1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል ንፁሐን በድሮን ድብደባ ተገድለዋል - ኢሰመኮ

ሰኞ፣ ጥቅምት 19 2016

በአማራ ክልል ለወራት በቀጠለው የትጥቅ ግጭት ምክንያት ድሮንን ጨምሮ በከባድ መሣሪያዎች በተሰነዘሩ ጥቃቶች በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ። በደብረ ማርቆስ በደምበጫ እንዲሁም በሰሜን ሸዋ የአንድ ዓመት ከሰባት ወር ሕፃንን ጨምሮ በርካታ ሲቪሎች ተገድለዋል።

https://p.dw.com/p/4YCQ6
ፎቶ ማህደር፤ አማራ ክልል የቀጠለዉ ግጭት
ፎቶ ማህደር፤ አማራ ክልል የቀጠለዉ ግጭት ምስል Awi zone communication office

በአማራ ክልል ጦርነት የአየር መሣሪያን ወይም ድሮንን ጨምሮ በከባድ መሣሪያዎች ጥቃት በርካታ ሲቪሎች ተገድለዋል ፤ የአካል ጉዳት ደርሷል

በአማራ ክልል ለወራት በቀጠለው የትጥቅ ግጭት ምክንያት ድሮንን ጨምሮ በከባድ መሣሪያዎች በተሰነዘሩ ጥቃቶች በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።የአማራ ክልል ውጊያ ወቅታዊ መረጃ

በሰሜን ሸዋ "የአንድ ዓመት ከሰባት ወር ሕፃንን ጨምሮ በርካታ ሲቪል ሰዎች" ፣ በደብረ ማርቆስ ስምንት ሰዎች እንዲሁም በደምበጫ ከተማ በርካታ ሰዎች በድሮን ጥቃት መገደላቸውን ኮሚሽኑ አምልክቷል። በሌላ በኩል በመንግሥት የጸጥታ ኃይል አባላት የሚፈጸሙ ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች አሁንም በአሳሳቢነታቸው መቀጠላቸውን ያስታወቀው ኮሚሽኑ የመንግሥት የጸጥታ አካላት በመንገድ ላይ ወይም ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ ከያዟቸው "በርካታ ሲቪል ሰዎች" ውስጥ "ፋኖን ትደግፋላችሁ፣ ለፋኖ መረጃ ትሰጣላችሁ፣ መሣሪያ አምጡ" በሚሉ ምክንያቶች ንፁሃን ዜጎችን መግደላቸውን ገልጿል።የአማራ ክልል የፀጥታ ሁኔታ የዛሬ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ውሎ

በግጭቱ ዐውድ የሚፈጸሙ የአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች አሳሳቢ እና በአፋጣኝ ተገቢው ምርመራ ተደረጎ እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባው መሆኑን የጠቆመው የኮሚሽኑ ዝርዝር መግለጫም ከሐምሌ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ቢያንስ 200 የአስገድዶ መድፈር ተጎጂዎች በጤና ተቋማት መመዝገባቸውንም ያሳያል ብሏል።

ምን ያህል ሰዎች ፣ የት አካባቢ በድሮን ጥቃት ተገደሉ ?

በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካካል በአማራ ክልል የቀጠለው የትጥቅ ግጭት በክልሉ በሁሉም ዞኖች በተለያየ ደረጃና ጊዜ መካሄዱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል። የትጥቅ ግጭቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያ እና አልፎ አልፎ በድሮን ድብደባ ጭምር የታገዘ መሆኑን የዘረዘረው ኢሰመኮ ወረዳዎችን መከላከያ እና የፋኖ ኃይላት በመፈራረቅ ሲቆጣጠሯቸው እንደቆዩም አመልክቷል።በአማራ ክልል 1,226 ፋብሪካዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ሥራ አቁመዋል

በግጭቱ ዐውድ የአየር መሣሪያን ወይም ድሮንን ጨምሮ በከባድ መሣሪያዎች ጥቃት ምክንያት በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱንና ሰዎች መኖሪያ አካባቢያቸውን ጥለው ለመሸሽ መገደዳቸውም ተገልጿል።

በሰሜን ሸዋ ዞን በረኸት ወረዳ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት የአንድ ዓመት ከሰባት ወር ሕፃንን ጨምሮ በርካታ ያላቸው ሲቪል ሰዎች ፣ በደብረ ማርቆስ ከተማ 8 ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉ እንዲሁም በደንበጫ ከተማ በከባድ መሣሪያ ድብደባ ምክንያት ሲቪል ሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎችና የዐይን ምስክሮች እንዳስረዱት ግልጿል። በኢሰመኮ የሕግና ፖሊሲ ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ታሪኳ ጌታቸው ስለ መግለጫው ለዶቼ ቬለ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል።  

ፎቶ ማህደር፤ ጎንደር ከተማ የፀጥታ ሁኔታ
ፎቶ ማህደር፤ ጎንደር ከተማ የፀጥታ ሁኔታ ምስል Nebiyu Sirak/DW

ከሕግ ውጪ ግድያ እና የአስገድዶ መድፈር ወንጅል

ኢሰመኮ በመንግሥት የጸጥታ ኃይላት የሚፈጸሙ ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች አሁንም ስለመቀጠላቸው ተዓማኒ መረጃዎችን ማግኘቱንና ግጭቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የጸጥታ አካላት በመንገድ ላይ ወይም ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ ከያዟቸው በርካታ ሲቪል ሰዎች ውስጥ «ፋኖን ትደግፋላችሁ፣ ለፋኖ መረጃ ትሰጣላችሁ፣ መሣሪያ አምጡ፣ የተኩስ ድምጽ ስለተሰማበት አቅጣጫ መረጃ ስጡ» በሚልና በመሳሰሉ ምክንያቶች ከሕግ ውጭ የሆኑ ግድያዎች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ ተዓማኒ መረጃዎች ለኮሚሽኑ እንደደረሱት ገልጿል።

በሲቪል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች፣ ግድያዎችና እገታዎች በታጠቁ ኃይሎች ተፈጽመዋል ያለው የኮሚሽኑ መግለጫ በግጭቱ ዐውድ የሚፈጸሙ የአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች በጣም አሳሳቢ እና በአፋጣኝ ተገቢው ምርመራ ተደረጎ እርምጃ እንዲወሰድ የጠየቀው ኮሚሽኑ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ቢያንስ 200 የአስገድዶ መድፈር ተጎጂዎች በጤና ተቋማት ተመዝግበዋል ብሏል።የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

ለዘላቂ መፍትሔ የኢሰመኮ ጥሪ

በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ በመደንገጉ ምክንያት የእንቅስቃሴ ጎደቦች ፣ የኢንተርኔት መቋረጥ እና ሌሎች እርምጃዎች ተወስደዋል። ከትጥቅ ግጭቱ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ሲቪል ሰዎች እና የሲቪል የንግድ እና የመሠረተ ልማት ተቋማት ላይ ዝርፊያ፣ የማሳ ላይ ሰብል ውድመት ጨምሮ በሲቪል ሰዎች፣ በሕዝብ እና በመሠረተ ልማት ላይ ጉዳት ደርሷል። በክልሉ የንግድ እና የማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በፈጠረው ተጽዕኖ ነዋሪዎች ለአቅርቦት እጥረት እና ለዋጋ ንረት እንዲሁም ለተያያዥ ችግሮች ተዳርገዋል።  ግጭቱን በዘላቂነት ለመፍታት ለሁሉም ሰላማዊ አማራጮች አሁንም ቅድሚያ እንዲሰጥ ኢሰመኮ ጥሪ አቅርቧል።

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ