1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ፤ ሊዮፓርድ 2 ታንኮችን ለዩክሬን ለመስጠት ያለመዉ ስብሰባ

ዓርብ፣ ጥር 12 2015

የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን የኔቶ አባል ሀገራት የመከላከያ ሚንስትሮች እና ሌሎች ደጋፊ ሃገራት ሊዮፓርድ 2 የተሰኘዉን የጀርመንን ታንኮች በሩሲያ ጥቃት ወደተሰነዘረባት አገር ለዩክሪይን ለመስጠት ጀርመን ላይ እየመከሩ ነው። ወደ 50 አገሮች በሚካፈሉበት ይህ ስብሰባ ላይ የጀርመን የአሜሪካ እና የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትሮች ተካፋይ ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/4MWSm
Deutschland | Ramstein-Treffen zum Krieg in der Ukraine
ምስል Wolfgang Rattay/REUTERS

 

የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን የኔቶ አባል ሀገራት የመከላከያ ሚንስትሮች እና ሌሎች ደጋፊ ሃገራት ለዩክሬን ጦር ሰራዊት ተጨማሪ ወታደራዊ ቁሳቁስ ለመስጠት በጀርመን በሚገኘው ራምሽታይን የዩናይትድ ስቴትስ የአየር ኃይል ሰፈር ለመወያየት ስብሰባ ተቀምጠዋል።  የስብሰባው ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ ሊዮፓርድ 2 የተሰኘዉን የጀርመንን ታንኮች በሩሲያ ጥቃት ወደተሰነዘረባት አገር ለዩክሪይን ለመስጠት ነው። ወደ 50 አገሮች በሚካፈሉበት  በዚህ ስብሰባ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚኒስትር  ሎይድ ኦስቲን፣ አዲስ የተሾሙት  የጀርመን አቻቸዉ  ቦሪስ ፒስቶሪየስ እና የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር ኦሌክሲ ሬስኒኮፍ ይገኙበታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ጀርመን ሊዮፓርድ ሁለት የተሰኘዉን ታንኳን እንድትሰጥ ከዩክሬይን የሚገደረዉ ከፍተኛ ግፊት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ነዉ።ሊዮፓርድ 2 የተባለዉ ታንክ ለዉግያ በጣም የሚመረጥ እና በብዛትም የሚገኝ መሆኑ ነዉ የተመለከተዉ። ጀርመን ይህን ዘመናዊ ታንኳን ለዩክሬይን ለመስጠት ማንገራገርዋ ታንኩን ከዚህ ቀደም ከጀርመን የገዙ ለዩክሬይን አሳልፈዉ እንዳይሰጡ የሚያግድ ነዉ ተብሏል። ታዋቂዉን ይህን ታንክ ለዩክሬይን እንዲሰጥ የሚደረገዉ ግፊት እና የጀርመን ማንገራገር ዛሬ ራምሽታይን ጀርመን የአሜሪካ ጦር ሰፍር ላይ እየተካሄደ በሚገኘዉ የመከላከያ ሚኒስትሮች እና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ስብሰባ ላይ ትልልቅ ርዕስ ሆንዋል። የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚኒስትር ልዮድ አዉስቲን የሚመሩት በዚህ ስብሰባ ላይ ዩክሬይንን የሚደግፎ ተካፋዮች የተገኙበት  ሲሆን የዩናይትድ ስቴትሱ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ አዉስቲን እንደተናገሩት ምዕራባዉያኑ ተባባሪዎች ዩክሬንን ለመደገፍ ያቅማቸዉን ሁሉ ማድረግ አለባቸዉ ብለዋል።  

«ይህ ወሳኝ ወቅት ነው። ሩሲያ እንደገና በማደራጀት እና እንደገና ለማስታጠቅ እየሞከረች ነው። አሁን ፍጥነት የሚቀነስበት ጊዜ አይደለም። ጊዜዉ የተቻለዉ ሁሉ የሚደረግበት ነዉ። የዩክሬን ሕዝብ እየተመለከተን ነው ። ክሬምሊንም እየተመለከተን ነው። ታሪክም እየተከታተልን ነው። ስለዚህ ዩክሬንን ከሩሲያ ጥቃት ለመከላከል ከያዝነዉ አቋም እና አንድነት አናፈገፍግም።»

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሜር ዜሌንስኪም በጀርመን ላይ ያደርጉት የነበረውን ጫና ከፍ አድርገዋታል። ፕሬዚዳንቱ ከጀርመን ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ታንኮች በፍጥነት እንዲደርሱ ጥሪ አድርገዋል።

«በቀላል አነጋገር ሌዮፓርዱን ትሰጣላችሁ አትሰጡም። እና እራሳችን ለመከላከል እንጂ ጥቃት ለመሰንዘር አይደለም የፈለግነዉ።» 

የጀርመን የልማት ትብብር ሚኒስትር ስቬንያ ሹልዝ ለዩክሬን ዳግም ግንባታ  ተጨማሪ 52 ሚሊዮን ዩሮ ለመስጠት ቃል ገቡ። ሚኒስትሯ ይህን የተናገሩት  ትናንት የዩክሬይንን የወደብ ከተማ ኦዴሳን በጎበኙበት ወቅት ነዉ። ሚኒስትሯ የኤሌክትሪክ፣ የውኃ እና የሙቀት ኃይል አቅርቦትን መልሶ በመገንባት በጦርነቱ የዩክሬንን ማህበረሰብ የመቋቋም ኃይልን በመደገፍ ረገድ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል። ለዩክሬን ከተሰጠዉ ከዚህ እርዳታ በተጨማሪ ለሚሊዮች የክረምቱን ብርድ ለመቋቋም መማሞቂ ክፍሎች, ጀነሬተሮች, የሕክምና ቁሳቁሶች ርዳታም እንደሚሰጥ ተነግሯል። የጀርመን የልማት ትብብር ሚኒስትር ስቬንያ ሹልዝ  ዛሬ አርብ የዩክሬይን አጎራባች በሆነችዉ የሞልዶቫ ሪፐብሊክ  ስቴፋን ቮዳ የተባለች ከተማን እየጎበኙ መሆኑ ተነግሯል።  

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ