ፀረ ሴማዊ ጥቃት በጀርመን
ሐሙስ፣ መስከረም 29 2012በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መባቻ ከ 6 ሚልዮን የሚልቁ አይሁዳውያን በጀርመኖች የአይሁዳውያን ጥላቻ ወይም ፀረ-ሴማዊነት ዘመቻ በግፍ ሕይወታቸውን ማጣታቸውን በማስታወስ ነው የዶቼ ቨለዋ DW ዋና አርታኢ ኢናስ ፖል ትላንት በጀርመን ዳግም በአይሁዳውያን ላይ የተቃጣውን የወንጀል ድርጊት የቃኘችበት ዘገባ የሚጀምረው:: በናዚ የስልጣን ዘመን ከ 80 ዓመታት በፊት ከተፈጸመው አስከፊው ጭፍጨፋ በኋላ በትላንትናው ዕለት በምስራቅ ጀርመን አንሃልት ክፍለሃገር ሃለ ከተማ በአይሁዳውያን ዕምነት " የኃጢአት ክፍያ የሚባለውን የዓመቱ ቅዱስ ቀን" "ዮም ኪፖር" በጸሎት እና በመዝሙር ለማክበር ከ 70 የሚልቁ ወንዶች እና ሴቶች አይሁዳውያን በተሰባሰቡበት ሙክራብ ደጃፍ አንድ የልዩ ኃይል ልብስ የለበሰ የብረት ኮፍያ ያጠለቀ እና ከባድ ጦር መሣሪያ የታጠቀ ጀርመናዊ ወጣት ባደረሰው ጥቃት የሁለት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ በጀርመን ነዋሪ የሆኑ አይሁዳውያን በሙክራቦቻቸው ዕምነታቸውን ያለስጋት በነጻነት ለማከናወን አሁንም ከፍተኛ ስጋት በሕይወታቸው ላይ መደቀኑን ጉልህ አመላካች ነው ስትል ፖል ገልጻለች።
ጥቃት ፈጻሚው እየተኮሰ የሙክራቡን በር ሰብሮ ወደ ውስጥ ለመዝለቅ ሙከራ ማድረጉንም የደህነት ካሜራዎች አረጋግጠዋል:: ከ 50 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡበት ልክ እንደ ኒውዝላንዱ የሽብር ክስተት ትላንት በሃለ ከተማ የተኩስ ጥቃት የፈጸመው ጀርመናዊው ወጣት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተኩስ እሩምታ ከመክፈቱ አስቀድሞ በአንድ ድረ ገጽ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ባስተላለፈው መልዕክት "ለምድራችን ችግሮች ሁሉ ዋንኛ መንስኤዎቹ አይሁዳውያን ናቸው" የሚል ፀረ-ሴማዊ ውንጀላ ማቅረቡ ታውቋል:: እንደ ፖል አስተያየት በዛሬው ዕለት ሁኔታውን ለመቆጣጠር የተወሰደው እርምጃ አንዳንድ መሻሻሎችን ባያሳይ ኖሮ ጀርመን ውስጥ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በርካታ አይሁዳውያን ላይ የጅምላ ግድያ ተፈጽሞ እናይ ነበር ስትል አደጋው የደቀነውን ከፍተኛ ስጋት ገልጻለች::
ኢናስ ፖል አስተያየቷን በመቀጠል ትላንት የተፈጸመው ጥቃት የሚያስገነዝበው ነገር ቢኖር በጀርመን ከጊዜ ወደ ጊዜ በአስጊ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የአይሁዳውያን ጥላቻ ወይም ፀረ-ሴማዊነት ጥቃት ለመከላከል እና የእስላማዊ አሸባሪዎችን እንቅስቃሴ ለመግታት የሚደረገው ጥረት አናሳ መሆኑን ነው ብላለች:: ከዚህ ውጭ አሁን ላይ ችግሩን መቆጣጠር ከሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል የሚል ማንኛውም ወገን ቢኖር አንድም እየዋሸ ነው አልያም ፈጦ የሚታየውን ዕውነታ ፊት ለፊት ለመጋፈጥ ድፍረቱን ያጣ ብቻ ነው ብላለች ፖል::
የ DW ዋና አርታኢ ፖል እንዳለችው ክስተቱ አሁንም በጀርመን ለሚገኙ የአይሁዳውያን ተቋማት ልዩ ጥበቃ እንደሚያስፈልግ ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ ቢሆንም እንደ "ዮም ኪፖር" ያሉት የአይሁዳውያን ልዩ ቅዱስ በዓላት በሚከበሩባቸው ቀናት አንዳችም የፖሊስ ጥበቃ አለመደረጉ በራሱ ጥያቄን የሚያጭር ጉዳይ ነው። በአይሁዶች ጥላቻ ወይም ፀረ-ሴማዊነትን ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቅን ጉዳዮች ሳይቀሩ ልዩ ትኩረት እየተሰጣቸው ክትትል እና ምርመራ እንዲደረግባቸው የሚጠቁም የማንቂያ ደውል መሆኑንም በዘገባው ተብራርቷል:: እንደ ፖል እምነት ከጥላቻ ጥቃቶቹ መካከል የእስራኤልን ሰንደቅ ዓላማ ማቃጠል እና ጭንቅላታቸው ላይ እንደሚያደርጉት ባርኔጣ ወይም "ኪፓ " ያሉ የእምነት መገለጫዎች ማዋረድን የሚያጠቃልል ነው:: በዘገባዋ ማጠቃለያም የፀረ- ሴማዊነት ጥላቻ በየትኛውም ዓለም በተለይም እንደ ጀርመን ባሉ አገራት በቸልታ መታየት እንደማይኖርበት አስተያየቷን ሰጥታለች::
የዶቼ ቨለ DW ዋና አርታኢ ኢነስ ፖል
እንዳልካቸው ፈቃደ