የሚጨሰዉ ጠረጴዛ እና የሥነ-ጥበብ ባለሙያዉ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 22 2016«የሃይማኖት ሰዉ ቄስ አይደለሁም፤ ጋዜጠኛ አይደለሁም፤ የኔ ዓይን ወይም እኔ የምቆምበት ቦታ ሌላ ነዉ። እንዴ ብዬ ራሳችንን እንይ ብዬ ቆም ብዬ አሰኩ። እናንተም እንደምትዘግቡት፤ እኛም እንደምንኖርበት፤ እንደሚታየዉ ሁሉ ቦታ ትርምስ ነዉ፤ በአፍሪቃ ትርምስ ነዉ። በኢትዮጵያ ትርምስ ነዉ። በአንድ በኩል ሥራ ይሰራል፤ በአንድ በኩል ኑሮ ይኖራል። እንደገና እየተባላን እየተገዳደልን በአሰቃቂ ሁኔታ ጣልያን ከነበረበት ጊዜ ያልተለየ ብዙ ነገር አለ። የዚህ ሁሉ መነሻ የቅኝ ግዛት ምንጭ ነዉ። የምዕራብ ሃገራት በርሊን ላይ ተሰብስበዉ ድንግልዋን አፍሪቃ ቁጭ ብለዉ ይቺ ለአንተ ይቺ ለኔ እያሉ እንደ ገና ዳቦ መስመር አስምረዉ፤ ዛሬ የምንኖረዉን ድንበር ሰሩ፤ የኛ የዛሬ ዉዝግብ ምክንያት አንዱ ይህ ነዉ።»
የሥነ-ጥበብ ባለሙያዉ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር በቀለ መኮንንን ከተናገሩት የተወሰደ ነዉ። የሥነ ጥበብ ባለሙያዉ በቀለ መኮንን በሰሜናዊ ኢጣሊያ በቶሪኖ ሮያል ሙዚየም ዉስጥ ሰሞኑን ያቀረቡት የጥበብ ሥራ ከፍተኛ ተደናቂነትን ብሎም አትኩሮትን ስቧል። በቀድሞ የጣልያን ነገስታት መቀመጫ በሆነዉ በቶሪኖ የተንቆጠቆጠ ቤተ-መንግሥት ዉስጥ በተከፈተዉ አዉደ ርዕይ ላይ ያቀረቡት የሚጨሰዉ ጠረጴዛ «The smoking Table» የተሰኘዉ ስራቸዉ፤ የዓዉደ ርዕዩ አስኳል ለመሆን አብቅቶታል። የሥነ ጥበብ ባለሙያዉ በቀለ መኮንን በአፍሪቃ የጣልያን ቅኝ ግዛት ዘመን በስጦታ፤ በዝርፍያ፤ በግዢ ጣልያን እጅ ዉስጥ የገቡት ቁሳቁሶች ለቀረቡበት አዉደ ርዕይ በቂ መልስ የሰጠ የጥበብ ምላሽ ተብሎለታል። በቀለ መኮንን ይህን ሥራ ለማቅረብ ብዙ መጻህፍትን አገላብጠዋል፤ ምሁራንን ጠይቀዋል፤ ከፍተና ጥናትም አካሂደዋል፤ በጣልያን ስራዉን የጀመሩት ከስድስት ወራት በፊት ጀምሮ ነዉ።
የጥበብ ስራዉን ለማቅረብ ለጥበበኛዉ በቀለ መኮንን ከስድስት ወራት በላይ ጥናትን ያላወቅነዉን ታሪኮቻችንን ደግሜ በጥሞና እንድመለከት አስገድዶኛል፤ አስተምሮኛል ይላሉ። ኢጣሊያ በቀድሞ ቅኝ ግዛቶችዋና አዋሳኞቹ ጋር በነበራት መልካምም ይሁን እኩይ ግንኙነት የተገኙ ስዕሎችና ሌሎች ውድ የቅርስ ስብስቦች የሚቀርቡበት ግዙፍ ትርዒት በመሆኑ ለዚህ ስብስብ የዘመነኛ ሥነ-ጥበብ ድምፅ ቢሰማ ቢታይ የሚል ጥያቄ ቀርቦ ስራዬን ለማቅረብ እድል አግኝቻለሁ፤ ጉዳዩ በሥነ-ጥበብ መነፅር በአፍሪቃና በምዕራቡ ዓለም መካከል በነበረው የቅኝ ገዢ ግንኙነት ከነመዘዙ ከጉዳይ አስገብቶ የማሄስን ብልሀት የሚጠይቅ ነበር ሲሉም ባለሞያዉ በቀለ መኮንን ተናግረዋል። የቀ/ኃ/ሥ ኪነ-ቅርፅና ትችቱ
እናም ኢትዮጵያዊዉ ጥበበኛ በቀለ መኮንን በጣልያንዋ ከተማ በቶሪኖ ሮያል ሙዚየም ዐውደ ርዕይ ላይ በአፍሪቃዊ ድምፅነት ያቀረቡት “The smocking table” የሚጨሰዉ ጠረጴዛ የተሰኘዉ የጥበብ ሥራ ፅንሰ አሳቡ መዘዙ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ጨምሮ አፍሪቃን እንዳዲስ በማተራመስ ላይ ስላለው የተዳፈነ የቅኝ ገዢ እሳት የሚያሳይ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ከትርዒቱ ጎን ለጎን የጣልያን ምሁራን፤ ተማሪዎች ጎብኝዎች የሚወያዩባቸው ብዙ ቀጠሮና መድረኮች ቀድመው ተዘጋጅተዋል። እኛ የጉዳዩ ግምባር ቀደም ባለቤቶች፤ ተሰብስበን ለመምከር መች ፋታ እናገኝ ይሆን የሚለዉ ጥያቄ የሥነ-ጥበብ ባለሙያዉ የበቀለ መኮንን ብቻ ግን አይደለም። ባለፈዉ ሳምንት በቶሪኖ ከተማ አዉደርዕይ መክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ የተገኙ አንዳ ጣልያናዊ ጥበበኛዉን በቀለ መኮንን ሆድ አባብተዋል።
የሥነ-ጥበብ ባለሙያዉ በቀለ መኮንን በመክፈቻዉ ሥነስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር “ያለፈን ጥቃትና ግፍ ከልብ ተማምነን እንደ 21 ኛ ክፍለ ዘመን ስልጡን ሰው፤ ለሁላችን የምትበቃዋን ምድር ያለስግብግብነት እና ያለጡንቸኝነት በሰብአዊነት ተሳስበን ብንኖር ለሁላችን መልካም ይሆናል። ይህንኑ እውነት አስረግጦ ለመናገር እነሆ ራሳችሁ በሰጣችሁኝ ዕድል አሳቤን በጥበብ ትርጓሜ አቅርቢያለሁ። ፍቺው እንደተመልካቹ ቢለያይም በበኩሌ ግን በአፍሪቃችን ምድር ቅኝ ገዥዎች በስውር አርቀው የቀበሩት እሳት እነሆ እስከዛሬ በመጨስ ላይ ይገኛል። ጪሱንም ስንገዳደል በደማችን ላይ፣ ስንቸገር ካዝናችን ውስጥ ፣ ደምቆ ይታያል። ከልብ ተነጋግረን ለስህተቱ ይቅርታ፣ ለጥፋቱ ካሳ፣ ለሐጢአቱ ንስሐ በማድረግ ተገባብተን የነገውን አዲስ ቀን ትሩፋት ተጋርተን፣ በሰላም ለመኖር አያቅተንም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ “ ብለዋል። የሥነ-ጥበብ ባለሙያዉ በቀለ መኮንን የጥልያንዋን ቶሪኖ ከተማን ጎብኝተዉ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ ብዙ ቢያጫዉቱን በወደዱ ግን ለዝግጅቱ የተሰጠዉ ሰዓት ገድቦናል።
ተባባሪ ፕሮፌሰር በቀለ መኮንንን በዶቼ ቬለ ስም በማመስገን ሙሉዉን ዝግጅት የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫn እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ