የሐምሌ 15 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ሐምሌ 15 2016ኢትዮጵያውያን አንጋፋ አትሌቶች የ21ኛው ክፍለ ዘመን ምርጥ አትሌቶች በሚል ስማቸው በዓለም መድረክ ጎልቶ ተጠርቷል ። የፓሪስ ኦሎምፒክ ሊጀመር አራት ቀናት ብቻ ቀርተውታል ። የፈረንሣይ ፕሬዚደንት ኤማኑኤል ማክሮ የኦሎምፒክ መንደሩን ዛሬ በስፍራው ተገኝተው ጎብኝተዋል ። ከፀጥታ ጥበቃው አንስቶ ፓሪስ ዛሬ ምን ትመስላለች? ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ። የሀገር ውስጥ ቡድኖች የእግር ኳስ የፍጻሜው ውድድር ውጤቶችን አካተናል ። በሴቶች ሱፐር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ፦ ቸልሲ አስቶን ቪላን ያስተናግዳል ።
አትሌቲክስ፦
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ምርጥ አፍሪቃዊ ስፖርተኛ ተባለ ። ስለ ስፖርት የሚዘግበው የአሜሪካው ቴሌቪዥን (ESPN) የ21ኛው ክፍለ ዘመን ምርጥ 10 ታላላቅ አፍሪቃውያን ስፖርተኞችን ይፋ ሲያደርግ፦ ኢትዮጵያ እና ኬኒያ ሁለት አትሌቶችን በማስመረጥ ቀዳሚውን ደረጃ ይዘዋል ። በምርጫው ኢትዮጵያዊው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ቀዳሚውን ደርጃ ይዟል ። ኬንያዊው የረጅም ርቀት ሯጭ ኤሉድ ኪፕቾጌ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል ።
በሴቶች ዘርፍ የዚምቧብዌ የዋና ስፖርተኛዋ ክርስቲ ኮቨንትሪ አንደኛ ሆና ተመርጣለች ። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች ። በሁለቱም ጾታ በተደረገው ምርጫ ደግሞ ጥሩነሽ የአምስተኛ ደረጃ ማግኘት ችላለች።
በወንድ አትሌቶች ምርጫ የሁለተኛ ደረጃ ያገኘው ኬንያዊው አትሌት ኤሉድ ኪፕቾጌ በዘንድሮ የፓሪስ ኦሎምፒክ ድል አስመዝግቦ በዓለም የማራቶን ሩጫ ታሪክ ስሙን ለማስፈር ቆርጦ ተነስቷል ። ገና አፍላ ወጣት ሳለ በአውሮፕላን ለመሳፈር እና አውሮፓን ለማየት ሲል ሩጫ መጀመሩን የገለጠው ኤሉድ ኪፕቾጌ፦ ከሁለት ዐሥርተ ዓመታት ወዲህ አዲስ ታሪክ ለማስመዝገብ ጫፍ ደርሷል ።
ኬኒያዊው የ39 ዓመት ሯጭ በፓሪስ ኦሎምፒክ ውድድር በማራቶን ፉክክር ድል ከቀናው በዓለም የማራቶን ታሪክ ሦስት ጊዜ በማሸነፍ አዲስ ክብረ ወሰን ይሰበራል ። በማራቶን ታሪክ ለሁለት ጊዜያት በማሸነፍ በታሪክ ድርሳን ስማቸው የተመዘገቡት፦ ዘመን የማይሽረው ኢትዮጵያዊው አትሌት አበበ ቢቂላ (1960, 1964) እና ጀርመናዊው አትሌት ቫልደማር ሲይርፒንስኪ (1976, 1980) ናቸው ።
የሚደንቀው ነገር የያኔው የ18 ዓመት ወጣት አትሌት ኤሊውድ ኪፕቾጌ ከ21 ዓመት በፊት በዓለም አቀፍ መድረክ ለድል የበቃው በፓሪስ ከተማ መሆኑ ነው ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2003 ኤሊውድ በ5,000 ሜትር ሲጠበቁ የነበሩትን አትሌት ቀነኒሳ በቀለን እና የሞሮኮው ሒሻም ኤል ጌሮዪን ቀድሞ ለድል የበቃው ፓሪስ ውስጥ ነበር ። ኤሊዩድ ኪፕቾጌ በስቴዲየም ውስጥ ካስገኘው ከዚህ ታላቅ ድል በኋላ ግን ፊቱን ያዞረው በጎዳና ላይ ውድድሮች ነበር ።
ለሁለት ጊዜያት የማራቶን ክብረወሰን በመሥበር አሸንፏል ። በ2018 እና በ2022 ። በመጀመሪያው ድል የገባበት ሰአት 2:01:39 ሲሆን፤ በሁለተኛው ደግሞ 30 ሰከንድ አሻሽሎ በ2:01:09 ውድድሩን ማጠናቀቅ ችሏል ። ምንም እንኳን ይፋዊ ውድድር ተብሎ ባይመዘገብም በቪዬና ውድድር እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2019 ባደረገው የማራቶን ፉክክር ከ2 ሰአት ያነሰ ጊዜ በማስመዝገብም በስሙ አዲስ ታሪክ ጽፏል ። በወቅቱ ውድድር ልዩ የመስፈንጠሪያ ጫማ እና አልባሳት ጥቅም ላይ ውሎ ነበር ።
ላለፉት 11 ዓመታት በይፋ ባደረጋቸው 20 ውድድሮች በ16ቱ በማሸነፍ ኤሊውድ ኪፕቾጌ ድንቅ አትሌት መሆኑን ዐሳይቷል ። በነዚያ ጊዜያቶች ውስጥም 11 ውድድሮችን ያሸነፈው በታላላቅ የውድድር መድረኮች ላይ ነው ። አምስት ጊዜ የቤርሊን፤ አራት ጊዜ የለንደን፤ አንድ አንድ ጊዜ ደግሞ የቶኪዮ እና ቺካጎ ማራቶን ፉክክሮች ላይ ለድል መብቃትም ችሏል ፤ ኤሊውድ ኪፕቾጌ ። ዘንድሮ ሕልሙ ተሳክቶለት በማራቶኑ ዘርፍ በዓለማችን አዲስ ታሪክ ያስመዘግብ ይሆን? በቅርቡ የሚታይ ይሆናል ።
ሊጀመር አራት ቀናት በቀሩት የፓሪስ ኦሎምፒክ የከተማዪቱ ጥበቃ ተጠናክሯል፤ ድባቡም ከወዲሁ ለየት ብሏል ። ከዐሥር ሺህ በላይ አትሌቶች ማረፊያ እንዲሆን ተብሎ በሰሜናዊ ፓሪስ አቅጣጫ የተገነባው የፓሪስ ኦሎምፒክ መንደር የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ኤማኑዌል ማክሮ በተገኙበት ተመርቆ ተከፍቷል ። በርካታ ሀገር ጎብኚዎች የሚመላለሱበት እና የመክፈቻ ስነስርዓቱ የሚደረግበት ቦታ ረጭ ብሏል ። በርካታ ጀልባዎች ይንቀሳቀሱበት የነበረው የወንዙ ክፍል እንቅስቃሴ ቀንሷል፤ የመገበያያ ስፍራዎች፤ ምግብ ቤቶች እንዲሁም ተቋማት ተዘግተዋል ። ጥበቃው ከወዲሁ እጅግ ተጠናክሯል ። የፓሪስ ወኪላችን ሐይማኖት ሁኔታውን ከቦታው ተከታትላለች ።
እግር ኳስ
የኢትዮጵያ ክልሎች የእግር ኳስ ቡድኖች የወንዶች ውድድር በትናንትናው ዕለት በጉባ ከተማ አሸናፊነት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዐሳውቋል ። 40 ቡድኖች ተሳታፊ የነበሩበት ውድድር ከሰኔ 22 ቀን፣ ጀምሮ የተካሄደው በድሬዳዋ ከተማ አዘጋጅነት ነው ። በድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም በተካሄደው የዋንጫ ጨዋታ ጉባ ከተማ አቶቲ ገደብ ሀሳሳን 2-0 ያሸነፈው በደሞቻ ጎዮ እና ታምራት አበራ ግቦች ነው ። ለሦስተኛ ደረጃ በተደረገው የመዝጊያ ጨዋታ፦ ጣና ክ/ከተማ መንጌ ቤላሻንጉልን 2-1 አሸንፏል ።
በሴቶች የሱፐር ሊግ ሻምፒዮንስ እግር ኳስ ውድድር ለሰባት ጊዜያት ዋንጫ ያነሳው የቸልሲ ቡድን በዘንድሮ የመክፈቻ ውድድር አስቶን ቪላን እንደሚያስተናግድ ታወቀ ። ከሁለት ወራት በኋላ በሚጀምረው የሴቶች ሱፐር ሊግ ውድድር፦ አርሰናል ከማንቸስተር ሲቲ፤ ብራይተን ከኤቨርተን፤ ሊቨርፑል ከላይስተር ሲቲ፤ ማንቸስተር ዩናይትድ ከዌስትሀም ዩናይትድ እንዲሁም ቶትንሀም ከክሪስታል ፓላስ ጋ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎችም የሚጠበቁ ናቸው ። የሴቶች እግር ኳስ ፉክክር አውሮጳ ውስጥ እጅግ በርካታ ተመልካቾች ያሉት ሲሆን በአዝናኝነቱም ይታወቃል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ