ፅንስ ለማቋረጥ ፈቃጁ ማነው?
ዓርብ፣ ሰኔ 24 2014የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከ 50 ዓመታት በኋላ ባለፈው ዐርብ ሴቶች ፅንስን ማቋረጥ እንዲችሉ የሚፈቅደውን ህግ ውድቅ አድርጓል። ውሳኔው ይፋ በሆነበት ወቅት ደስታቸውን ከገለፁ አሜሪካውያን አንዱ የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው። እሳቸውም« ፍርዱ የእግዚአብሔር ውሳኔ ነው» ሲሉ ለፎክስ ኒውስ የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል። ለመሆኑ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በተግባር ምን ማለት ነው?
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በዩናይትድ ስቴትስ ከ50 ዓመታት በፊት የነበረውን ህጋዊ ሁኔታ ወደነበረበት ይመልሳል። ይህም የሀገሪቱ ግዛቶች ፅንስ ማቋረጥን በሚመለከት ጠንካራ ገደብ እንዲጥሉ ወይም ሙሉ በሙሉ ማገድ እንዲችሉ ይፈቅዳል። የሚዙሪ ግዛት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ይፋ እንደሆነ ወዲያው ህጉን ሙሉ በሙሉ እንደሚተገብር አስታውቋል። ሙሉ በሙሉ ማለት ደግሞ አንዲት የተደፈረች ሴት ብታረግዝ ወይም ፅንሱ የተገኘው ከዘመድ ቢሆን እንኳን ፁንሱን ማቋረጥ አይፈቀድላትም። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እስካሁን በሰባት ግዛታት ፅንስ ማቋረጥ ህገ ወጥ ነው።
ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን በርካታ አሜሪካውያን ፅንጹን ማቋረጥ በህግ ወደማያስጠይቃቸው ቦታ በመጓዝ ለመፈፀም ከፍተኛ ወጪ ማውጣት እንዳለባቸው ይናገራሉ።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ « ትልቅ ስህተት ነው» በማለት አውግዘው የሀገሪቱ ሴቶች ጤና እና ህይወት አሁን አደጋ ላይ እንደሆነ እና ሰዎች በሰላማዊ ሁኔታ ለፅንስ ማቋረጥ መብት እንዲሟገቱ አሳስበዋል። በሀገሪቱ ከግማሽ ዓመት በፊት የተደረገ አንድ መጠይቅ እንደሚጠቁመው 71 በመቶ አሜሪካውያን ፅንስ ማቋረጥ በመጀመሪያዎቹ ሶስት የእርግዝና ወራት እንዲገደብ ይስማማሉ። 17 በመቶ አሜሪካውያን ደግሞ አንዲት ሴት በማንኛውም የእርግዝና ወር ፅንሱን የማቋረጥ እድል እንዲኖራት ይስማማሉ።
ፅንስን ማቋረጥን በተመለከተ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችስ ምን ይላሉ? የኢትዮጵያ ህግስ ምን ይላል?
ወጣት ሃና የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ውሳኔ ትደግፋለች። ሙሉ በሙሉም ባይሆን ፅንስ ማቋረጥን የሚከለክል ህግ መኖሩ አስፈላጊ ነው ባይ ናት። « የተለያዩ መከላከያዎች አሉ። ፅንስ እንዳይፈጠር መጀመርያ ላይ ሊወሰዱ የሚችሉ እንደ እንክብል ወይም መርፌ የመሳሰሉ መከላከያዎች አሉ። » እነዚህ ነገሮች ሳይደረጉ ፅንስ ከተፈጠረ ግን ሴቲቱ ፅንስ እንዳታቋርጥ ብትደረግ ትክክል ነው የምትለው ሃና « ማንም ሰው ፈቅዶ ባላመጣው ዓለም ላይ ማንንም የማስወገድ መብት አለው ብዬ አላምንም» ትላለች። ሴቲቱ ተደፍራ ወይም ፆታዊ ጥቃት ደርሶባት ከሆነ ግን ፅንስ ማቋረጥ መቻሏ አግባብ ነው ባይ ናት።
ሌላው ኢትዮጵያዊ ወጣት እመሻው፤ ፅንስ ማቋረጥን አይደግፍም አይቃወመውምም « ብዙ ጊዜ እንደዚህ አይነት ነገር የሚፈጠረው ባልታሰበ ሁኔታ ነው። እና ባይደረግ ጥሩ ነው። ከባድ ሆኖ ከሆነ ደግሞ በጤና ጣቢያ ውስጥ ቢደረግ ጥሩ ነው። አንዛኛውን ጊዜ በባህላዊ መንገድ የሚያደርጉ አሉ»
ዶክተር ሲሳይ ተክሉ፤ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ጥቁር አምበሳ ሆስፒታል የማህጸን ሀኪም ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ሰዎች ወይም ማህበረሰቡ ለህይወት የሚሰጡት ትርጉም ነው ፅንስ ላይ የሀሳብ ልዩነቱን የፈጠረው፤ « ፅንስ በአልትራሳውንድ ቢታይ ከአራተኛው ሳምንት አንስቶ የልብ ምት ይታያል። ያ ህይወት ያለው ነገር መብት አለው። ፅንስ ማጨናገፍን የሚደግፉ ሰዎች ደግሞ እስኪወለድ ድረስ ተሸክማ የምታሳድገው እናቲቱ ስለሆነች እሳ የመወሰን መብት አላት ብለው ነው የሚከራከሩት።» ፅንስን ማቋረጥ ኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው የተከለከለ እንደነበር የሚያስረዱት ዶክተር ሲሳይ በ 2005 ዓ ም ተሻሽሎ የቀረበው አንቀፅ 545 የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ላይ እንደሚብራራ ይናገራሉ። «በዚህም መሠረት ፅንስ ማቋረጥ ህገ ወጥ ነው። ይህንንም የምታደርግ ሴትም ትሁን ያንን የፈፀመ ባለሙያ በህግ ይቀጣል። ነገር ግን ያ ፅንስ የተከሰተው በመደፈር ወይም ከቤተሰብ ጋር በተደረገ ግንኙነት ከሆነ፣ እናቲቱ ልጁን የማሳደግ አቅም ከሌላት እና የአዕምሮ በሽተኛ ከሆነች፣ ወይም ፅንሱ የማደግ ሁኔታው አስቸጋሪ ከሆነ ወዘተ » ህጉ የሚፈቅድበት ሁኔታ አለ።
ዶክተር ሲሳይ እንደሚሉት «ፅንሱ በመደፈር ምክንያት ከተከሰተ» የሚለውን አንቀፅ ያላግባብ የሚጠቀሙ በርካታ ሴቶች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ። ይህም ባለጉዳይዋ መደፈሯን ከተናገረች በቂ ስለሆነ እና በማስረጃ ማረጋገጥ ስለማይጠበቅባት ነው« ይህን ለማረጋገጥ የሚወስደው ጊዜ ረዥም ጊዜ ስለሆነ ያ እስከሚደረግ ፅንሱ ያድግና ለማጨናገፍ አስቸጋሪ ደረጃ ላይ ይደርሳል። ስለዚህ ብዙ ሰዎች ወደ ጤና ተቋማት ይሄዱ እና ይኼ በመደፈር የመጣ ፅንስ ነው ብለው ያንን አገልግሎት ያገኛሉ።
ይህ ግን እንደ ዶክተር ሲሳይ ገለፃ በተለያዩ ምክንያቶች ልክ አይደለም። ዶክተር ሲሳይ የማህፀን ሀኪም እንደመሆናቸው የተለያዩ የጸነሱ ሴቶች ይገጥሟቸዋል። በተለይ ደግሞ ፅንስ ማቋረጥን እንደ ቤተሰብ ምጣኔ አድርገው ሰዎች መቁጠር የለባቸውም የሚሉት ዶክተር ሲሳይ ይህ ከሞራል አኳያ ብቻ ሳይሆን ከጤና አኳያም አይመከርም» ይላሉ ።
ስለሆነም ዶክተር ሲሳይ ወጣት ሴቶች ማወቅና ማድረግ አለባቸው የሚሉት « እርግዝናውን ካልፈለጉ መከላከያ መንገዶች አሉ። እነዚያን መከላከያ መንገዶች እንደ ስራ አድርገው መውሰዳቸውን ርግጠኛ መሆን ይኖርባቸዋል። ማጨናገፍ በጣም ከባድ ነገር ነው። የሞራል ጥያቄ አለው። ከአጨናገፉ በኋላ ሴቶች ብዙ የምክር አገልግሎት ያስፈልጋቸዋል። ድብርት ሊይዛቸው ይችላል። ስለዚህ እዛ ነገሮች ውስጥ ከመግባታቸው በፊት የተሻሉ ነገሮችን ማድረግ ይኖርባቸዋል። » ይላሉ የማህፀን ሀኪም የሆኑት ዶክተር ሲሳይ ተክሉ ።
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ