ጦርነቱ በትግራይ ላደረሰዉ ኪሳራ ልዩ የድጋፍ ማዕቀፍ ያስፈልጋል መባሉ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 13 2015በትግራይ የደረሰው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ለማካካስ ልዩ የድጋፍ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ የትግራይ ኢንቨስትመንት ኮምሽን ገለፀ። በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያደረሰው ጫና የሚዳስስ ሀገራት ኮንፈረንስ ዛሬ በመቐለ ተካሂዷል። ጦርነቱ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተለየ ደግሞ በትግራይ ከፍተኛ ጉዳት መፍጠሩ በመድረኩ የተገለፀ ሲሆን በድህረ ጦርነት ወቅትም ቢሆን አመርቂ ለውጥ እየታየ አለመሆኑ ከትግራይ ነጋዴዎች በኩል ተገልጿል።
ጦርነቱ በትግራይ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያደረሰው ጫና የሚዳስስ ሀገራት ኮንፈረንስ በመቐለ እየተካሄደ ውሏል። በዓለምአቀፉ የግል ኢንተርፕራይዞች ማእከል ወይም CIPE እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰላም ሚኒስቴር እና የትግራይ የንግድ ዘርፍ ማሕበራት ምክርቤት አስተባባሪ የተዘጋጀው ይህ ኮንፈረንስ፥ ከሁለት ዓመት የጦርነት ግዜ በኃላ የተፈጠረው የሰላም ዕድል በጦርነቱ የወደመው ኢኮኖሚ መልሶ ለመገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
በመድረኩ የተገኙት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ በጦርነቱ ምክንያት ተዘግተው የነበሩ ትግራይን ከተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል የሚያገናኙ መንገዶች እንዲከፈቱ እና ድህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን መሰራት አለበት ያሉ ሲሆን በመንገዶቹ ተዘግቶ መቆየት አትራፊ ሊሆኑ የሚችሉ አካላት አደብ ማስገዛት እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል። በጦርነቱ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊ እና ሰብአዊ ኪሳራ መድረሱ ያነሱት የኢትዮጵያ ሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ታየ ደንድአ በበኩላቸው የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ኪሳራውን ማስቆም የቻለ ታሪካዊ ስኬት መሆኑ አንስተዋል። "በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የዚህ አደገኛ አስቸጋሪ ጦርነት አካል በመሆኔ ጥልቅ ህመም ይሰማኛል" ያሉት አቶ ታየ ደንድአ፥ አሁን ላይ ሁኔታዎች መቀየራቸው ግን ትልቅ ስኬት መሆኑ ገልፀዋል።
ጦርነቱ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተለየ ደግሞ በትግራይ ከፍተኛ ጉዳት መፍጠሩ በመድረኩ የተገለፀ ሲሆን በድህረ ጦርነት ወቅትም አመርቂ ለውጥ እየታየ አለመሆኑ ከትግራይ ነጋዴዎች በኩል ተገልጿል። የንግድና ኢንቨስትመንት ስራዎች የሚያግዙ ማበረታቻዎች ከመንግስት አለማግኘት፣ ፀጥታ እና ድህንነት አለመረጋገጥ፣ ብድር ጨምሮ የተለያዩ ማካካሻዎች ማጣት በትግራይ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት ፈተና ሆነው እንዳሉ ተመላክቷል። የትግራይ ኢንቨስትመንት ኮምሽን በትግራይ ያለው ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለማቃለል የፌደራል መንግስቱ ለትግራይ 'የተለየ የድጋፍ ማዕቀፍ' ማመቻቸት ይገባዋል ብሏል።
ዛሬ በመቐለ እየተካሄደ ባለ የድህረ ጦርነት የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ማነቃቂያ መድረክ የኢትዮጵያ ሁሉም ክልሎች የንግድ ቻምበር ማሕበራት ተወካዮች፣ የግል ሴክተር የንግድ አንቀሳቃሾች፣ ኢንቨስተሮች፣ የንግዱ ዘርፍ ባለስልጣናት እና የዓለምአቀፍ ተቋማት ተወካዮች ታድመዋል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ