1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ወዳጅነቷን ከማሊ ወደ ጎረቤት ኒጀር

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 7 2015

የጀርመን መንግሥት ወታደሮቹን ለዓመታት ለሰላም ማስከበር ተልእኮ በሚል ካሰፈረባት ማሊ በማስወጣት ዐይኑን ወደ ጎረቤት ኒጀር አማትሯል ። ከቻድ ጋርም ዲፕሎማሲያዊ አተካራ ውስጥ ገብቷል ። ጀርመን ሙሉ ለሙሉ ጓዙን ሸክፎ ከአካባቢው ይወጣል ማለት ግን አይደለም ። የልማት ሚንሥትሯ ስቬንያ ሹልትስም ያረጋገጡት ይህንኑ ነው ።

https://p.dw.com/p/4Q5xX
Mali Gao | Verteidigungsminister Boris Pistorius und Entwicklungsministerin Svenja Schulze
ምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

ጀርመን ከማሊ ወደ ኒጀር

የጀርመን የልማት እና የመከላከያ ሚንሥትሮች ስቬንያ ሹልትሰ እና ቦሪስ ፒስቶሪዩስ ምእራባዊ ሠሐራ ወደሚገኘው «ካምፕ ካስትሮ» ወታደራዊ ጦር ሠፈር ሲደርሱ የፀጥታ ጥበቃው እጅግ ጥብቅ ነበር ። ሥፍራው ፀጥታዋ አስተማማኝ ካልሆነችው ማሊ በስተሰሜን ሲል ጋዖ ውስጥ የሚገኘው የጦር ሠፈር ነው ። ሁለቱ የጀርመን ሚንሥትሮች በጋራ ሲጓዙም የመጀመሪያቸው ነው ።  የጀርመን ወታደሮች እጅግ አደገኛ በሆነ ተልእኮ ውስጥ እንደሚገኙም ለማመላከት ነው የጋራ ጉዞው ። ሁለቱም ማስስተላለፍ የፈለጉት፦ ያለ ፀጥታና መረጋጋት ልማት እውን ሊሆን እንደማይችል፤ ያለ ልማትም ፀጥታ እና ደኅንነት ትርጉም አልባ መሆኑን ማስረገጡን ነው ። በእርግጥ በቀጣዩ ዓመት ግንቦት ወር ላይ የጀርመን ፌዴራል መንግሥት ወታደሮቹን ከማሊ ጠቅልሎ ማስወጣት ይሻል ። እስከዚያ ድረስም በጦር ሠፈሩ በበርካታ ግዙፍ የብረት ሠንዱቆች የተከማቹ የጦር ጓዱ ቁሶችን ይሰበስባል ። ጀርመን ሙሉ ለሙሉ ጓዙን ሸክፎ ከአካባቢው ይወጣል ማለት ግን አይደለም ። የልማት ሚንሥትሯ ስቬንያ ሹልትስም ያረጋገጡት ይህንኑ ነው ።

«ሀገሪቷ ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ እዚህ አለን ። እዚህም ከወታደራዊ የደኅንነት ጉዳዮች ጋር በተገናኘ በጋራ እየሠራን ነው ። እዚህ ያለው ኤምባሲያችን በግልፅ ማስተላለፍ የሚፈልገው ወታደራዊ ተሳትፏችን ቢጠናቀቅ እንኳ የጋራ ልማት ሥራችን የሚቀጥል መሆኑን ነው ። ወደፊትም እዚህ መሆን እንፈልጋለን ።»

ማሊ እስልምና አክራሪ ታጣቂዎች የሚርመሰመሱባት እና በሣኅል ቀጣናም የሽብር ጥቃት ለመፈጸም የሚንደረደሩባት ናት ። ይህ ስፍራም ራሱን «እስላማዊ መንግሥት» ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን እና አል ቃይዳ የሀገር ውስጥ ቅርንጫፎች የሚፈልቁበት ነው ። የጂሃድ ተዋጊዎቹ በቃላት ለመግለጥ የሚከብዱ ጥፋቶችን ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ ይፈጽማሉ፤ኅብረተሰቡ ላይ ያሰፈኑት ሥጋትም እንደቀጠለ ነው ። ያ በመሆኑም በዐሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ስደት እንዲገቡ፤ ረሐብ እና መከራ ማሊ ውስጥ እና በአጠቃላይ ቀጣናው እንዲንሰራፋም ሰበብ ሆኗል ።  

በዚህ ሁሉ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የፌዴራል ጀርመን ወታደሮች ኅብረተሰቡን ሲጠብቁ ለሀገሪቱ መረጋጋት ለቃጣናው ደኅንነት ሲጥሩ ነበር ። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘርፈ-ብዙ የተቀናጀ ማሊን የማረጋጋት ተልእኮ(MINUSMA) የሰላም አስከባሪ ጓድ ስርም  1100 የጀርመን ወታደሮች  ማሊ ከከተሙ ዓመታት ተቆጥሯል ። በዘመነ-መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የጀርመን ወታደሮች ማሊ የሰፈሩት በቀጣናው ሦስት ጉዳዮች ማለትም፦ ደኅንነት፤ ልማት እና ፍልሰትን መታገል ላይ በማተኮር ነበር ። ካለፉት ጥቂት ወራት አንስቶ ግን የጀርመን መከላከያ ይህን የማሊ ተልእኮ ማሟላት ተስኖታል ። እንደ ጀርመን መከላከያ ሚንሥትር ቦሪስ ፒስቶሪዩስ ምክንያቶቹ ዘርፈ ብዙ ናቸው ።  

«ተልእኮው በዚህ መልኩ ፍጻሜውን ማግኘቱ ያሳዝነኛል ። ምክንያቱም ዛሬም በንግግሮቻችን ግልጽ የሆነልን አንዳች መስቀለኛ መንገድ ላይ መገኘታችን ነው ። ማሊ ውስጥ ሁኔታዎች አልተሻሻሉም ። እንዲያም ሆኖ ተልእኮዋችን አይደለም የተሰነካከለው፤ ሁኔታዎች ናቸው ተልእኮውን እንዲደናቀፍ ያደረጉት ። ያ የሆነው በጀርመን ፖለቲካ አይደለም፤ በእርግጠኝነት ጥፋቱ የጀርመን ወታደሮችም አይደለም ።» 

የማሊፕሬዚደንት ዓሲሚ ጎይታ የሩስያ ወታደሮችን ወደ ማሊ አስገብተዋል
የማሊፕሬዚደንት ዓሲሚ ጎይታ የሩስያ ወታደሮችን ወደ ማሊ አስገብተዋል ምስል French Army/AP/picture alliance

በእርግጥ የማሊ መንግሥት ምእራባውያን ወደ ሀገሪቱ መጥተው ሰላም እንዲያሰፍኑ ከተማጸነ ዐሥር ዓመት አልፎታል ። ሆኖም ባለፉት ዐሥር ዓመታት በማሊ ከሁለት መፈንቅለ መንግሥታት በኋላ በርካታ ነጎሮች ተቀይረዋል ። የ40 ዓመቱ የማሊ ፕሬዚደንት ዓሲሚ ጎይታ እና እሳቸው የሚመሩት ወታደራዊ ሁንታ አዲስ ወዳጅ አበጅተዋል ። ምእራባውያንን ትተውም ከሩስያ ጋር ተወዳጅተዋል ። ዓሲሚ ጎይታ በእየ ጊዜው ራሳቸውን ከምእራባውያን እያራቁ ነው ። እናም ፕሬዚደንቱ «ቫግነር» የተባለውን የሩስያ የግል ወታደራዊ ኩባንያ ወታደሮች ወደ ማሊ ጋብዘዋል ።

ማሊ 23 ሚሊዮን ነዋሪዎች ያሏት ደሀ ከሚባሉት የምትመደብ ሀገር ናት ። አብዛኞቹ ነዋሪዎቿም በድሕነት አረንቋ ውስጥ ይማቅቃሉ ። 8,8 ሚሊዮን የማሊ ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት የሰብአዊ ድጋፍ የሚያሻቸው ናቸው ። የጀርመን መንግሥት በማሊ ወታደራዊ ተልእኮው መገባደጃው ቢቃረብም በልማት እና በሌሎች ጉዳዮች ትብብሩን ለማስቀጠል ግን ቃል ገብቷል ። ዐይኖቹንም ወደ ሌላኛዋ በሣኅል ቀጣና የምትገኝ ደሃዪቱ ሀገር ኒጀር አማትሯል ። እንደ ልማት ሚንሥትር ስቬንያ ሹልትሰ ከሆነ የጀርመን መንግሥት በትምህርት፤ በጤና፤ በንጹሕ ውኃ አቅርቦትና በመሳሰሉት ዘርፍ ከኒጀር ጋር መሥራት እንደሚሻ ተናግረዋል። የጀርመን መንግሥት ማሊን ለሩስያ ትቶ ግን ከቀጣናው ሙሉ ለሙሉ መውጣቱን የሚሻ አይመስልም ።  በሣኅል ቀጣና መረጋጋትን ለማስፈን የጀርመን መንግሥት ኒጀርን ማጠናከር እንደሚሻ ገልጧል።

የጀርመን መንግሥት ዐይኖቹን ከማሊ ወደ ሌላኛዋ በሣኅል ቀጣና የምትገኝ ደሃዪቱ ሀገር ኒጀር አማትሯል
የጀርመን መንግሥት ዐይኖቹን ከማሊ ወደ ሌላኛዋ በሣኅል ቀጣና የምትገኝ ደሃዪቱ ሀገር ኒጀር አማትሯል

ያም ብቻ አይደለም፦ ከማሊ ባሻገር ኒጀርን በስተምሥራቅ የምትጎራበተው ቻድ እና ጀርመንም ዲፕሎማሲያቸው መልካም አይመስልም ። ቻድ የጀርመን አምባሳደር «ለዲፕሎማሲው ክብር የላቸውም» ስትል በሁለት መስመር ትእዛዝ ከሀገሯ እንዲባረሩ ከወሰነች በኋላ የጀርመን መንግሥትም በአጸፌታው የቻድ አምባሳደር ከሀገር እንዲወጡ ማክሰኞ ዕለት ማዘዙ ተዘግቧል ።  የጀርመን አምባሳደር ከቻድ የተሰናበቱት የሰላ ትችት በመሰንዘራቸው ነው ሲል የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አትቷል ።  የጀርመን ውሳኔ ደግሞ የተከተለው የቻድ ድርጊት «ምክንያታዊ አይደለም» በሚል ነው ። በስተ ምእራብ ማሊ፤ በስተ ምሥራቅ ቻድን የተጎራበተችው ኒጀር ለጀርመን በእርግጥም ልዩ ትኩረትን የምትሻ ናት ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ