ጀርመን ለዩክሬን ፀረ-አውሮፕላን ታንኮችን እንደምትሰጥ ዐስታወቀች
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 18 2014ጀርመን ጸረ አውሮፕላን ታንኮችን ለዩክሬን እንደምታቀርብ ይፋ አደረገች። የጀርመን መንግሥት ለሣምንታት ሲያቅማማ ከቆየ በኋላ «ጌፓርድ» የተሰኙ ታንኮችን ለዩክሬን እንደሚያቀርብ ያስታወቀው ዛሬ ነው። የጀርመን መከላከያ ሚንሥትር ክርስቲና ላምብሬሽት በጀርመን የራምሽታይን ዐየር ኃይል በመገኘት ባደረጉት ንግግር ይህንኑ አረጋግጠዋል።
«ዩክሬንን ጌፓርድ በተሰኙ ጸረ አውሮፕላን ታንኮች ለመደገፍ ትናንት ወስነናል። ዩክሬን ከምድር የአየር ክልሏን ለመጠበቅ በአሁኑ ወቅት በትክክል የሚያስፈልጋት ያ ነው። ያም እዚህ ግልጽ ኾኗል። ዩክሬንን በዚህ ጀግንነትን በተላላበሰ ግን ደግሞ በዚህ ለነጻነትና ለሰላም ወሳኝ በሆነ ጦርነት መደገፋችንን መቀጠል ይቻል ዘንድ በዛሬው ጉባኤ አማራጮችን በሙሉ እንቃኛለን። ጀርመን ለዚህ ዝግጁ ናት።»
ጸረ አውሮፕላን ታንኮቹ በቀጥታ ከጀርመን መከላከያ የሚላኩ ሳይሆን ሙይንሽን ከሚገኘው ክራውስ ማፋይ ቬግማን(KMW)ከተሰኘው የጀርመን እና ፈረንሳይ የጦር መሣሪያ ቴክኒክ ቡድን መሆኑ ተጠቅሷል። የጀርመን መራኄ-መንግሥት ዖላፍ ሾልትስ ጦር መሣሪያዎችን በቀጥታ ከጀርመን ወደ ዩክሬን ላለመላክ እምቢ በማለታቸው ሲወቀሱ ነበር። እስካሁን ድረስ ፈረንሳይ 40 ኪሎ ሜትር ድረስ የሚምዘገዘጉ ሴዛር መድፎችን ለዩክሬን አቅርባለች። ብሪታንያ በበኩሏ የአየር መቃወሚያ ሚሳይሎችን እና ታንኮችን ሰጥታለች። በዛሬው ደቡብ ምዕራብ ጀርመን ራምሽታይን ዐየር ኃይል በሚካኼደው ጉባኤ የዐርባ ሃገራት ተወካዮች የዩክሬን ጦርን ስለማጠናከር ድንገተኛ ስብሰባ ለማድረግ ተቀምጠዋል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ