር ከዚህ ሊያሻቅብ ይችላል።እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባ ከ11 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ወደ ስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች እና ጎረቤት ሀገራት እንዲሰደዱ በማድረግ ጦርነቱ በዓለም ላይ ትልቅ የመፈናቀል ቀውስን አስከትሏል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ እንደገለፀው  ረሃብ እና እንደ ኮሌራ ያሉ በሽታዎች በአካባቢው በመከሰቱ ደግሞ ሁኔታውን የበለጠ አባብሶታል።

በሀገሪቱ የተፈጠረው ይህ መሰሉ ምስቅልቅልም ሰላማዊ ዜጎች የሚቀርበውን እርዳታ እና የድጋፍ አስተጓጉሏል።
የአቡ ሹክ  መጠለያ ጣቢያ የድንገተኛ ክፍል አባሉ ሳላህ አዳም ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች እንዲታደግ በተጎጅዎች ስም ተመፅነዋል።
«እኔ ራሴ፤  ተፈናቃዮቹን ወክዬ እጠይቃለሁ ። እንግዲህ እኛ  ጊዜ በማይሰጥ ችግር ላይ ነን።ለረድኤት ድርጅቶች ፣ ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና በሰብአዊነት ጉዳዮች ላይ እየሰሩ ያሉ ሰዎች በሙሉ፤  የኤል ፋሸርን ህዝብ ለመታደግ አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰዱ ይገባል በማለት ጥሪዬን አቀርባለሁ።»

ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ