1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን አፍሪቃ የልማት ስልት

ቅዳሜ፣ ጥር 20 2015

የጀርመን የልማት ትብብር ሚኒስቴር የአፍሪቃ ሀገራት ተዳሽ የኃይል ምንጮችን እንዲያስፋፉ እና ለወጣቱ ትውልድም አዳዲስ የስራ መስኮችን እንዲፈጥሩ ድጋፍ የመስጠት እቅድ አለው።መስሪያ ቤቱ እንደሚለው ፈጣን የህዝብ ቁጥር እድገት ባላት በአፍሪቃ በየዓመቱ 25 ሚሊዮን አዳዲስ የስራ እድሎች መፈጠር አለባቸው።

https://p.dw.com/p/4MoVZ
Svenja Schulze, Bundesministerin für wirtschaftliche Zusammenarbeit und Entwicklung
ምስል DW

አዲሱ የጀርመን አፍሪቃ የልማት ስልት ፤ የተረሱ የሳህል ሀገራት ቀውሶች

የጀርመን የልማት ትብብር ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በአፍሪቃ ከእስካሁኑ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ሚና መጫወት ይፈልጋል። የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ስቬንያ ሹልዘ በቅርቡ ይህን በሚመለከት አዲስ እቅድ አቀር በዋል። ስቬንያ ሹልዘ ስለ ጀርመንና አፍሪቃ የልማት ትብብር ያቀረቡት እቅድ ከርሳቸው ከቀደሙት ሚኒስትር ቢያንስ ብዙም ያልተጋነነ ተብሏል። የቀድሞው ሚኒስትር ጌርድ ምዩለር ከዛሬ 6 ዓመት በፊት ያቀዱትን የጀርመንና የአፍሪቃ የልማት ትብብር «ማርሻል ፕላን ለአፍሪቃ» ነበር ያሉት።ይህ እቅድ በአመዛኙ መንገድ ላይ እንደወደቀ የሚቆጠር ነው ይላል የዶቼቬለው የዳንኤል ፔልስ ዘገባ ። ከእቅዱ አብዛኛው ከእቅድነት ደረጃ አላለፈም ፣ምዩለርም ራሳቸውን ከፖለቲካ አግለዋል። የአዲሷ ሚኒስትር የስቬን እቅድ ስያሜ « የጀርመን የአፍሪቃ ስልት» ይባላል። እቅዱ ጀርመን ወደፊት ከአፍሪቃ ጋር የሚኖራትን ግንኙነት ቅርጽ የመስጠት  ፍላጎት አለው።ሹልዘ የእቅዳቸውን ዓላማ አስረድተዋል።
«ሀገራቱ በቋሚነት በኛ ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ አንፈልግልም።አዲስ የቅኝ ግዛት  አሰራር መራመድ አንፈልግም።የምንፈልገው ወዳጅነትን መሠረት ያደረገ ግንኙነት ነው።አፍሪቃ እንዴት እያደገች እንደሆነ ፣ምን ያህል የፈጠራ አቅም እንዳላት፣ ምን ያህል ወጣቶችም በአፍሪቃ እንደሚገኙ እየተመለከትን ነው። አንዱ ብቻ ሳይሆን ሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን የሚጠቀሙበትን አሰራሮች እና ወዳጅነትን መገንባት ነው የምንፈልገው።»
 በትብብሩ ስልት ቅድሚያ የሚሰጣቸው አዳዲስ ጉዳዮች አሉ።ከሁሉ አስቀድሞ ዘላቂነት ትልቁን ሚና ይጫወታል። በሚያስገርም ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ በአፍሪቃ ሀገራት የዓየር ንብረት ለውጥ ያስከተላቸው ተጽእኖዎች በግልጽ ይታያሉ።ጀርመን በዚህ ረገድ በአፍሪቃ ኤኮኖሚዎች ማኅበራዊ እኩልነትና አካባቢ ጥበቃ ተኮር ስራዎች እንዲካሄዱ ትፈልጋለች። የጀርመን የልማት ትብብር ሚኒስቴር በጀርመንኛው ምህጻር BMZ የአፍሪቃ ሀገራት ተዳሽ የኃይል ምንጮችን እንዲያስፋፉ እና ለወጣቱ ትውልድም አዳዲስ የስራ መስኮችን እንዲፈጥሩ ድጋፍ የመስጠት እቅድ አለው። የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚለው ፈጣን የህዝብ ቁጥር እድገት ባላት በአፍሪቃ   በየዓመቱ 25 ሚሊዮን አዳዲስ የስራ እድሎች መፈጠር አለባቸው።በጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ግምት በ2050፣ ከዛሬ 27 ዓመት በኋላ መሆኑ ነው፣ የአፍሪቃ ህዝብ ብዛት 2.5 ቢሊዮን ይደርሳል ። 
«ሳውዝ አፍሪካን ኦፊስ ኦፍ ዋን» የተባለው ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ስር የሰደደ ድህነትንና ፣መከላከል የሚቻሉ በሽታዎችን እስከ ዛሬ ሰባት ዓመት ድረስ ለማስወገድ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነው። የድርጅቱ ተንታኝ ኦላውንሚ ኦላ ቡሳሪ በአዲሱ የጀርመንንየአፍሪቃ የልማት ተራድኦ ስልት ውስጥ ቅድሚያ ትኩረት በተሰጣቸው ጉዳዮች ይስማማሉ።  
«አዲሱ የBMZ የአፍሪቃ ስልት ጀርመን ከአፍሪቃ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ ትክክለኛውን መንገድ ያስቀመጠ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ለአፍሪቃ ሀገራት፣ መንግሥታት እና ተቋማት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ቁልፍ ጉዳዮችን አጉልቷል። ስልቱ እያደገ በመሄድ ላይ ላለው፣አፍሪቃ በዓለም ላይ ለምታሳድረው ተጽእኖ እውቅና ሰጥቷል። አፍሪቃውያን ራሳቸው በአጀንዳ 2063 ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ብለው ያስቀመጧቸውን ጉዳዮችን ለመደገፍ ያለመም ነው።»
አዲሱ ስልት የቀድሞው ሚኒስትር ምዩለር የጀርመን ኩባንያዎች በአፍሪቃ በሰፊው እንዲወርቱ ከቀረጹት ማርሻል ፕላን ይለያል። ያኔ እቅዱንም በተለያዩ የድጋፍ መርሃ ግብሮች ለመደገፍ ቃል ተገብቶ ነበር።ሆኖም በጀርመኑ የላይፕሲሽ ዩኒቨርስቲ የአፍሪቃ ጥናቶች የቀድሞ ፕሮፌሰር ሮበርት ካፔል ለዶቼቬለ እንደተናገሩት በዚህ ሃሳብ ውስጥ የኤኮኖሚ ትብብር ዋነኛ ሚና አይጫወትም።
«ከሁሉም በላይ የሚኒስትር ምዩለር ማዕከላዊ ምክንያት በድርጊት መርሃ ግብሩም ላይም ቢሆን  ኤኮኖሚያዊ ትብብር ነበር።በዚህ አስተሳሰብ ደግሞ ኤኮኖሚያዊ ትብብር ምንም ዓይነት ጉልህ ሚና ሊጫወት አይችልም።ሊሆን ይገባ የነበረው ወደፊት ከጀርመን በኩል የምንፈልገው ምን ዓይነት ውረታ ነው የሚለው ነው።የአሁኑ መንግስት እንደቀድሞው በዚህ ጉዳይ ላይ መግፋት ይኖርበታል።»
አሁን ያሉት መርሃ ግብሮች እንደሚቀጥሉ የገለጹት ካፔል በአፍሪቃና በአውሮጳ መካከል የፍትሀዊ የንግድ ግንኙነት እቅድ የለም ብለዋል። ለአፍሪቃ አምራቾች ከባድ ፉክክር የሚያስከትሉት ድጎማ የሚደረግላቸው የአውሮጳ ምርቶች ጉዳይ የአፍሪቃ መንግሥታት በተደጋጋሚ ጥያቄ የሚያቀርቡበት መሆኑንም አስታውሰዋል።  በዚህ ረገድ ብዙ ይጠብቁ እንደነበርም ነው ካፔል የተናገሩት።
የልማት ትብብር  ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የሴቶችን መብቶች ጉዳይ ይበልጥ ማስተዋወቅ በእቅዱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶታል። ይህ በአፍሪቃ ሞቅ ያለ ውይይት ሊያስነሳ የሚችል እንደሆነ ይገመታል።በእቅዱ መሰረት ለጾታ እኩልነት በቀጥታ የሚደረገው አስተዋጽኦ በ2025 በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ93 በመቶ ያድጋል።. መስሪያ ቤቱ በአፍሪቃ ሴቶችና ልጃገረዶች አሁንም አድልዎ እንደሚፈጸምባቸው ጠቅሷል። በመስሪያቤቱ የአፍሪቃ ስልት ላይ «ሴቶችና ልጃገረዶች ጥሩ ትምህርት የማግኘትና የመማር እድላቸው ዝቅተኛ መሆኑን፣የቅጥር ሁኔታቸው ያልተስተካከለና በአብዛኛው ኢ-መደበኛ በሆነ ስራ  እንደተሰማሩ በብዙ የአፍሪቃ ሀገራት ልጃገረዶች ተገደው እንደሚዳሩ በጤና ተቋማት የመታከም የወሊድ መቆጣጠሪያ የማግኘት እድላቸው የተገደበ መሆኑንም ተጠቅሷል።  
አንዳንድ የአፍሪቃ ሀገራት መሪዎች በምዕራባውያን ሀገራት የሚፈጸም የባህል ጣልቃ ገብነት በሚሉት ላይ ለረዥም ጊዜያት ቅሬታቸውን  ሲያሰሙ ቆይተዋል። ለአንዳንድ ተባዕት ፖለቲከኞች ይህ ምዕራባውያን «የእኩልነት መብቶች» የሚሏቸውን ይጨምራል ። ይህም በእቅዱ ለተመሳሳይ ጾታ ጥንዶች የታቀደውንም ድጋፍ የሚመለከት ሊሆን ይችላል ።  ከነዚህ የሹልዘ እቅዶች የትኛዎቹ ክፍሎች እንደሚተገበሩ የሚወሰነው በጀርመን የልማት ትብብር ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ብቻ አይደለም። እቅዱ እንዲሳካ የጀርመን የውጭ ጉዳይ የኤኮኖሚና የመከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችም ድጋፍ ያሻል።

Äthiopien Addis Abeba | Svenja Schulze bei der Afrikanischen Union
ስቬን ሹልዘ አዲe አበባ በሚገኘው የአፍሪቃ ኅብረት ጽህፈት ቤትምስል Mey Dudin/epd
Filmstill Dokumentatio Terror im Sahel - Kampf gegen die Dschihadisten
የሃይማኖት ጦርነት ያወጁ አሸባሪዎች ጋር የሚደረግ ትግል ምስል Inside the Resistance

ቀውሶች ትኩረት የተነፈገባቸው የሳህል ሀገራት 

በዓለማችን የተረሱ የተባሉ ቀውሶች ያሉባቸው ሀገራት ዝርዝር በማገባደድ ላይ ባለነው በጥር ወር ይፋ ሆኗል።  ኬር የተባለው የእርዳታ ድርጅት ባወጣው በዚህ ዝርዝር ውስጥ በተለይ መገናኛ ብዙሀን ትኩረት የነፈጓቸው ሲል ከጠቀሳቸው 10 ሀገራት መካከል ሦስት የሳህል አካባቢ ሀገራት ይገኙበታል ።ድርጅቱ በየዓመቱ በሚያወጣው በዚህ ዝርዝር የጠቀሳቸው ሦስቱ የሳህል ሀገራት ማሊ ኒዠርና ቻድ ናቸው።እነዚህ ከሰራ በታች የሚገኙት የአፍሪቃ ሀገራት በሽብር በጎሳ ግጭቶች እና የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተላቸው ጎርፍና ረሀብ ጋር እየተሰቃዩ መሆኑን የኬር ምክትል ፕሬዝዳንት ክላውድያ ሜናሽ አዉንቴ ያስረዳሉ
«አንዲት የማሊዋ የማዕከላዊ ማፑቶ ግዛት ነዋሪ የተናገረችውን ላካፍላችሁ እፈልጋለሁ።ከ2012 አንስቶ ማሊ ያገጠማት ዘርፈ ብዙ ቀውሶች ባሳደሩት ጫና ማኅበረሰባችን እየተሰቃየ ነው። በተመሳሳይ ጊዜ በኮቪድ 19 ወረርሽኝም ተጠቅተናል። በ2022 በማሊ ላይ የተጣለው የኤኮኖሚ ማዕቀብና የየአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው ተጽእኖ ሁኔታውን ይበልጥ አባብሶታል። በመስከረም 2022 ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ 540 ቤተሰቦችን አፈናቅሏል። ሰብሎች ትምህርት ቤቶች የጤና ተቋማት እና የውኃ መሰረተ ልማት ወድሟል። አነስተኛ ንግዶች ተዘግተዋል።  የምግብ  ዋስትና ቀንሷል። ይህ ሴቶችና ህጻናትን አደጋ ላይ ጥሏል። ያለንን ሁሉ ነው ያጣነው»   ነበር ያሉኝ ይህን የመሰሉ ታሪኮችን ነው የምንሰማውና የምናየው። ይህን የሚሉት በሳህል ሀገራት በቻድ በማሊ እና በኒዠርየሚገኙ በሺህዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ናቸው። »
የሳህል ሀገራት በጎርጎሮሳዊው 2022 የዩክሬኑ ጦርነት ተጽእኖ ያሳደረባቸው ሀገራትም ናቸው።ቻድ ለምሳሌ በምግብ ዋጋ ንረት ምክንያት አስቸኳይ አዋጅ ደንግጋ ነበር።በጦርነቱ ምክንያት የምግብ ዘይት ስኳር አትክልት እና ነዳጅ በጣም ተወዶ ነበር። ከሳህል ሀገራት አብዛኛዎቹ በስፋት ከውጭ የሚገባ ምግብ ጥገኛ ናቸው።ረሀብን ለመከላከል የሚሰራው «አክስዮን ጌግን ዴን ሁንገር» የተባለው የጀርመን የእርዳታ ድርጅት ሃላፊ ያን ሴባስቲያን ፍሬድሪክ ረስት  የዋጋ ንረቱ በእርዳታ አቅርቦቱ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ተናግረዋል። 
«በኛ ስራችን ከዓለም ገበያ ዋጋ ጋር ለተሳሰረው ሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች ላይ የሚደርሰው ተጽእኖ ተለዋዋጭ ነው። ለምሳሌ የነዳጅ ዘይት ዋጋ መጨመር፣ እኛ በምግብ እጥረት ለተጠቁ ህጻናት ህክምና የምንሰጠው የምግብ ዓይነት ዋጋ ከፍ እንዲል አድርጓል። በግልጽ ለመናገር በቀላሉ አንዳንድ ጊዜ እኛ በምግብ እጥረት የተጠቁ ህጻናትን ባለን አቅርቦት ማከም አልቻልንም።»
በተባበሩት መንግሥታት የምግብ መርሃ ግብር ግምት መሠረት በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት በተለይ ከሰሀራ በታች በሚገኙ ሀገራት ተጨማሪ 47 ሚሊዮን ሰዎች ለረሀብ አደጋ መጋለጣቸው አይቀርም።የእርዳታ ድርጅቶች በምዕራብ አፍሪቃ በአስር ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የተባለ የከፋ የምግብ ቀውስ ሊደርስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ያን ሴባስቲያን ፍሬድሪክ ረስት የሳህል አካባቢው የምግብ ችግር መባስ ሌሎች አስከፊ ችግሮችን እያስከተሉ መሆኑን ገልጸዋል። ችግሩ መፍትሄ ካልተፈለገለትም እዳው ለአውሮፓም መትረፉ አይቀርም ይላሉ።    
ያኔ ብቻ ቀውሱ በመገናኛ ብዙሀን መታየት ይጀምራል ብለዋል የኬርዋ አውንቴ ። መገናኛ ብዙሀን  ለጉዳዩ ትኩረት የሚሰጡበት ይህ w።ቅት ግን የብዙ ሰዎች ሕይወት ካለፈ በኋላ መሆኑ ዋጋ አይኖረውም።
ኂሩት መለሰ 
ታምራት ዲንሳ

Filmstill Dokumentatio Terror im Sahel - Kampf gegen die Dschihadisten
የሃይማኖት ጦርነት ያወጁ አሸባሪዎች ጋር የሚደረግ ትግል ምስል Inside the Resistance