1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀ/ኃ/ሥ ኪነ-ቅርፅና ትችቱ

ሐሙስ፣ የካቲት 7 2011

በመጀመርያ ደረጃ የንጉሠ-ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ሐዉልት መቆሙም በራሱ ትልቅ ነገር ነዉ። ለምን በመዳልያ አልተደረገበትም ፤ ለምን ጺማቸዉ አልተላጨም ፤ ለምን ኮፍያ አላደረጉም፤ ሐዉልቱ ለምን አልወፈረም ለምን አልከሳም …እናም በጣም ከባድ ነዉ። ሰዉ ምኞቱና መቆርቆሩ ጥሩ ነዉ ወደፊት አዲስ አበባ ከተማ ዉስጥ ሲሰራ በጎፈር እናደርገዋልለን።

https://p.dw.com/p/3DPQW
Äthiopien - Die Afrikanische Union enthüllt eine Statue von Haile Selassie.
ምስል Bekele Mekonnen

«መጀመርያ እስቲ ምን ተሳክቶአል ብለን በቀና እንጠይቅ»

የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ያሁኑ የአፍሪቃ ሕብረት በ1950ዎቹ አጋማሽ እንዲመሠረት በግንባር ቀደምትነት ከታገሉ የአፍሪቃ መሪዎች አንዱ በመሆናቸዉ አዲስ አበባ በሚገኘዉ የሕብረቱ ቅፅር ግቢ የቆመላቸዉ ሐዉልት ሰሞኑን ተመርቋል። በኅልፈተ ሕይወታቸው 45 ዓመታት በኋላ ለክብራቸው የቆመዉ ሐዉልት  የተመረቀዉ ኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ዘዉዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ እንዲሁም በ32ኛዉ የአፍሪቃ ኅብረት ጉባዔ ለመካፈል አዲስ አበባ የመጡ በርካታ የአፍሪቃ ኅብረት አባል መንግሥታት መሪዎች፣ ንጉሣዊ ቤተሰቦች በተገኙበት ነዉ፡፡ የጃንሆይ ሐዉልት መቆሙ በርካቶችን ቢያስደስትም ሐዉልቱ ንጉሱን አይመስልም ሲሉ ትችት ያቀረቡ ጥቂቶች አይደሉም። የሀውልቱ ቀራጺ ረዳት ፕ/ር በቀለ መኮንን በበኩላቸዉ ሐዉልቱን መጥቶ ቦታዉ ላይ ማየት ጥሩ ነዉ መልስ ያገኛሉ ሲሉ ይመልሳሉ።  

Äthiopien - Die Afrikanische Union enthüllt eine Statue von Haile Selassie.
ምስል Bekele Mekonnen

የዛሬ 20 ዓመት አካባቢ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትን የተካዉ የአፍሪቃ ኅብረት የዛሬ ሁለት ዓመት አዲስ አበባ ላይ ባካሄደዉ 29ኛው መደበኛዉ የመሪዎች ጉባዔ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሐዉልት በኅብረቱ ዋና ጽ/ቤት  እንዲቆም መወሰኑ ይታወሳል፡፡ አዲሱ የኅብረቱ  ሕንጻ ሲመረቅ፣ ለአፄ ኃይለ ስላሴ ሐዉል ሳይቆም፣ የጋናው ፕሬዚዳንት ለነበሩት ክዋሜ ንኩሩማ ብቻ ሐውልት መቆሙ ብዙ ኢትዮጵያዉያንን ብሎም የአፍሪቃ ሃገራት ዜጎችን  ከፍተኛ ወቀሳና ትችት አስነስቶ ነበር። ኅብረቱ ለዚህ ከፍተኛ ጥያቄ ምላሽ ሰጥቶ ሥራዉ  የጀመረዉ የዛሬ ስድስት ወር መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ኪነ ቀራፂ ተባባባሪ ፕሮፊሰር በቀለ መኮንን ናቸዉ።

« ሰኔ ግንቦት አካባቢ የዉጭ ጉዳይ ሐዉልቱን ለማሰራት ወድያ ወዲህ በሚልበት ሰዓት ነዉ ወደእኔ ሲደዉሉ እኔም ወደ ትምህርት ቤት አመጣሁት። እንደሚታወቀዉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በሥነ ቅርፅ አኳያ ያለ አንድ ከፍተኛ ተቋም ነዉ። »  

Äthiopien - Die Afrikanische Union enthüllt eine Statue von Haile Selassie.
ምስል Bekele Mekonnen

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ኪነ ቀራፅያን በቀለ መኰንን፣ መስፍን ተስፋዬና ሔኖክ አዘነ እንደተነደፈና እና እንደተቀረፀ የተነገረዉ ሦስት ሜትር ርዝመት ያለው በነሐስ የተበጀው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ኪነ -ቅርፅ ሥራ ስድስት ወር እንደፈጀ አድካሚም እንደነበር ተባባባሪ ፕሮፊሰር በቀለ መኮንን ተናግረዋል። 

« በመጀመርያ ደረጃ የንጉሠ-ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ሐዉልት መቆሙም በራሱ ትልቅ ነገር ነዉ።  በዝያ መሠረት የዉጭ ጉዳይ መስርያቤት እኛ ባለሞያዎቹ እየተነጋገርን ቤተሰቦቻቸዉንም እያሳየን ነዉ የሰራነዉ። በሥነ ቅርፅ ስራ አኳያ ምንም አይነት ቴክኖሎጂ በሌለበት ኢትዮጵያ ስራዉ ለስድስት ወር ዘልቆአል በጣም አድካሚም ነበር።  በምረቃዉ ስነስርዓት ላይ የተገኙት ቤተሰቦቻቸዉ በሙሉ፤ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር አብረዋቸዉ የሰሩ በሕይወት ያሉ የካቢኔ ሚኒስትሮች ፤ የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎችና ተገኝተዋል። እንዲሁም በጥበብ ሥራ ላይ ትችት በማቅረቡ የሚታወቀዉ ክፍሌ ብፅአት «ፕሮፌሰር» ተገኝቶ ነበር። መርቀን ተመሰጋግነን ተደስተዉ ነዉ የተለያየነዉ። ከዝያ ፤ ሐዉልቱ እሳቸዉን አይመስልም የሚል ጭምጭምታ ሰማሁ። ትችት እንዲኖር ይጠበቃል አለበለዝያ ስራዉ ዋጋ የለዉም ማለት ነዉ። ነገርግን ሐዉልቱ ከመመረቁ በፊት በስቱድዮ እየሰራን ሳለ የሆነ ሰዉ ፎቶ አንስቶ በማኅበራዊ መገናኛ የለቀቀዉን አይተዉ ነዉ ብዙ ትችት ሲዘነዘር የነበረዉ።  ይህ ደግሞ የሆነዉ ሆን ተብሎ በመንጋ ሰዉ እንዲጮህ ተደርጎአል።  ከዝያ በኋላ ለቅን ሰዎች አንዳንድ ማብራርያ ለማድረግ ሞከርኩኝ ። ከዝያ በኋላ ብዙ ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ ይቅርታ ጠየቁ፤ አንዳንድ ባሉበት አይመልሰኝ ያሉም አሉ። »

Äthiopien - Die Afrikanische Union enthüllt eine Statue von Haile Selassie.
ምስል Bekele Mekonnen

በዚህም ይላሉ ትችት አቅራቢዎች ሁሉ ተባባባሪ ፕሮፊሰር በቀለ መኮንን፤ አፍሪቃ ኅብረት ጊቢ የቆመዉን የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሐዉልት ሄደዉ እንድያዩ እመክራለሁ።

የኛ ሰዉ ለስዕል አይደለም ለፖለቲካም የራሱን ሁኔታን ብቻ ነዉ የሚፈልገዉ። ለምሳሌ ይህን ሐዉልት አስመልክቶ መቶ ሚሊዮኑም የራሱ ጃንሆይ በችንቅላቱ ዉስጥ አለ። ለምን በመዳልያ አልተደረገበትም ፤ ለምን ጺማቸዉ አልተላጨም ፤ ለምን ኮፍያ አላደረጉም፤ ሐዉልቱ ለምን አልወፈረም ለምን አልከሳም …እናም በጣም ከባድ ነዉ። ሰዉ ምኞቱና መቆርቆሩ ጥሩ ነዉ ወደፊት አዲስ አበባ ከተማ ዉስጥ ሲሰራ በጎፈር እናደርገዋልለን። ይህ የመጨረሻ አይደለም። ጋና ዉስጥ 20 እና 30 ኑክሩማ ተሰርቶአል። እና አንዱም ከአንዱ አይመሳሰልም።  ለጃንሆይ የተሰራዉ ይህ ሐዉልት ለአፍሪቃ ኅብረት ነዉ። ንጉሠ ነገስቱ በአፍሪቃ ኅብረት ሲሳተፉ አለባበሳቸዉ ሁልጊዜ እንዲህ ነበር። ሐዉልቱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን አይመስልም መባልን የሰሙ ንጉሳዉያኑ ቤተሰቦች ምን መልስ ሰጥተዉ ይሆን?

 ሙሉ ቃለ ምልልሱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ!  

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ