ጀርመን የተዘረፉ ቅርሶችን ለናይጀሪያ መመለስ ጀመረች
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 14 2015በጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ባርቦክ የተመራዉ ከፍተኛ የጀርመን ልዑካን ቡድን በናይጀሪያ ዋና መዲና አቡጃ፤ በተካሄደዉ እና «ታሪካዊ» በተባለዉ ሥነ-ስርአት ላይ ከ 120 ዓመት በፊት በእንጊሊዝ ቅኝ ግዛት ዘመን የተዘረፉ ቅርሳ ቅርሶችን መልሰዋል። በርግጥ የጀርመንዋ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌላ ቤርቦክ እንደተናገሩት በጀርመን ሙዚየሞች የሚገኙት በቤኒን ሥርወ-መንግሥት ዘመን የተሰሩት ቅርሳ ቅርሶች የባህልና የቅርስ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የማነት ጉዳይም ነዉ። ሚኒስትሯ አቡጃ ላይ ከናይጀሪያዉያን ባለስልጣናት ፊት ለፊት ቆመዉ እንደተናገሩት ዛሬ እዚህ የመጣነው የቤኒን ነሐስ ቅርሶች ባለቤት ለሆነዉ ለናይጀሪያ ህዝብ ለመመለስ ነው፤ የመጣነዉን ስህተቱን ለማስተካከል ነዉ።ወደ አፍሪቃ የተመለሱ ቅርሶች ዳግም ላለመሰረቃቸዉ ምን ማስተማመኛ አለ?
«ናይጀርያን ለመጎብኘት ዛሬ ወደዚህ ስንመጣ የቢኒን ቅርሳ ቅርሶችንም ይዘን መምጣታችን ጥሩ እርምጃ ነዉ። በናይጀርያ ሲጠበቁ የነበሩት ቅርሳ ቅርሶች በስተመጨረሻ መቀመጥ ወደሚገባቸዉ ቦታ ወደ ናይጀርያ ይዘን መጥተናል። ይህን የነሐስ ቅርስ መዘረፉ ስህተት ነበር። ይህ የመዳብ ቅርሳ ቅርስን ለባለቤቱ ሳይመልሱ ይዞ መቀመጥም ስህተት ነበር። ቅርሱን ለመመለስ ሁለቱ ሃገራት ያደረጉት እርምጃ ሃገራቱ አሁን ለሚያካሂዱት የትብብር ስራ እጅግ አስፈላጊ ነዉ። ቅርሱ መመለሱ ለናይጀርያ ህዝብ የባህል እና የቅርስ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የማንነት ጥያቄም በመሆኑ ነዉ። ስለዚህ ሁለቱ ሃገራት ለዚህ ዉሳኔ አብረዉ መስራታቸዉ አስፈላጊ ነበር።»
በጎርጎረሳዉያኑ 1897 ዓ.ም በብሪታንያ ቅኝ ገዥዎች የተዘረፉና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ሙዚየሞች ከተሸጡት መካከል 22 ከነሐስ የተሰሩ እጅግ ውድ የሆኑት ቅርሳ ቅርሶች ወደ ናይጀርያ የመመለሳቸዉ የጅማሮን እለትን «ታሪካዊ ቀን» ሲሉ አቡጃ ላይ የተናገሩት የጀርመን የባህል ሚኒስትር ክላውዲያ ሮት «የእኛ ያልነበርነውን መመለስ እንፈልጋለን» ሲሉ ተናግረዋል።
የሥነ ጥበብ በታሪክ ዉስጥ ይኖራል፤ ታሪክም በሥነ ጥበብ ዉስጥ ይኖራል ያሉት የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ፤ ሥነ ጥበብ ራሳችንን ብሎም ዓለምን የምናይበትን ምናብ የሚገልጽ ነዉ ሲሉ ተናግረዋል። በጀርመን የሚገኙ የቤኒን የነሐስ ቅርሶች ገና ተመልሰዉ እንዳላለቁም አክለዋል።
«ይህን የመጀመርያ ዉሳኔ የመጀመርያ እርምጃ ብለን ነዉ የምንይዘዉ። ምክንያቱም ሌሎች ገና ናይጀርያ ያልገቡ እና ተሰርቀዉ የነበሩ በርካታ የነሐስ ቅርሳቅርሶች አሁንም እጃችን አሉ። እነዚህ ባህላዊ ቅርሳቅርሶች ወደ ናይጀርያ ይመለሳሉ። ለዚህም ሁለቱ ሃገራት በትብብር ይሰራሉ። በሌላ በኩል ያለፈዉን እና የራሳችን የነበረዉን ጥቁሩን የቅኝ ግዛት ታሪካችንን ለማረም እና በናይጀርያ እና በጀርመን መካከል መካከል አዲስ እና ጥልቅ የሆነ የጋራ ትብብር ምዕራፍን ለመክፈት አስፈላጊ እርምጃ ነዉ።»
ለናይጀርያ የተመለሱት እና በቤኒን ሥርወ መንግሥት ዘመን የተሰሩት እና ውድ የሆኑት ቅርሳ ቅርሶች በጀርመን በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ በርካታ ቤተ መዘክሮች ውስጥ ከሚገኙ 1,130 የተዘረፉ ባህላዊ ኃብቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። ቅርሳቅርሶቹ ከነሐስ፣ ከዝሆን ጥርስና ከመዳብ እና ከሌሎች ውድ ቁሳቁሶች የተሠሩት የናይጀርያ ብሎም በአፍሪቃ አህጉር የሥነ ጥበብ ዉጤቶች ናቸዉ።
የናይጀሪያ የማስታወቅያና የባህል ሚኒስትር አልሃጂ ላይ መሐመድ በርክክቡ እለት ባደረጉት ንግግር «እነዚህን የናይጀርያ ጥንታዊና ባህላዊ ከነሐስ የተሰሩ ቅርሳቅርሶች ከሃያ ዓመት በፊት፣ ሌላው ቀርቶ ከዛሬ 10 ዓመት በፊት፣ ወደ ናይጀሪያ ይመለሳሉ ብሎ የጠበቀ አልነበረም። ምክንያቱም ቅርሶቹን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የነበረዉ እንቅፋት እና መሰናክል መልስ የሚያገኝ አይመስልም ነበር። ይሁንና ዛሬ፣ በወዳጅ አገር፣ ጀርመን፣ ቅን አሳቢነት ታሪኩ ተቀይሯል» ሲሉ ተናግረዋል።
በዋሽንግተን ዲሲ የሲምሶንያን የተፈጥሮ ሳይንስ ሙዝየም ተመራማሪ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ዮሐንስ ዘለቀ እንደሚሉት ጀርመን ጥንታዊ የሆነዉን ለናይጀርያ መመለስዋ የሚያስደስት ርምጃ ነዉ።
ከአፍሪቃ የተዘረፉ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶችናይጄሪያ ከጀርመን የተመለሱትን የመጀመሪያዎቹን የነሐስ ቅርሳቅርሶች በተመለከተ ከሁለት ሳምንታት ገደማ በኋላ በሚገባዉ በፈረንጆቹ 2023 ዓም መጀመሪያ ላይ አዉደ ርዕይ በመክፈት በትልቁ እንደምታከብር ተነግሯል። ኤግዚቢሽኑ «የተመለሰዉ የታሪካችን ክፍል፤ የማንነታችን አካል የሆነዉን ቅርሳችንን ናይጄሪያውያን እንዲያዩ ያስችሏቸዋል» ሲሉ የናይጄሪያ ብሔራዊ የሙዚየሞችና የሐውልቶች ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር አባ ኢሳ ቲጃኒ ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ ሁኔታዉ እጅግ ስሜታዊ የሚያደርግ ነዉ ሲሉም አክለዋል። በዋሽንግተን ዲሲ የሲምሶንያን የተፈጥሮ ሳይንስ ሙዝየም ተመራማሪ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ዮሐንስ ዘለቀ፤ የቤኒን ቅርሶች ማለት ምን ማለት እንደሆን ጠይቀናቸዋል።
ከጀርመን ለናይጀርያ የተመለሱት ጥንታዊ ቅርሶች በጀርመን በርሊን፤ ሃምቡርግ፤ ኮሎኝ፤ ድሬስደን፤ ላይፕሲግ እና ሽቱትጋርት ከተሞች በሚገኙ ሙዚየሞች ውስጥ ለዓመታት የተቀመጡ ነበሩ። እነዚህ ሙዚየሞች ባለፈዉ ሰኔ ወር የያዝዋቸዉን የቤኒን የነሐስ ቅርሶች ሁሉ ለመጀመርያ ጊዜ የባለቤትነት መብትን አዛወሩ። ቅርሶቹ ወደ ናይጀርያ እስኪመለሱ ድረስ በሙዚየሞቹ ዉስጥ ለእይታ እንዲቀርቡ አንዳንድ ስምምነት ላይም ተደርሷል። ጀርመን ለናምቢያ የመለሰችዉ ቅርስና ዉዝግቡ
ባለፈው ሳምንት በጀርመን የኮሎኝ ከተማ 92 የቤኒን የነሐስ ቅርሶችን በጀርመን ለሚገኙት ለናይጄሪያ አምባሳደር ለአባ ኢሳ ቲጃኒ እና ዩሱፍ ማይታማ ቱግጋር ካስረከበ በኋላ አምባሳደሮቹ በጀርመን የተለያዩ ከተሞች የሚገኙትን ቅርሶች ለመሰብሰብ ጉዞን ጀምረዋል።
የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ሌሎች የጀርመን ባለስልጣናት ባለፈዉ ማክሰኞ አቡጃ ናይጀርያ ላይ በተካሄደዉ የርክክብ ሥነ ስርዓት ላይ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቤርቦክ እንደተናገሩት አገሬ ጀርመን በቅኝ ግዛት ዘመን የተዘረፈ ቅርሳ ቅርስ መሆኑን እያወቀች በገንዘብ ገዝታለች፤ ከተገዛም በኋላ እቃዉ የናይጀርያ መሆኑ እየታወቀ ለረጅም ዓመታት ሳይመለስ ተይዞ መቀመጡ ስህተት ነዉ፤ ሲሉ ተናግረዋል። ይህ ደግሞ በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት ጨለማ ሚና የነበረዉን የአዉሮጳ የቅኝ ግዛት ታሪክን የሚያሳይ ነዉ።
«በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለዉ የባህላዊ የትብብር ስራ በናይጀርያዋ ቤኒን ከተማ ቅርሳቅርሶቹ ለእይታ የሚቀርቡበት የአዉደ ርዕይ ማሳያ ቦታ ተገንብቶ ለናይጀርያ ህዝብ ብሎም ከዓለም ሃገራት ታሪኩን ለማጥናት ለሚፈልጉ ለተማሪዎች እና ለታሪክ ተመራማሪዎች ክፍት እንዲሆን እንሰራለን።» በቅኝ ግዛት ዘመን ከተለያዩ አፍሪቃ ሃገራት ወደተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት ተዘርፈዉ የወጡ ቅርሳቅርሶች ዘራፊዎቹ ሃገራት ከመመለስ ባለፈ ካሳ ሊከፍሉ ይገባል የሚል አስተያየት ሲሰጥ ይሰማል፤ ይህ እንዴት ይታይ ይሆን። ዶ/ር ዮሃንስ ዘለቀ ሰፋ ያለ መልስ ሰጥተዋል። ለተዘረፉ ቅርሳ ቅርሶች ካሳ መጠየቅ ስህተት የለዉም ብለዋል።
ሙሉ ጥንቅሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ