1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፆታዊ ጥቃቶችን በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች መዋጋቱ ምን ያህል ስኬታማ ነው?

ዓርብ፣ ሐምሌ 3 2012

አፍሪቃ ውስጥ ስለ ፆታዊ እና ወሲባዊ ጥቃት ማውራት እንብዛም የተለመደ አይደለም። ይህ የዝምታ ባህል በተለይ ሰሜን ናይጄሪያ ውስጥ የባሰ የሚባል ነው። ይሁንና አሁን አሁን አንዳንድ ወጣቶች በማህበራዊ የመገናኛ ብዙኃን በጀመሩት ዘመቻ ማህበረሰቡን ግንዛቤ እያስጨበጡ እና የጥቃት ሰለባዎችንም ፍትህ እንዲያገኙ እያበረታቱ ነው።

https://p.dw.com/p/3f13S
The 77 Percent Abuja
ምስል DW

ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃቶችን በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች መዋጋቱ ምን ያህል ስኬታማ ነው?

ከሦስት ዓመታት ገደማ በፊት #MeToo በሚል የፆታ እና ወሲባዊ ጥቃትን በመንቀፍ የጀመረዉ  ዘመቻ በዓለማችን ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማግኘቱ ይታወሳል። ይህንን ሀሽታግ ወይም መንሰላል የሚመስለውን ምልዕክት በመጠቀም በርካታ ሴቶች እነሱም ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ አልያም ጥቃት ደርሶ እንደነበር በትዊተር እና ሌሎች የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በድፍረት በመፃፍ ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ምልዕክቱ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተፃፉ ሀሳቦችን በቀላሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ለማግኘት ይረዳል።

ይህ የኢንተርኔት ዘመቻ ናይጄሪያ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችም ዝምታቸውን እንዲሰብሩ አበረታቷል። ወጣቶቹ #ArewaMeToo የሚል ንቅናቄ በማህበራዊ የመገናኛ ብዙኃን ጀምረዋል። አርዋ ሰሜን ናይጄሪያ ውስጥ የምትገገኝ ከተማ ናት። የዶይቸ ቬለዋ ኤዲት ኪማኒ ወደ አቡጃ በመጓዝ ፆታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶችን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መዋጋቱ ምን ያህል ስኬታማ እንደሆነ አጠያይቃለች። በጎዳና ላይ በተካሄደው ክርክር ከተሳተፉ ናይጄሪያውያን መካከል የዘመቻው አራማጆች፣ የመብት ተቆርቋሪዎች እና የፖሊስ ባልደረባ ይገኙበታል። ሚሪያም አዋይሱ የዚህ ዘመቻ አራማጅ ናት። በምታካሂደው ዘመቻ ምክንያትም ታስራም ነበር።“ በግልፅ ሰዎችን ዝም ለማስባል የተደረገ ነው። ለዚህም ነው ኢንተርኔትን ተጠቅሞ ሌሎችን በመጉዳት ክስ የታሰርኩት። ከየት እንደመጣ እንኳን አላውቅም። ሰዎች ከሐይማኖት ጋር ያገናኙታል። እኔ ግን ሐይማኖትን በተሳሳተ መልኩ ማቅረብ ነው የምለው።  ምክንያቱም አብዛኛው ሰሜን ናይጄሪያ የሚገኘው ማህበረሰብ የእስልምና እምነት ተከታይ ነው። እስልምናን የምትረጂ ከሆነ ደግሞ ይህ ትርጉም አይሰጥም። እስልምና መጥፎ ነገር ሲደርስባችሁ ዝም በሉ ወይም ሸሽጉ አይልም። ስለሆነም ሐይማኖትን እና ባህልን በተሳሳተ መልኩ የማቅረብ ሁኔታ አለ። »

Symbolbild #MeToo
ምስል picture alliance/dpa/B. Pedersen

ስለሆነም ጥቃት የሚደርስባቸው ልጃ ገረጆች ዝምታን ይመርጣሉ ትላለች ሚሪያም። ወላጆችም ቢሆኑ ከማህበረሰቡ በሚደርስባቸው ጫና ምክንያት ለተጠቂ ልጆቻቸው ከዝምታ በቀር ለፍትህ እንዲታገሉ አያደፋፍሩዋቸውም። በመሆኑም ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ሚሪያም ታመላክታለች። ሌላው ችግር ደግሞ ለፆታዊ እኩልነት የምትሟገተው ኡሚ ቡከር እንደምትለው ባህላዊ ተፅዕኖው ነው። በተለይ በዚህ በአርዋ አካባቢ ሰዎች በተወሰኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በግልፅ ለመወያየት እና ግንዛቤ ለመጨበጥ ያፍራሉ። ይህንን ሀሽታግ ወይም ምልዕክት ተጠቅማ ለመጀመሪያ ጊዜ የፃፈችው ፋክሪያህ ሂሻም ዝምታውን እንዴት ለመስበር እንደቻለች ትገልፃለች።«የ ArewaMeToo ሀሽታግ በአጋጣቢ የሆነ ነገር ነው። ከሁለት አመት በፊት አንዲት ወጣት ሴት በትዊተር ስለደረሰባት ጥቃት በግልፅ ትናገራለች። እኔም ይህን ያደረኩት ድጋፌን ለመግለፅ ነበር እንጂ የሰው ቁስል ይነካል ብዬ አልጠበኩም ነበር። የሆነው ነገር ግን ሰዎች በዚህ ሀሽታግ ስር ከለላ የሚያገኙበት ስፍራ ፈጥሯል።»

The 77 Percent Abuja
ምስል DW

ወጣቶቹ እንደሚሉት ፆታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶች የሚደርስባቸው ሰዎች በዚህ ምልዕክት ስር ትዊተር ላይ የሚያገኙት ድጋፍ እና ከለላ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ከሚያገኙት የተሻለ ነው። የኦንላይን ዘመቻን የምታራምደው ሚሪያም ምሳሌ አላት« የአስገድዶ መድፈር ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች አሉ። በሆነው ነገር ተደናግጠው ወደ ፖሊስ የሚሄዱ። እዛ ሲደርሱ ግን የሚደረግላቸው አቀባበል በራሱ ሌላ ጥቃት ነው። ከተደፈረች ልጅ ጋር አብሬ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄጄ አውቃለሁ። ፖሊስ ግን ይባስ እሷኑ ተጠርጣሪ ነው ያደረጋት። ያየሁትን እንጂ የሰማሁትን አይደለም እየተናገርኩ ያለሁት። ፈጣሪ ከዚህ ይሰውረኝ እንጂ ይህ ቢደርስብኝ እኔም በፍፁም ወደ ፖሊስ ጣቢያ አልሄድም። ከዚህ ይልቅ የማህበራዊ መገናኛን እመርጣለሁ። »

 ወጣቶቹ እንደሚሉት አቡጃ ውስጥ ሳይቀር በምሽት የተደፈች ሴት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ስትሄድ ያገኘችው ምላሽ የወሲብ ሰራተኛ ነሽ ወይ የሚል እና ሴት ሆና በምሽት ጎዳና ላይ መገኘት እንዳልነበረባት ነው። ጥፋተኞችን ለፍርድ ያቀርባል ተብሎ የሚጠበቀው ፖሊስ ላይ ለምን ወጣቶቹ እምነት የላቸውም? ችግሩ ያለው ምኑጋ ነው? የአቡጃ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሳኒ ባባ ወቀሳውን በከፊል ያጣጥላሉ። የፖሊስ ባልደረቦች እንደዚህ አይነት ክሶችን አግባብ ባለው መልክ እንዲቀበሉ የተለያዩ የዘርፍ ክፍሎች እየተቋቋመ እና ስልጠና እየተሰጣቸው ነው። እንደ እሳቸው ከሆነም « ጉዳዩን በኦንላይ ማቅረብ ችግሩን ያስወግዳል ወይም ሁኔታውን በቁጥጥር ስር አድርጓል ማለት አይደለም።» በተለይ በገጠራማው አካባቢ ለሚገኙ የጥቃት ሰለባዎች።«  እንበል እና አስገድዶ የመድፈር ጥቃት የደረሰባት የ 14 ዓመት ወጣት ልጅ ናት። የት ነው የምትሄደው? የማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች እስከመኖሩ እንኳን አታውቅም። ስለዚህ ወደቤት ስትመለስ ለእናቷ ትነግራታለች። እናቷ ደግሞ በቅርቱ ትዳሪያለሽ። ዝም በይ አርፈሽ ተቀመጭ ትላታለች። ስለዚህ ትኩረታችንን ገጠራማው አካባቢ ላይ ማድረግ ይኖርብናል። አቡጃ ላይ በወር በአማካይ 100 የሚሆኑ የአስገድዶ ወንጀል ጥቃቶችን ፖሊስ ጣቢያ ይመዘገባሉ። »

Symbolbild Gewalt gegen Frauen Vergewaltigung
ምስል Fotolia/detailblick

ከነዚህ 100 ክሶች 80 በመቶ ያህሉ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ክሶቹ ይቋረጣሉ። ይህም የፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው እንደሚሉት ጥቃት አድራሹ ይሰወራል ወይም የተጠቂ ወላጆች ክሱን ያነሳሉ።ሌላዋ በዚህ የጎዳና ክርክር ላይ የተካፈለችው ወጣት ሲቦማሪ ገጠመኟን ታስረዳለች። አስገድዶ የመድፈር ጥቃት እንዲቆም ለሚታገል አንድ ተቋም ውስጥ ነው የምትሰራሉ።« ባለፈው ወር አንድ የተደፈረች ልጅን ይዤ ፖሊስ ጣቢያ ሄጄ ነበር። የእንግዳ መቀበያው ጋር በአስገድዶ መድፈር ክስ ምክንያት እንደመጣን ነገርኳቸው እና በዛ ሰዓት የጠበኩት ወደ ሚመለከተው ክፍል እንደሚያስተላልፉን ነው። ነገር ግን ሰው ሁሉ በተሰበሰበበት በዚሁ ቦታ ተጠቂዋን በጥያቄዎች አፋጠጧት። ጥቃቱ የተፈፀመው አርብ ዕለት ነበር የሄድነው ደግሞ ሰኞ ዕለት ነው። ልጅቷ በሆነው ነገር ተጎድታ ስለነበር ምን እንደምታደርግ አታውቅም ነበር። ስለ እኛ ተቋምም ገና መስማቷ ነው። ብቻ ጥቃቱ መቼ እንደተፈፀማት ስትናገር አንዷ ሴት ፖሊስ ታድያ ዛሬ ነው የምትመጪው በማለት ጮሀባት ክፍሉን ለቃ ወጣች።»

እነዚህም ወቀሳዎችን ሲሰሙ የአቡጃ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምን ይሰማቸው እንደው ጋዜጠኛ ኤዲት ኪማኒ ጠይቃቸውም ነበር።« አዎ ይከሰታል። እሳዝነናቸውም እናውቃለን። የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመን ሊረዳ ይችላል። ነገር ግን መጥፎ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ ዝምብለው የሚወነጀሉ እንዳሉም እናውቃለን። »ከወሲባዊ ጥቃት ባሻገር ሴቶች ናይጄሪያ ውስጥ በዋንኛነት ፆታዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ህጉም ቢሆን ሴት ለባሏ ታዛዥ እንድትሆን ያበረታታል እያሉ የፆታ መብት ተከራካሪዎች ይተቻሉ።

ይሁንና ይህ የኢንተርኔት ዘመቻ ዝምታን እያስቆመ እና ለውጥም እያስገኘ ነው

« አንድ አስገድዶ መድፈሩን ያጋለጥኩት ሰው ከስራው እንዲለቅ ተደርጓል። እንደሚመስለኝ ይህ ዘመቻ ያስከተለው መዘዝ ነው። ይህንን የሚፈፅሙ ወጣቶች እንዲያስቡበት አድርጓቸዋል። ነገ እኔም ሀሽታግ ተደርጌ ይፃፍብኝ ይሆን? እንዲሉ አድርጓቸዋል።ይህ የሚያስከትለው መዘዝ ነው። መቼም አንዱ ጋር መጀመር አለበት።» ትላለች ሚሪያም። ፋክሪያህ ይህንን #ArewaMeToo ንቅናቄ ስትጀምር አላማዋ የወሲብ ጥቃት ለደረሰባቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆን ፤ ፆታዊ ትንኮሳ ለደረሰባቸው እና ለተደበደቡ ሰዎችም ጭምር ነበር።  ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለወንዶች እና ህፃናትም ።«  #ArewaMeToo እንደሚያመላክተው በተለይ ሰሜን ናይጄሪያ ውስጥ አብዛኞቹ የወሲብ ተጠቂዎች ህፃናት እንደሆኑ ነው። »

ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቅሞ ውስንነት

 የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ተጠቅሞ የማጋለጡ ሁኔታ ውስንነት አለው። አንዳንድ ወንዶችን እንዲሸማቀቁ እያደረገ መሆኑን ነው በዚህ ክርክር የተካፈለው የኮሚኒኬሽን ተመራማሪ ኦሲ ኤስቶሞቦር የሚያብራራው። ሌላው የዚህ ዘመቻ ፈተና ደግሞ የአመኔታ ጉዳይ ነው።« በማህበረሰቡ ውስጥ የተወሰኑ ሰዎች የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ህግ የሌለበት ቦታ እንደሆነ ያምናሉ። ስለሆነም እዛ ላይ የሚፃፉ ነገሮች አመኔታ የላቸውም የሚል ነገር አለ። ስለዚህ ኢንተርኔት በተወሰነ መልኩ በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባ ነው።» ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከፖሊስ ስራ ጋር ይገናኛል። በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሲወነጀል የነበረን ሰው ጉዳይ ፖሊስ እንዴት ይመለከተዋል? የፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው የወጣቶቹ ንቅናቄ ጥሩ ቢሆንም ወሬውን ለአለም ከማሰራጨታቸው በፊት ጠበቃ ይዘው ይከራከሩ ባይ ናቸው።  ተደብድቤያለሁ ብላ የምትከስ ሴት ካለችም እንደ ፖሊሱ ከሆነ አንድ ጊዜ ብቻ በቂ አይደለም።« ባለቤቷን ጠርተን እንደይቃለን። ተደጋግሞ የሚከሰት ነገር ነው? ወይስ አንድ ጊዜ ብቻ የሆነ ነገር? ስንል እንጠይቃለን። ወደድንም ጠላንም ናይጄሪያ ውስጥ ነው ያለነው። ባህል ሚና ይጫወታል። መታ ስትከስ እናምናታለን? አናምናትም። ማረጋገጫ እንፈልጋለን። የአይን እማኝ ካለ ሁሉንም ማስረጃዎች እናሰባስባለን። »አብዛኛውን ጊዜ እንደዚህ አይነት ፆታዊም ይሁን ወሲባዊ ጥቃቶች ሲፈፀሙ የአይን እማኞች በሌሉበት ቦታ መሆኑ ፖሊሱን ብዙም አያሳስባቸውም።

Symbolbild Gewalt gegen Frauen
ምስል Fotolia/Miriam Dörr

ታድያ መፍትሄው ምንድን ነው?

« ይሔ ታገሽ ታገሽ የሚለው ምክር እየገደለን ነው። አሁን ስለ ልጃ ገረዶች እና ሴቶች ነው በብዛት እያወራን ያለነው ነገር ግን ወንድ ልጆችም ጥቃት ሲደርስባቸው መናገር ትክክል እንደሆነ ልናስረዳቸው ይገባል።»

« ውይይቱ የማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ውስን እንደሆነ አሳይቶናል ይሁንና ያለውን ሁኔታ አጉልቶ ማሳየት ይችላል። ፍርድ ለመስጠት ይህን አስፈፃሚ አካላት ያስፈልጉናል። ሰዎች ወንጀል ፈፅመው ማምለጥ እንደሚችሉ ያውቃሉ። ምክንያቱም በሀገራቸውን የሚደረገው የወንጀል ክትትል እና ምርመራ ው ትንሽ በመሆኑ ። በ 2017 ዓም  በመላው ናይጄሪያ 18 ክሶች ብቻ መሰለኝ ብይን ያገኙት።  ይህ የሚያመላክተው የማይረባ ስርዓት እንዳለን ነው።  በማህበረሰባችን መካከል ያለውንም ክፍተት መረዳት ይኖርብናል። ግንዛቤ ከማስጨበጥ ስራው እና ከህጉ በተጨማሪ ይህ የሚተገበርበት መንገድ መፈጠር ይኖርበታል።»ይላሉ ፆታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶችን በሚመለከት በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ግንዛቤ ማስጨበጥ እና ዝምታን መስበር የጀመሩት ናይጄሪያዊ ወጣቶች።

ኢትዮጵያ ውስጥም ቢሆን ፆታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶች በተለይ በዚህ በኮሮና ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተረጋግጧል። ከ 100 በላይ በሆኑ ህፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት መፈፀሙም ይፋ ሆኗል። ይህም በሀገሪቱ ዝም አልልም የሚል ዘመቻ አስነስቷል። 

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ