ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው ለመመለስ ውይይት
ረቡዕ፣ ጥቅምት 14 2016ባለፉት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች በተከሰተው ግጭት የተነሳ የተፈናቀሉትን ወደ ቀዬያቸው ለመመለስ በሚያስችል ሁኔታ ላይ የአማራ እና ኦሮሚያ ክልል አመራር መስማማታቸው ተገለጸ ። የሁለቱ ክልሎች የፀጥታ ዘርፍ እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ ተወያይተዋል ። በውይይታቸውም፦ በተለይም በተለያዩ ጊዜያት በተቀሰቀሱ ቅጭቶች ከቀየያቸው ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል የሸሹ የአማራ ተወላጆች ወደ ቀዬያቸው ተመልሰው መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲመሩ አቅጣጫ መቀመጡ ተነግሯል ።
ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተባባሰው አለመረጋጋት እና ግጭት የተነሳ በተለያዩ አከባቢዎች መጠነ ሰፊ የዜጎች መፈናቀል መስተዋሉ ይታወቃል። በተለይም በክልሉ በስፋት የተስተዋለውን ግችት ሸሽተው አማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ የአማራ ብሔር ተወላጆች በተደጋጋሚ በሚያቀርቡት የድጋፍ አቅርቦት እጥረት እንደሚፈተኑ በመግለጽ ወደ ቀዬያቸው በመመለስ መደበኛ ሕይወታቸውን መምራ እንደሚፈልጉም ያነሳሉ።
«መንግስት በመኪና አሳፍሮ ወደ ቀዬያችን ቢመልሰን ደስታችን ነው» ያሉ አንድ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ተፈናቅለው አሁን አማራ ክልል ተሰደው የሚገኙ ተፈናቃይአስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ ሲሰጡ ከተናገሩት ነው።
ይህን ለተፈናቃዮች እሮሮ መፍትሄ ይሰጣል በሚል በትናንትናው እለት ከኦሮሚያ እና ከአማራ ክልል የተውጣጡ አመራሮች በክልሉ በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉትን ዜጎች ወደ ቀዬያቸው በመመለስ በዘላቂነት ማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡ የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች በውይይታቸው ወቅት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከፍተኛ ቁርጠኝነት መኖሩንም ነው ያነሱት፡፡
በውይይቱ ላይ ከታደሙት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ ይገኛሉ፡፡ ኃላፊ በውይይቱ ላይ ስለተነሱት አበይት ሃሳቦችና ትኩረቱን በማስመልከት ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ማብራሪያ በውይይቱ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ዜጎችን ያፈናቀለው ተግዳሮት ተቀርፎ ወደ ቀየያቸውም እንዲመለሱ በሚያስችል አግባብ ላይ መክረው ከስምምነትም ደርሰዋል ነው ያሉት፡፡
"ተፈናቃዮች የተፈናቀሉት ከኦሮሚያ ክልል ነው፡፡ የተፈናቀሉት ሕዝቦች ደግሞ አማራም ኦሮሞም ናቸው፡፡ አፈናቃዮቹ ጽንፈኛው ፋኖ እና ሸነ ናቸው፡፡ ይህ ተግባር የሁለቱን ክልል ህዝቦች እና አመራሮችን የማይወክል ነው፡፡ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች የአከባቢው ሰላም ሲረጋገጥ ተፈናቃዮች ወደ ቄየያቸው እንዲመለሱበሚል ነው ሲሰሩ የቆዩትና በትናንትናውም የስራ ማስጀመሪያ ውይይት ወደ ከተሞች የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችና ወደ አማራ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ ነው ስምምነት የተደረገው” ብለዋል፡፡
ኮሚሽነር አራርሳ በግጭቱ ምክኒያት ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ተፈናቃዮች ብዛት ተጠይቀው አመራሮቹ በውይይታቸው የተፈናቃዮች ቁጥር በአማራ ክልል በኩል ተጣርቶ እንዲቀርብ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡ ዶይቼ ቬለ በአማራ ክልል በኩል አስተያየት ለማካተት ለክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋሁን ባታብል፣ ለክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው እንዲሁም ለክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መንገሻ ፈንታው ብደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡
የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ በሰጡን ተጨማሪ ማብራሪያ ግን የሁለቱ ክልሎች አመራሮች በውይይታቸው ተፈናቃዮቹን ወደ ቀዬያቸው ከመመለስም ባሻገር በተፈናቃይ ማህበረሰቡ መካከል ውይይት እንዲደረግና ሰላም እንዲወርድ ብሎም ተፈናቃዮች ስለሚቋቋሙበት ርዳታ ከወዲሁ መታሰቡን አስረድተውናል፡፡
"በህዝብ ደረጃ ህዝብ ለህዝብ ምንም ችግር የለውም ከዚህ በፊትም ውይይት ተደርጓል፡፡ ሁለቱን ህዝብ የወከሉ በማስመሰል ሰላም የሚያዉኩ ጽንፈኞች ህዝብን እንደማይወክሉ የሚደረግ ውይይትም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በአመራር ደረጃ የተጀመረው ውይይት ወደ ህዝብም ይወርዳል፤ በዚያ መካከል ወንጀል የሰራ አካልም ተጠያቂ ይሆናል፡፡ የወደሙ መሰረተ ልማቶች በኦሮሚያ ክልል መንግስት እንዲጠገኑና የወደሙ የግለሰቦች ቤትና ንብረቶች የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ህዝብን አስተባብረው እንዲጠገን ነው የተስማማን፡፡”
በምዕራብ ኦሮሚያ በተለይም በምስራቅ ወለጋ የተረጋጋ አንጻራዊ የሰላም ይዞታ መኖሩንና በተወሰነ መልኩ ተፈናቃዮችንወደ ነባር ቄያቸው የመመለስ ሥራ መጀመሩን ዶይቼ ቬለ ባለፈው ሳምንት የአከባቢው ተፈናቃዮችና የምስራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ገመዳ ተፈራን ዋቢ አድርጎ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ