ሱዳን፣ ሁሉም የሚሻት አንዱም ያልጠቀማት ሀገር
ሰኞ፣ ሚያዝያ 16 2015
ዉኃ የሚጠማት ግብፅን ዉኃ ከሚፈልቅባት ግን ከማትጠቀምበት ኢትዮጵያ ጋር አማክላ በሁለቱ የኃይል ስበት ሰሜን-ደቡብ ትረግጣለች።ሱዳን።ከ2011 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀምሮ በአመፅና በኔቶ ጦር ወረራ ከሐብታም፣ሰላማዊ፣ስልታዊ ሐገርነት ወደ ጎጥ ታጣቂዎች መፈንጫነት የዘቀጠችዉን ሊቢያን፤ በአማፂን ዉጊያ የመሪዋን ሕይወት ሳይቀር የገበረችዉን ቻድን፣ በርስ በርስ ጦርነት የምትተራመሰዉ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክን፣ ካንድ መሪ ሌላ ፓርላማ፣ሕገ-መንግስት፣ ነፃ ፕረስ ዝር የማይልባት ኤርትራን፣በነፃነት ማግስት በርስበርስ ጦርነት የወደመችዉን ደቡብ ሱዳንን ታዋስናለች።አረብነትን ካፍሪቃዊነት የቀየጠች፣ማዕድንን ከእርሻ መሬት ያሰባጠረች -ሰፊ፣ቀይ ባሕርን የተንተራሰች በሐብታም-ኃያላን ተፈላጊ-ስልስታዊ ሐገር ናት።ፈላጊዋ በዝቶ፣ብልሕ አሳዳሪዋ ጥፍቶ-በጅል ገዢዎችዋ እብሪት እየጣፋች ነዉ።ሁለተኛ ሳምንቷ።ላፍታ እንዴት ለምን እንላለን አብራችሁን ቆዩ።
የኢትዮጵያን ኮሚንስታዊ ወታደራዊ መንግስት በጋራ ወግተዉ ከስልጣን ያስወገዱት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) እና የቀድሞዉ የኤርትራ ሕዝብ ነፃ አዉጪ ግንባር (EPLF) ወይም ሻዕቢያ አዲስ አበባና አስመራ ላይ ሁለት መንግስታት በመሰረቱ በ7ኛ ዓመታቸዉ ዉጊያ መግጠማቸዉ ለብዙዎች ያልተጠበቀ፣ አስገራሚ ላንዳዶች አስደንጋጭም ነበር።
በሁለቱ ኃይላት ግፊት ስልጣናቸዉን ለቅቀዉ የተሰደዱት የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ግን ሁለቱ ጠላቶቻቸዉ ስለገጠሙት ዉጊያ ሲጠየቁ «ሌባ ድሮስ ሲካፈል እንጂ ሲሰርቅ መች ይጣላል» ማለታቸዉን ብዙዎች ይጠቅሳሉ።
ካርቱም ወሕኒ የሚገኙት የቀድሞዉ የሱዳን ፕሬዝደንት ብርጌድየር ጄኔራል ዑመር ሐሰን አል በሽር ሁለቱ የቀድሞ አገልጋዮቻቸዉ የሚያዟቸዉ ኃይላት ስለገጠሙት ዉጊያ ያሉት ካለ የነገረን የለም።ኢትዮጵያዊዉ የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ሙከረም ሚፍታሕ እንደሚሉት ግን አልበሽርን ለዓመታት በታማኝነት እኩል ሲያገለግሉ ኖረዉ፣ በ2019 አልበሽርን እኩል ከድተዉ፣ ከስልጣን አስወግደዉ እኩል ሥልጣን የያዙት ጄኔራሎች የሚያዟቸዉ ወታደሮች የገጠሙት ዉጊያ በሱዳን የቅርብ ጊዜ ታሪክ አዲስ ነዉ።
አዲሱን ዓይነት ዉጊያ ያቀጣጠለዉ የመጨረሻዉ ጠብ ብዙዎች እንደሚሉት ፈጥኖ ደራሹ ጦር ከመደበኛዉ ሠራዊት ጋር የሚቀየጥበት ጊዜ ነዉ።የወታደራዊ ሁንታዉ መሪ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐንና የሚመሩት ቡድን ፈጥኖ ደራሹ ጦር በሁለት ዓመታት ዉስጥ ከመደበኛዉ ሠራዊት ጋር መቀየጥ አለበት ባይ ነበሩ።
የፈጥኖ ደራሹ ጦር አዛዥ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሐምዲቲ) ግን በዶክተር ሙከረም አገላለፅ «ዓየር ላይ ተንጠልጥለዉ እንዳይቀሩ» ዉሐደቱ በ10 ዓመት ዉስጥ መከናወን ይገባዋል ባይ ናቸዉ።የሁለቱ ጄኔራሎች ጠብ ቃታ ያስብ እንጂ የሱዳን የሲቢል ፖለቲከኞች፣ የተለያዩ የሲቢል ማሕበራት ልዩነትና ልዩነቱ ያስከተለዉ ጫና ጠቡን ማጋጋሙ አልቀረም።
ሱዳን በርግጥ ለዉጊያ ጦርነት እንግዳ አይደለች።የደቡብ ሱዳን ጦርነት፣የዳርፉር ጦርነት፣የኮርዶፋን ጦርነት፣ የብሉ ናይል ግዛት ጦርነት፣ ሁሉም ጦርነቶች በአማፂያንና በመንግስት ወይም በአማፂያን መካከል የተደረጉ ከትላልቅ ከተሞች በብዙ ኪሎሜትሮች በራቁ አካባቢዎች ነበሩ።
ያሁኑ ግን ርዕሰ-ከተማ ካርቱምን ነዉ-የሚያነደዉ።አዉሮፕላን ጣቢያዎችን፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን፣የንግድ ተቋማትን፣ ሐኪም ቤቶችን እያወደመ ነዉ።10ኛ ቀኑ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደቆጠረዉ ሐኪሞች፣የርዳታ ድርጅት ሰራተኞች፣ ኢትዮጵያዉያንን ጨምሮ የተለያዩ ሐገራት ዜጎች ተገድለዋል።ድምር 427 ሰላማዊ ሰዎች።
በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ቆስለዋል።መድሐኒት፣የሕክምና መሳሪያ፣ የምግብ ሸቀጥ፣የንፅሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ እየተሟጠጠ ነዉ።መብራት የለም።ከ20 ሺሕ የሚበልጥ ሕዝብ ቻድ፣10 ሺሕ የሚሆን ደግሞ ደቡብ ሱዳን ገብቷል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ደግሞ ኢትዮጵያና ግብፅ ደንበር ላይ መኮልኮላቸዉ ተዘግቧል።
ሱዳን ዉስጥ አንድ ሚሊዮን ዜጎች እንዳሏት የሚነገረዉ ኢትዮጵያ ዜጎችዋን ለመርዳት ወይም ለማስወጣት ያደረገችና ያሰበችዉ ስለመኖር አለመኖሩ እስካሁን የሚታወቅ ነገር የለም።የአረብ መንግስታት፣ዩናያትድ ስቴትስ፣ብሪታንያ፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣ሩሲያ፣ቻይና፣ጃፓን፣ ሕንድ ኢንዶኔዚያና ሌሎችም ዜጎቻቸዉን እያስወጡ ነዉ።
ሁለቱ ጄኔራሎች ዉጊያዉን እንዲያቆሙ የአረብ ሊግ፣የአፍሪቃ ሕብረት፣ኢጋድ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረት ጠይቀዋል።የሰማ እንጂ የተቀበላቸዉ የለም።
የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት የበላይ ኃላፊ ጆሴፍ ቦርየል ጥሪዉን ዛሬም ደገሙት።
«ከሁሉም ጎረቤቶች፣ከሁሉም ወዳጆቻችን ሌላዉ ቀርቶ ተዋጊዎቹን ኃይላት ከሚያዙት ከሁለቱ ጄኔራሎች ጋር እየተነጋገርኩ ነዉ።የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ መልዕክት ተመሳሳይ ነዉ።ጦርነቱ ማቆም አለባቸሁ።የጠመናጅዉን አፈሙዝ ዝጉና ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመፈለግ ተደራደሩ የሚል ነዉ።ምክንያቱም ለጦርነቱ ወታደራዊ መፍትሔ ሊኖር አይችልም።»
ቦርየል አላበሉም።ይሁንና ዶክተር ሙከረም እንደሚሉት አስገዳጅ ነገር ካልተፈጠረ ወይም ከሁለት አንዳቸዉ የበላይነት ካላገኙ የተኩስ አቁሙ ጥሪዉ ተቀባይነት ይኖራዋል ብሎ ማሰብ ያስስታል።
«ሁለት ኃይሎች አንድ ሐገር ዉስጥ ሲቢል ዋር የሚመስል ነገር ዉስጥ ከገቡ ወደ ዉይይት ወደ መድረክ ሊመጡ የሚችሉበት አንድ አስገዳጅ ነገር ካልተፈጠረ ቁጭ ብለዉ ለመነጋገር አንዱ ኃይል ገንኖ መዉጣት አለበት።ተኩስ አቁሙ ያልተሳካዉ ለዚሕ ይመስለኛል።»
ከሁለት አንደኛዉ አንድ ቀን ያሸንፍ፣ ዉጊያ፣ጦርነቱም ይቆም ይሆናል።እስኪዚያ ግን ምን ያሕል ሰዉ መሞት፣መቁሰል፣ስንት ሕዝብ መሰደድ-መፈናቀል፣ ስንት ሐብት-ንብረት መወደም አለበት ነዉ-ለጊዜዉም ቢሆን መለስ የሌለዉ ጥያቄ።
ጥቅምት 2021 በተደረገዉ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የተወገዱት የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ ባለፈዉ ሳምንት በሰጡት መግለጫ የዉጪ ኃይላት በሱዳን የዉስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ አደራ ብለዋል።
«በሱዳን ጉዳይ ማንኛዉም የዉጪ ኃይል ጣልቃ እንዳይገባ እጠይቃለሁ።ፖለቲካዊዉ ድርድር እንዲቀጥል ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ገንቢ ሚና እንዲጫወት እጠይቃለሁ።»
የሐምዶክ ጥሪ በርግጥ ተገቢ ነዉ።ግን ማን ሊቀበላቸዉ? ግብፅና ቱርክ እንደ ቅኝ ገዢም፣እንደ ጥብቅ ወዳጅም ከሱዳን ርቀዉ አያዉቁም።ግብፅና ኢትዮጵያ እንደ ጎረቤትም፣እንደ ጠላትም እንደ ወዳጅም የካርቱምን ፖለቲካ መዘወር ይሻሉ።ሱዳን አረብም-አፍሪቃም ናት።አረቦች በተለይም እንደ ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ያሉ ሐብታም ነገስታት በህዝብ የተመረጠ መንግስት የካርቱምን ቤተ-መንግስትን እንዲይዝ አይፈልጉም።
አፍሪቃዉያን ከጋዜጣዊ መግለጫ ግፋ ቢል ሰላም አስከባሪ ከማዝመት ባለፍ የሚሹቱን ለማድረግ አቅም የላቸዉም።
ባንድ በኩል የዴሞክራሲያዊ ስርዓትን አስፈላጊነት እየሰበኩ በሌላ በኩል ለግብፅ አምባገነኖችና ለአረብ ነገስታት ዙሪያ መለስ ድጋፍ የሚሰጡት የዋሽግተን፣የለንደን፣ ብራስልስ መንግስታት የካርቱምን ሁለንተናዊ ጉዞ ግራ ቀኝ ያላጉታል።
ቻይናና ሩሲያም ለሸቀጥ ማራገፊያ፣ማዕድን ለመነገጃ ወይም ለጦር ሰፈርነት ሱዳንን ዉስጥ እግራቸዉን መትከል ይፈልጋሉ።እንዲያዉም ዋግነር የተባለዉ የሩሲያ ወታደሮች አከራይ ቡድን የሱዳንን ወቅርቅ ለገበያ እንደሚያቀርብ እየተነገረ ነዉ።
ምዕራባዉያን መንግስታትና የአረብ ተከታዮቻቸዉ የቻይናና የሩሲያን ተፅዕኖ ለማክሸፍ የሱዳኖችን ምኞትና ፍላጎት ደፍልቆ ለነሱ ላደረላቸዉ ገዢ ማዳላታቸዉ መዘዙ በርግጥ አስከፊ ነዉ።የፊላንዱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፔካ ሐቪስቶ የምዕራባዉያኑን ፍላጎት በዲፕሎማሲ ቋንቋ እንኳ ሊሸፋፍኑት አልሞከሩም።
«እርምጃችንን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ከተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ አገልግሎት ጋር ማቀናጀት አለብን።በዚሕ ሁኔታ ሁሉም የዉጪ (ዜጎች) ሐገሪቱን ጥለዉ መዉጣታቸዉ ተገቢ አይደለም።እኛ የሆነ ክፍተት ከተዉን የዋግነር ወታደሮችና ሩሲያ ይህን ጨዋታ እንዲጫወቱ እናደርጋለን።እና እንደሚመስለኝ አዉሮጳ ሱዳን ዉስጥ የራስዋን ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አለበት።»
በቅርቡ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶን) የተቀየጠችዉ ሰሜን አዉሮጳዊቱ ሐገር እስከ 1917 ድረስ የሩሲያ ንጉሳዊ አገዛዝ ግማደ ግዛት ነበረች።ትልቁ ዲፕሎማትዋ ዛሬ እንዳሉት አዉሮጳ ሱዳን ዉስጥ የሚጫወተዉን ሚና መጨመር ያለበትና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር ስራ-እንቅስቃሴዉን የሚያቀናጀዉ ለሱዳን ሰላም ወይም ለሕቧ ፍላጎት ስኬት አይደለም።ሩሲያን ከሱዳን ለማራቅ እንጂ።
የሱዳን የቀድሞ ቅኝ ገዢ ብሪታንያዎች የሱዳኖችን ባሕሪ እንደቀልድም-እንደምርም እያስመሰሉ በሶስት የእንግሊዝኛ ፊደላት በሚወከሉ ሶስት ቃላት ያጠቃልሉታል ይላሉ-የሚያዉቁ።IBM ብለዉ።ኢንሻአላሕ፣ቡክራ፤ ማፊሽ ሙሽኪላ።አላሕ ቢሻዉ።ነገ።ችግር የለም እንደማለት።
ብዙዎች እንደሚመክሩት የሱዳን ልሒቃን «ችግር አለ» ብለዉ ችግሩን ለማስወገድ በጋራ ካልጣሩ የሐምዶክ መግለጫ፣ የጄኔራሎቹ ዉጊያም ሆነ የሲቢል ማሕበራቱ ጩኸት ሐገር-ሕዝባቸዉን ከልቁል ከማስፈንጠር ወይም የሐብታም-ኃያላን መሻኮቻ ከማድረግ ሊያስጥሏቸዉ አይችሉም።
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ