የኤሊዜ ውል 60ኛ ዓመት መታሰቢያ
ማክሰኞ፣ ጥር 16 2015ፈረንሳይና ጀርመን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከ18 ዓመት በኋላ የተፈራረሙትን የኤሊዜ ውል 60ኛ ዓመት ባለፈው እሁድ ፓሪስ ፈረንሳይ ውስጥ በተለያዩ ስነስርዓቶች አስበዋል። ውሉ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት በሁለቱ ሀገራት መካከል የተካሄዱት ግጭቶችና ጦርነቶች ትተዉት ያለፉት ጠባሳ እንዲሽርና እርቅ እንዲወርድ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግና ለአውሮጳ ኅብረት ምስረታም መንገድ በመጥረግ ዓይነተኛ ሚና በመጫወት ይነሳል። በውሉ 60ኛ ዓመት መታሰቢያ የጀርመን ካቢኔ አባላት በሙሉ ፓሪስ ነበሩ። የፍራንኮ ጀርመን የሚኒስትሮች ምክር ቤት 23ተኛው ጉባኤም ተካሂዷል። ከሁለቱም ሀገራት የተውጣጡ 300 ሕግ አውጭዎች በታሪካዊው የፓሪሱ የዞርቦን ዩኒቨርስቲ የውሉን የአልማዝ እዮቤልዩ አክብረዋል። የአውሮጳ ኅብረት ሞተር የሚባሉት ጀርመንና ፈረንሳይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንደቀድሞው በተለያዩ ጉዮች ላይ ተመሳሳይ አቋም አለመያዛቸው ልዩነታቸውን እያሰፋ መምጣቱ ይነገራል ።ይሁንና በተለይ የዩክሬኑ ጦርነት ያስከተለውን የኃይል ቀውስ ለመፍታት የነደፏቸው ስልቶች እንዲሁም በወደፊቱ የአውሮጳ ወታደራዊ ትብብር ላይ የያዙት አቋም የተለያየ ቢሆንም ባለፈው እሁድ የኤሊዜን ውል 60ኛ ዓመት ሲያከብሩ የሀገራቱ መሪዎች ትብብራቸውን ይበልጥ አጠናክረው አውሮጳን በጋራ ወደፊት ለማራመድ ቃል ገብተዋል። በስነ ስርዓቱ ላይ የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ሁለቱ ሀገራት ከ60 ዓመት በፊት የኤሊዜን ውል ለመፈራረም ያበቃቸውን ምክንያት አንዲህ አስታውሰው ነበር።
«የአውሮጳ ሀገራት አንድ መሆን ለብዙ መቶ ዓመታት የዘለቀው የፈረንሳይና የጀርመንን ጥላቻ መወገድን ይጠይቃል።»ሲሉ የቀድሞ (የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር)ሮበርት ሹማን በጎርጎሮሳዊው 1950 የተናገሩትን (የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት) ሻርል ደጎልና የጀርመኑ መራኄ መንግሥት ኮናርድ አደናወር ከ12 ዓመታት በኋላ የኤሊዜን ውል በመፈረም እውን አድርገውታል።ይህም ለተወሰኑ መቶ ዓመታት በጀርመንና በፈረንሳይ ሲወርድ ሲዋረድ የነበረውን ጥላቻ እንዲቆም አድርጓል። አዲሱ የትብብር ዘመን ጅማሬ በቀጣዮቹ ዓመታት የማይበጠስ ወዳጅነት እና ወንድማዊ ፍቅርን አስከትሏል። »
በአስራ ዘጠነኛውና በ20ኛው ክፍለ ዘመን የፈረንሳይና የጀርመን ግንኙነት ስር የሰደደ ጥላቻና ተቃውሞ የታየበት ነበር። በሁለቱ ሀገራት መካከል በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱት ግጭቶችና ፖለቲካዊ ፍጥጫዎች በሁለቱ ሀገራት መካከል ረዥም ጊዜ ያስቆጠሩ ጥላቻዎችን አስከትለው ነበር። ፍጥጫዎቹ ካስከተሏቸው ጦርነቶች አንዱ የአንደኛው የዓለም ጦርነት ነው።በዚህ ጦርነት ጀርመንና አጋሮቿ በጎርጎሮሳዊው 1918 ለሽንፈት ተዳርገዋል። ከ21 ዓመት በኋላ የናዚ ጀርመን መሪ አዶልፍ ሂትለር ፖላንድን ሲወር ብሪታንያና ፈረንሳይ በጀርመን ላይ በጎርጎሮሳዊው መስከረም 1939 ጦርነት አወጁ ።በዚህ ጦርነት የጀርመን ወታደሮች ፓሪስንና ከፊል ሰሜናዊ ፈረንሳይን ይዘው ነበር። ፈረንሳይ በአጋሮቿ አማካይነት በ1944 ነጻ ወጣች።ጀርመን በግንቦት 1945 ተሸንፋ እጅ ሰጠች። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳበቃ በጀርመንና በፈረንሳይ መካከል እርቅ ማውረድ የሚታሰብ አልነበረም። ሆኖም የያኔው የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር በኋላም የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሻርል ደጎል የወሰዱት ያልታሰበ እርምጃ ሊሆን አይችልም ለተባለው እርቅ መነሻ ሆነ። ደ ጎል የያኔው የፌደራል ጀርመን መራሄ መንግሥት ኮናርድ አደናወር ወደ ፈረንሳይ የግል ቤታቸው እንዲመጡ ግብዣ አቀረቡ። ይህም የሁለቱን ሀገራት የቀደመ ታሪክ መቀየር የቻለ ልዩ ክስተት ነበር። የግብዣው ዓላማም የፈረንሳይና የጀርመንን ግንኙነቶች በባህል በንግድና በፖለቲካ ደረጃ ማስቀጠል ነበር። ከዚህ በመነሳት ሁለቱ ሀገራት የተከተሉት የእርቅ ሂደት ለአውሮጳ ኅብረትና አንድነት መንገድ ከፈተ።ይህም በሮሙ ውል ፊርማና በ1957 በአውሮጳ የኤኮኖሚ ማኅበረሰብ ምስረታ ተጀመረ።በሐምሌ 1962 አደናወርና ደ ጎል የፈረንሳይ ንጉሶች ዘውድ በጫኑበት ራይም በተባለችው ከተማ በሚገኝ ካቴድራል በተካሄደ የሰላምና እርቅ የጸሎት መርሃ ግብር ላይ ተገኙ።በዚህም ሁለቱ መሪዎች የጀርመንንና የፈረንሳይን ወዳጅነት ለዓለም ይፋ አደረጉ። ከዚህ በኋላም ዓመት ሳይሞላ በጥር 1963 በፈረንሳዩ ኤሊዜ ቤተ መንግሥት ፈረንሳይና ጀርመን የወዳጅነት ውል ተፈራረሙ ።የኤሊዜ ስምምነት መፈረም በአውሮፓ ታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚይዝ ጉዳይ ነው ። በኤሊዜ ውል የአልማዝ ኢዮቤልዩ መታሰቢያ ላይ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ ውሉ ከ60 ዓመት በኋላ ዛሬም ልዩ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን አስታውቀዋልየኤሊዜ ውል 50 ኛ ዓመት
«የኤሊዜ ውል አሁንም በሁለቱ ሀገሮች መካከል የማይለወጥ ተምሳሌታዊ የሆነ ግንኙነት መሰረት ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ሁለቱን ሀገራት ከአንዱ የራይን ወንዝ ዳርቻ እስከ ሌላው የራይን ወንዝ ዳርቻ ላስተሳሰሩ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ድሮች ምስጋና ይግባቸውና ሁለቱ ሀገራት ለሰላም ለነጻነት እና ዴሞክራሲያዊ እሴቶቻቸውን ለመከላከል እንዲሁም በአውሮጳ የጋራ ራዕያቸው እውን ለማድረግ በአንድነት የዘለቁበትም ነው።»
በጎርጎሮሳዊው 1963 ጥር 22 ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በመጀመሪያው የጀርመን መራሄ መንግሥት በኮናርድ አደናወር እና በፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ሻርል ደ ጎል የተፈረመው የኤሊዜ ውል ከወታደራዊ ትብብር አንስቶ እስከ ወጣቶች ልውውጥ ድረስ የሚዘልቅ ነው። ደጎልና አደናወር እውን ያደረጉት ይህ ውል የአውሮጳ የእርቅ ፖሊሲ አዋቂ አስብሏቸዋል። በውሉ ከተካተቱት ጉዳዮች ውስጥ በፖለቲካ ደረጃ አስፈላጊ የሆኑ መደበኛ የምክክር ስብሰባዎችን ማካሄድ፣ በውጭ እና በአውሮጳ የመከላከያ ፖሊሲ እንዲሁም በትምህርትና በወጣቶች ጉዳዮች ላይ መንግስታቱ ይበልጥ ተቀናጅተው እንዲሰሩ ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል።በውሉ መሠረት የተቋቋመው የፍራንኮ ጀርመን የወጣቶች ቢሮ አንዱ ምሳሌ ነው። በዚህ ድርጅት አማካይነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሁለቱ ሀገራት ህጻናትና ወጣቶች ከ320 ሺህ በላይ በሚሆኑ የልምድ ልውውጥ መርሃ ግብሮች ተካፋይ መሆናቸውን የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል ከዚያን ጊዜ አንስቶ ጀርመንና ፈረንሳይ አውሮጳ ውስጥ የሚከሰቱ ቀውሶችን መፍታት የሚያስችሉ መሰረቶችን ጥለዋል።አሁንም ሰላማቸውን ለመጠበቅ ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ያሳወቁት
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በኤሌዚው ውል 60ኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ልዩነቶች እንዳሏቸው አልሸሸጉም። ለምሳሌ ጀርመን የአውሮጳ የፀረ ሚሳይል ከለላ ፕሮጀክት አሁንም በሚሰራበት በእስራኤልና በዩናይትድ ስቴትስ ቴክኖሎጂዎች የሚታገዝ እንዲሆን ስትፈልግ ፈረንሳይ ግና ፕሮጀክቱ በአውሮጳውያን ብቻ እንዲከናወን ነው ፍላጎቷ። ጀርመንና ፈረንሳይ የአውሮጳ ኅብረት አንቀሳቃሽ ሞተር የሚባሉ ሀገራት ናቸው ። ሁለቱ ሀገራት 27 አባላት ያሉት የአውሮጳ ኅብረት በሚያስተላልፋቸው ልዩ ልዩ ውሳኔዎች ላይ የላቀ ተጽእኖ አላቸው። ሽቴፋን ዛይደንዶርፍ የሉድቪግስቡርግ የጀርመን ፈረንሳይ ተቋም ምክትል ሃላፊ ይህን ያረጋግጣሉ።
«ካለፈረንሳይና ጀርመን ስምምነት ተግባራዊ የሚሆን ነገር የለም።ሁለት የተለያየ አቋም ይዘው ሆኖም የሚያስማማ መንገድ መፈለግ ከቻሉ በአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት በሙሉ ተቀባይነት የሚያገኙና የሚያግባቡ ሃሳቦች ላይ መድረስ ይቻላል። ጥሩ የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ሊሆን የሚችለው አባል ሀገራት ኮሮና ያስከተለባቸውን ተጽእኖ መቋቋም እንዲችሉ ፈረንሳይና ጀርመን ያቀረቡት የእርዳታ አሰጣጥ ሃሳብ በመላ የኅብረቱ አባል ሀገራት ተቀባይነት ማግኘቱ ነው።ይህም ለመጀመሪያ ጊዜ የጋራ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገበት መጠነ ሰፊ የመልሶ ግንባታ እርዳታ ነው። አባላቱ በርካታ እንደመሆናቸው የተለያዩ አቋሞች የሚይዙበት እድል ይፈጠራል። ፈረንሳይና ጀርመን ከበርካታ አባል ሀገራት ጋር ኅብረት የመፍጠር እድል አላቸው።በስተመጨረሻ ይህ እንዲሳካ ሁለቱ ሀገራት መግባባት አለባቸው። ይህ ካልሆነ ምን ዓይነት መግባባት ላይ መድረስ አይቻልም።»
ተንታኞች እንደሚሉት ምንም እንኳን ፈረንሳይና ጀርመን የአውሮጳ ኅብረትን አንድነት በማጠናከርና አባል ሀገራትም አግባቢ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ በማድረግ የሚጫወቱት ሚና የላቀ ቢሆንም የዩክሬኑ ጦርነት የተለያየ ስልት የሚከተሉ መሆናቸውን አጋልጧል። ሁለቱ ሀገራት ጦርነቱ በአውሮጳ ያስከተለው የኃይል ቀውስ ለመፍታትና የወደፊቱን የአውሮጳ የጋራ መከላከያ በሚመለከት የተለያየ አቋም ማራመዳቸው በዚህ ረገድ ይጠቀሳል። ዛይደንዶርፍ የችግሩን መነሻ ወደ ኃላ መለስ ብለው በመመልከት መፍትሄ ያሉትንም ጠቁመዋል።
«የዩክሬኑ ጦርነት እስካሁን ያልተነገሩ ውዝግቦችን ወይም መፍትሄ ያልተገኘላቸውን የትብብር መስኮች በጣም ግልጽ አድርጎዋቸዋል። ጉዳዮቹ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ መሆናቸውንም አመልክቷል። በዚህ ረገድ የኃይል ፖሊሲ ጥሩ ምሳሌ ነው።ሁለቱ ሀገራት ከ15 ዓመት አንስቶ በዚህ ረገድ የተለያየ መንገድ መከተላቸው ችግሩ ከሩስያ የጋዝ አቅርቦት እጥረት ጋር ብቻ የተያያዘ የሚሆን አይመስልም። አሁን እንደ አውሮጳ ኅብረት አውሮጳዊ መፍትሄ በአስቸኳይ መፈለግ ይገባል።ምክንያቱም ሁለታችንም የችግሩ ሰለባዎች ነን። የጀርመን ኤኮኖሚ ችግር ውስጥ ከወደቀ ለመላው የአውሮጳ ኅብረት አስቸጋሪና መጥፎ ነው የሚሆነው።በአንጻሩ የፈረንሳይ የኒዩክልየር ኃይል ማመንጫዎች በቂ የኤሌክትሪክ ኤይል ማመንጨት ካልቻሉ፣ይህ እርስ በርስ ለተተሳሰረው ለመላው አውሮጳ አደጋ ነው።በዚህ ላይ መተባበርና አብሮ መስራትን የግድ ይላል።ሁለቱም በዚህ ረገድ ለ15 ዓመታት የተለያየ መንገድ መከተላቸው አለመተባበራቸው በርግጥም ብዙ ጊዜ የቆየ ጉዳይ ነው። »
ሁለቱ ሀገራት የተለያየ አቋም የያዙባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም ሾልዝ በኤሊዜው ውል 60ኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ እንደተናገሩት ወደፊት የሚያተኩሩት በነርሱ አቅጣጫ አስፈላጊ በሚሏቸው ጉዳዮች ላይ ነው የሚሆነው።
«ዓለማችን በቅርቡ የ10 ቢሊዮን ህዝብ መኖሪያ ትሆናለች። በርካታ ተጽእኖ አድራጊ ሀገራትም ይኖሯታል። ዓለማችን የተለያየ ጽንፍ የያዙ ሀገራትም የሚገኙባት ትሆናለች። እና እንደ አውሮጳውያን እንደ ፈረንሳይ እና እንደ ጀርመን ተጽእኖ ልናሳርፍ የምንችለው ለኛ በዓለማችን እኛ በምንከተለው አቅጣጫ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ነው።ይህ ደግሞ 60 ዓመት ከሆነው የኤሊዜ ውል የመነጨ ተልዕኮም ጭምር ነው።»
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ