የቄለም ወለጋ-ሃዋ ገላን ዞን ተፈናቃዮች ጥሪ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 5 2014በኦሮሚያ ክልል ቀሌም ወለጋ ዞን ሃዋ ገላን ለምለም ቀበሌ ከባለፈው ሳምንት የጅምላ ጭፍጨፋ ጥቃት የተረፉ ዜጎች ከወደመው ቀዬያቸው በመፈናቀላቸው ለተደለያዩ ጉዳት መዳረጋቸውን ገለጹ፡፡
ነዋሪዎቹ መንግስት ለጊዜው አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ከማቅረብ ባሻገር ለዘለቄታዊ ደህንነታቸው ዋስትና የሚሆን ሁኔታን እንዲያመቻችላቸው ነው የጠየቁት፡፡ እንደ ነዋሪዎቹ አስተያየት መቻራ በተባለች ከተማ ተፈናቅለው የሚገኙ ተፈናቃዮች እስካሁን የእለት ድጋፍ እየተደረገላቸው ያለው በአከባቢው ማህበረሰብ ብቻ ነው፡፡ 24 ሺህ ነዋሪዎች በቀሌም ወለጋው ሃዋ ገላን ወረዳው ጥቃት መፈናቀላቸውን የሚገልጸው የኦሮሚያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር (ቡሳ ጎኖፋ) በበኩሉ፤ የአከባቢው የፀጥታ ስጋት የእርዳታ ማጓጓዝ ሂደቱን እንዳይቀላጠፍ እንቅፋት መሆኑን ገልጾ፤ 11 የተለያዩ የድጋፍ ቁሳቁሶችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደዚያው እያመሩ ነው ብሏል፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ ተናግረው አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ ያጋሩት አንድ ከጥቃቱ የተረፉ የአከባቢው ነዋሪ እንደሚሉት ግድያውን ተከትሎ አከባቢው ላይ የደረሰው መከላከያ ሰራዊት አከባቢውን በማረጋጋት ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው ብመልስም፤ ከቅዳሜ ጀምሮ የመከላከያ ከአከባቢው መውጣትና በሌሎች የፀጥታ ኃላት መተካት ህብረተሰቡን ጥርጣሪ ውስጥ ከተውታል፡፡
በዚህም ያንን ተከትሎ “መቻራ ወደ ተባለች ከተማ የተፈናቀሉ የማህበረሰብ አካላት ቁጥራቸው በሺዎች ይቆጠራል” ይላሉ እኚው አስተያየት ሰጪ፡፡ እስካሁን ለማህበረሰቡ የደረሰ ድጋፍ እንደሌለም የሚናገሩት ነዋሪው የአከባቢው ማህበረሰብ እስካሁን ተፈናቃዮችን የመመገብ ኃላፊነቱን ወስዶ እንደሚገኝ ነው ያብራሩት፡፡
ወደ ሦስት አራት ቀበሌያት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል የሚሉት ሌላው የአከባቢው ነዋሪ በአስተያየታቸው፤ የባለፈው ሳምንት ሰኞ ጥቃቱ በሃዋ ገላን ወረዳ ለምለም ቀበሌ መንደር 20 እና መንድር 21 የሚባሉ አከባቢዎች ላይ ያነጣጠረ ቢሆንም ለጥቃቱ ሰለባ ያልነበሩም ሌሎች ቀበሌያት በስጋት እየተፈናቀሉ ወጥተዋል ነው ያሉት፡፡
ባለፈው ሳምንት ሃሙስ እና ዓርብ ተፈናቃዮች ከተፈናቀሉበት ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ ባለስልጣናት ተማጽነው እንደነበር የገለጹት ነዋሪው፤ መከላከያ ቅዳሜ እለት አከባቢውን ለቆ ወደ ደምቢዶሎ መውጣቱን ተከትሎ እንደገና ወደ መቻራ ተመልሰዋል ነው ያሉት፡፡ እኚም ነዋሪ እንዳሉት እስካሁን በአከባቢው የደረሰ በመንግስት በኩል የመጣ ድጋፍ ባለመኖሩ ሁሉም የአከባቢው ማህበረሰብ ለተፈናቃዮች ድጋፍ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡ የፌዴራል መንግስት አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ እንደሚሉት በኦሮሚያ ምእራብ ወለጋ እና ቀለም ወለጋ በቅርቡ የተከሰተውን ሰው ሰራሽ አደጋ ተከትሎ በርካታ የምግብ እና ምግብ ነክ ቁሳቁሶች ወደ ኦሮሚ ክልል መላካቸውን አመልክተዋል፡፡ እንደ አቶ ደበበ ማብራሪያ በቅርብ ጊዜያት ብቻ ወደ 2 ሺህ 572 ሜትሪክ ቶን የእርዳታ ቁሳቁሶች ወደ ኦሮሚያ ተልከዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ሙስጠፋ ከድር በበኩላቸው፤ ክልሉ በቅርቡ በምዕራብ ወለጋ እና ቀሌም ወለጋ ዞኖች ያጋጠሙትን የጅምላ ግድያ ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ የማህበረሰብ አካላትን ለመደገፍ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ ከምእራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በሰኔ 11ዱ ጥቃት የተፈናቀሎ 5000 ሰዎች ገደማ በአርጆ ጉደታ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው፡፡
በሌላ በኩል በቀሌም ወለጋው የሰኔ 27ቱ ጥቃት የተፈናቀሉትን 24 ሺህ ገደማ ዜጎች ለመርዳት የሚውል የተለያዩ ቁሳቁሶችን የጫኑ 11 ሺህ ተሽከርካሪዎች ወደ ስፍራው እያቀኑ ነው ብለዋል፡፡ በመንገድ ላይ ያለው የጸጥታ ስጋት መጠነኛ መዘግየት መፍጠሩንም በማመልከት በቂ ያሉት የምግብና ሌሎች የመጀመሪያ ደረጃ የድጋፍ ቁሳቁሶች እየደረሱ ነው ብለዋልም፡፡
በጥቃቱ የተፈናቀሉ ዜጎች ግን ስጋታቸው ከእርዳታ ቁሳቁሶች በላይም መሆኑን ያነሳሉ፡፡ አስተያየታቸውን ከሰጡን ተፈናቃዮች አንደኛው እንደሚሉት፤ መንግስት በአከባቢው የጥቃት ሰለባ የሆኑትን ዜጎች በማስታጠቅ ወግ ማዕረግ ወዳዩበት ቀዬያቸው ሊመለ፤ሳቸው ይገባል፡፡ ሌላኛው ተፈናቃይ በበኩላቸው ምንም ተስፋ የማይታይበት ካሉት አከባቢ ተነስተው እስከነልጆቻው አገራቸው ወዳሉት መልሱን ሲሉ ተስፋ በሙቁረጥ ስሜት አማራጭ ያሉት ሃሳብ አጋርተውናል፡፡
በርካታ የአከባቢው ነዋሪዎች ያላቸውን በእርካሽም እየሸጡ መሰደድን አማራጭ ያደረጉ እንዳሉም ነዋሪዎቹ አክለው አብራርተዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ሙስጠፋ ከድር ግን የጸጥታ ሁኔታውን አስተማማኝ በማድረግ የወደመውን የነዋሪዎች ንብረትም በመጠገን በዘላቂነት የሚቋቋሙበት አማራች ላይ መንግስት እየሰራ ይገኛል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ