ጀርመን አዲስ ፕሬዚዳንት መረጠች
እሑድ፣ የካቲት 5 2009ማስታወቂያ
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር 12ኛው የጀርመን ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ። ዛሬ በበርሊን ከተማ በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሽታይንማየር 931 ድምፅ በማግኘት ምርጫውን በመጀመሪያው ዙር አሸንፈዋል። ምርጫውን በአንዱ ዙር ለማሸነፍ ተመራጩ 631 ድምፅ ማግኘት ይገባዋል። ሶሻል ዴሞክራቱ ሽታይንማየር በሌሎች የጀርመን የፖለቲካ ፖርቲዎች ገና ከምርጫው በፊት ድጋፍ አግኝተዋል። በጀርመን ፕሬዚዳንቱን የሚመርጡት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ቡንደስታግ)ተመራጮች እና የጀርመን ግዛቶች ተወካዮች ናቸው። ከእነዚህ መካከል ታዋቂ አርቲስቶች እና ስፖርተኞች ይገኙበታል። እንደሚያሸንፉ ሲጠበቁ የነበሩት ሽታየንማየር ምርጫውን በደስታ ተቀብለዋል። ወቅታዊው የጀርመን ፕሬዚደንት ዮአኺም ጋውክ የስልጣን ዘመን ከአምስት ዓመት በኋላ መጋቢት 8 ቀን 2009 ዓም ያበቃል። የ 77 አመቱ ጋውክ በእድሜያቸው ምክንያት ዳግም ለምርጫ መወዳደር ሳይፈልጉ ቀርተዋል።
ልደት አበበ
ማንተጋፍቶት ስለሺ