1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ የሚገቡ የሱዳን ስደተኞች

ሐሙስ፣ ግንቦት 10 2015

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) ባወጣው ዘገባው ከ25ሺ በላይ ሰዎች ከሱዳን በ3 ክልሎች በኩል ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን አመልክተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ከ6ሺ በላይ ሰዎች የሚሆኑት በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ አል-ማሀል በተባለ ስፍራ እና በአሶሳ ዞን ኩርሙክ ወረዳ የገቡ ናቸው፡

https://p.dw.com/p/4RXeg
Sudan Flüchtlingswelle
ምስል Gueipeur Denis Sassou/AFP

25 ሺሕ የሱዳን ስደተኞችና ኢትዮጵያዉያን ኢትዮጵያ ገብተዋል-ኦቻ

 የሱዳንን ጦርነት ሽሽት ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር መጨመሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታዉቋል።የድርጅቱ የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) እንዳስታወቀዉ ከ25 ሺሕ የሚበልጡ የሱዳን ስደተኞች በሶስት አዋሳኝ ክልሎች በኩል ኢትዮጵያ ገብተዋል።የበኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እንዳስታወቀዉ ደግሞ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት ሱዳናዉያን ብቻ ሳይሆኑ ሱዳን የነበሩ ኢትዮጵያዉያን ጭምር ናቸዉ።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) ባወጣው ዘገባው ከ25ሺ በላይ ሰዎች ከሱዳን በ3 ክልሎች በኩል ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን አመልክተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ከ6ሺ በላይ ሰዎች የሚሆኑት በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ አል-ማሀል በተባለ ስፍራ እና በአሶሳ ዞን ኩርሙክ ወረዳ የገቡ ናቸው፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ታሲሳ 17ሺ የሚደርሱ ሰዎች ከሱዳን ወደ ክልሉ ሊሻገሩ ይችላሉ በሚል ግምት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ከትናንት በስቲያ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሰዎች ተጨባጭ ቁጥርና ዜግነት ለጊዜው እንዳላረጋገጡ ጠቁመዋል፡፡ ወደ ክልሉ የሚገቡ ሰዎችን ለመከታተል ከተለያዩ ተቋማት የተዋቀረ  ኮማንድ ፖስት ማቋቋማቸውን መቋቋሙን አቶ ታረቀኝ ተናግረዋል፡፡

የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ተቋም በበኩሉ በመተማ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ  እና ጋምቤላ ክልል ያለውን ሁኔታ በማጥናት የቅድመ ምዝገባ ጣቢያዎችን ማቋቋሙን ገልጸዋል፡ሱዳን፣ ሁሉም የሚሻት አንዱም ያልጠቀማት ሀገር፡ የአገልግሎ የኮሙኒኬሽን እና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ በአካል ንጉሴ ለዶቼቨለ እንደተናገሩት እስካሁን ወደ 3ሺ 4መቶ የሚደርሱ ሰዎች ጥገኝነት መጠየቃቸውን አብራርተዋል፡፡ ጥገኝነት ለጠየቁ ሰዎች ጥበቃ እና ከለላ ይደረጋል ያሉት ኃላፊው ለጥገኝነት ጠያቂዎች አስፈላጊውን መሠረታዊ ድጋፍ  ለማድረግ እንዲቻል ከዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ  ከፍተኛ ድጋፍ ያስፍልጋል ብለዋል፡፡

የሱዳን ስደተኞች አዉላላ ሜዳ ላይ
የሱዳን ስደተኞች አዉላላ ሜዳ ላይ ምስል Mahamat Ramadane/REUTERS

የመተከል ዞን አስተዳደር  በ3 በሮች በኩል ወደ ዞኑ ሰዎች መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ለሜሳ ዋቅወያ በአል-መሀል በኩል የገቡ ከዚህ ቀደም ወደ ሱዳን ተፈናቅለው የነበሩ ኢትዮጵያዊን መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ በጠርፍ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ሊሻገሩ እንደሚችሉ የገለጹ ሲሆን ከሱዳን ጋር በሚያናኙ አልመሀልና ሌሎች 2 ቀበሌዎች የገቡ የሰዎች ምዘገባ አለመጠናቀቁን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አብራርተዋል፡፡

ከአንድ ወር በላይ በሆነው የሱዳን  ጦርት ምክንያት 843ሺ ዜጎቿ በሀገር ውስጥ ሲፈናቀሉ 259ሺ የሚደርሱት ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገራት መሰደዳቸውን የዓለም ዓቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ይፋ አድርጓል፡፡

 ነጋሳ ደሳለኝ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ