1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

ፕሬዝዳንት ባይደንና ተመራጩ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ነጩ ቤተ-መንግሥት ዉስጥ ተገናኙ

አበበ ፈለቀ
ሐሙስ፣ ኅዳር 5 2017

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንና ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትላንት ኋይት ሃውስ ተገናኝተው ተወያይተዋል። ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ሲለቁ ለጆ ባይደን ያላደረጉት ቢሆንም እንዲህ ያለው ተግባር ለዘመናት የኖረ፣ የአሜሪካ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አንድ አካል ነው። ሁልቱም ወገኖች ለሰላማዊና ለሰከነ ሽግግር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4mypI
USA | Joe Biden trifft Donald Trump
ምስል Saul Loeb/AFP/Getty Images

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንና ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተጨባበጡ 

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንና ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትላንት ኋይት ሃውስ ተገናኝተው ተወያይተዋል። ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ሲለቁ ለጆ ባይደን ያላደረጉት ቢሆንም እንዲህ ያለው ተግባር ለዘመናት የኖረ፣ የአሜሪካ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አንድ አካል ነው። ሁልቱም ወገኖች ለሰላማዊና ለሰከነ ሽግግር እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው አዲስ የሚመሰርቱትን ካቢኔ የሚቀላቀሉ ሹሞቻቸውን በመሰየም ተጠምደዋል። እስካሁንም የያዙትን አጀንዳ ያሳኩልኛል ብለው ከመረጧቸው እጩወች ውስጥ በብዙወች ዘንድ ግርምትና ግርታን የፈጠሩም አሉ።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንና ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትላንት ኋይት ሃውስ ተገናኝተው ተወያይተዋል። ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ሲለቁ ለጆ ባይደን ያላደረጉት ቢሆንም እንዲህ ያለው ተግባር ለዘመናት የኖረ፣ የአሜሪካ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አንድ አካል ነው። ሁልቱም ወገኖች ለሰላማዊና ለሰከነ ሽግግር እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው አዲስ የሚመሰርቱትን ካቢኔ የሚቀላቀሉ ሹሞቻቸውን በመሰየም ተጠምደዋል። እስካሁንም የያዙትን አጀንዳ ያሳኩልኛል ብለው ከመረጧቸው እጩወች ውስጥ በብዙወች ዘንድ ግርምትና ግርታን የፈጠሩም አሉ።

ዶናልድ ትራምፕ የዛሬ አራት አመት በጆ ባይደን መሸነፋቸውን ዛሬም ድረስ አላመኑም። ለወትሮው የተለመደውን የ’ተሸንፌያለሁ’ ስልክም አልደወሉም። ጆ ባይደንን ወደ ኋይት ሃውስ አልጋበዙም። በጆ ሃይደን በዓለ ሲመት ላይም አልተገኙም። ጆ ባይደን ግን ብድር በምድር ሳይሉ፣ የአሜሪካ የዲሞክራሲ ትሩፋት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር መሆኑን ባስረገጠ መንገድ፣ አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ ዶናልድ ትራምፕን ወደ ኋይት ሃውስ እንኳን ደህና መጡ ብለዋቸዋል። በዚሁ  የኋይት ሃውስ ቆይታቸው ዶናልድ ትራምፕም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ከሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በዘለለም፣ የሃገሪቷ ዋና ዋና ትኩረቶች በሆኑ እንደ ዩክሬይን፣ እና መካከለኛው ምስራቅ ያሉ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸው ተነግሯል። ከጆ ባይደን ጋር ሲገናኙ ቁጥብና ሰከን ያለ ስበዕናን ያሳዩት ዶናልድ ትራምፕ፣ የካቢኔ ሹሞቻቸውን ባናት ባናቱ እያሳወቁ ነው። የመረጧቸውም ሰወች ከወትሮው በተለየ፣ ያስቀመጡትን አጀንዳ የሚያስፈጽሙ፣  እጅጉን ታማኝ የሆኑና ሲጠሯቸው አቤት፣ ሲልኳቸው ወዴት የሚሉ አይነት እንደሆኑ እየተነገረ ይገኛል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንና ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተጨባበጡ
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንና ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተጨባበጡምስል Artem Priakhin/Sipa/Sopa/picture alliance

የመከላከያ ሚኒስትር አድርገው የሾሟቸው ፒት ሄግሴት የብሄራዊ ጥበቃ ጦር አባል ሆነው ያገለገሉ፣ የዶናልድ ትራምፕ ታማኝና የወግ አጥባቂው ፎክስ ቴሌቪዥን አቅራቢ ናቸው። የአመራር ልምድ የሌላቸው ፒት ሄግሴት፤ ‘ሴቶች ጦርሜዳ የመዋል አቅም የላቸውም፣ ይህን አይነቱን አካታችነት ሚና የሚጫወቱ ጀነራሎች ደግሞ መባረር አለባቸው’ የሚሉ የዶናልድ ትራምፕ ቀንደኛ ደጋፊ ናቸው። እናም ለዚህ ከሶስት ሚሊዮን በላይ የሰው ሃይል ላለው፣ እጅግ የተወሳሰበ ቢሮክራሲና አለማቀፍ ሽፋን ላለው የመከላከያ መስርያ ቤት መታጨታቸው በሁሉም ዘንድ ድንጋጤን ፈጥሯል።

ሌላው በሁሉም ዘንድ አግራሞትን የጫረው፣ በተወካዮች ም/ቤትም በፍትህ ሚኒስትርም በኩል የወንጀል ምርመራ ስር የሚገኙትን የፍሎሪዳውን ተወካይ ማት ጌይትዝን ጠቅላይ አቃቢ ህግ አድርገው መሾማቸው ነው። ይሄ ቦታ ለዶናልድ ትራምፕ ልዩ ትርጉም አለው። የፍትህ ሚኒስቴርንና የደህንነቱን ተቋማት ተጠቅመው የተቃወሟቸውንና በጠላትነት የፈረጇቸውን ቁም ስቅላቸውን ሊያሳዩ፣ በራሳቸው ላይ የተመሰረቱ ክሶችንም ለያቋርጡ ዝተዋል።

የቀድሞው የቴክሳስ ተወካይና በመጀመርያውየትራምፕ የስልጣን ዘመን የብሄራዊ ደህንነት ቢሮ ዳይሬክተር የነበሩትን፣ የዶናልድ ትራምፕ ታማኝ ጆን ራትክሊፍ የአሜሪካው የስለላ ተቋም (ሲአይኤ) ዳይሬክተር አድርገው መርጠዋቸዋል። ከተሰጡት ሹመቶች ውስጥ ከታማኝነት ሌላ የስራ ብቃትና ልምድን ከግምት ያስገባ የተባለለት፣ የፍሎሪዳውእንደራሴ ማርኮ ሩብዮ ለውጪ ጉዳይ ሚኒትርነት መሾም ነው። የቀድሞው የአርካንሰስ ገዢና ‘ዌስት ባንክ ብሎ ነገር የለም እስራኤል እንጂ’ የሚሉት ማይክ ሃከቢንም በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር አድርገው ሾመዋቸዋል።

እነዚህና ሌሎች ሹሞቻቸው በአሜሪካው የእንደራሴወች ም/ቤት ተገምግመው ማለፍ ይኖርባቸዋል። በሰፊ የድምጽ ልዩነት ያሸነፉት ዶናልድ ትራምፕ፣ ሴኔቱም፣ የተወካዮች ም/ቤቱም በሪፐብሊካን እጅ ወድቆላቸዋል። ዶናልድ ትራምፕ ያሰቡትን፣ ያለሙትን ያለከልካይ መፈጸም ከቻሉ፣ የአሜሪካ ማህበረ፣ ፖለቲካ፟ ኢኮኖሚያዊ ሁባሬ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ይቀይረዋል ብለው የሚፈሩ ብዙ ናቸው። የዛኑ ያህልም ይሄን ለውጥ የደገፉ፣ ዶናልድ ትራምፕና ሃሳባቸውን የመረጡ በልጠዋልና፣ ለጊዜው፣ ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ ከመጠበቅ ያለፈ ሌላ አማራጭ ያለ አይመስልም።

አበበ ፈለቀ

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ