1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድርቅ በሸበሌ ዞን በርካታ እንሰሳትን ገደለ

ሐሙስ፣ የካቲት 10 2014

የክልሉ መንግስትም ሆነ ለጋሽ አካላት የተረፉ ሌሎች እንስሳትን እና የህብረተሰቡን ህይወት ለመታደግ የጀመሩት ጥረት ቢኖርም በቂ ባለመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።በዞኑ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ውሀ ፣ ምግብ እና የእንስሳት መኖ ለህብረተሰቡ ለማዳረስ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ድጋፉ በቂ አይደለም ብሏል የክልሉ መንግሥት ። 

https://p.dw.com/p/47BJN
Dürre in Äthiopien Somali Region
ምስል Mesay Teklu/DW

ድርቅ በሸበሌ ዞን በርካታ እንሰሳትን ገደለ

በሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ በርካታ እንስሳቶቻቸው መሞታቸውን የሸቤሌ ዞን ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። የክልሉ መንግስትም ሆነ ለጋሽ አካላት የተረፉ ሌሎች እንስሳትን እና የህብረተሰቡን ህይወት ለመታደግ የጀመሩት ጥረት ቢኖርም በቂ ባለመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። በዞኑ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ውሀ ፣ ምግብ እና የእንስሳት መኖ ለህብረተሰቡ ለማዳረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን  የገለፁት የዞኑ አደጋ ስጋት አመራር ፅ/ቤት የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ አስተባባሪ አቶ አብዲ አህመድ በበኩላቸው ድጋፉ ግን በቂ አይደለም ብለዋል። 
በሶማሌ ክልል ድርቅ ያስከተለውን ጉዳት ለመመልከት በተንቀሳቀስንበት ሸቤሌ ዞን ሀዳዌ ቀበሌ ያገኘናቸው ወ/ሮ እስቡር አብደልኑር በድርቁ ሳቢያ አንድ መቶ አምሳ በግ እና ፍየሎቻቸው መሞታቸውን ገልፀዋል።"ሀዳዌ ከተባለው ቀበሌ ጠዋት ነው የተነሳሁት ። አሁን አብረውኝ ያሉት ፍየሎች አምሳ ናቸው።ከድርቁ በፊት የነበሩኝ ግን ሁለት መቶ ነበሩ ። አንድ መቶ አምሳዎቹ ሞተዋል። የቀሩት ሃምሳዎቹም በሞት መንገድ ላይ ነው ያሉት ምክንያቱም በጣም ከስተዋል ፤ ተጎድተዋል። እንደምታየው የእንስሳት መኖ የሚባል ነገር የለም ። በእርግጥ ለገጠመን ችግር በትንሹም ቢሆን ድጋፍ ማግኘት ጀምረናል ይሁን እንጂ በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግልን እንጠይቃለን።"አቶ አብዱረዛቅ የተባሉ ነዋሪም በድርቁ ከሃያ በላይ ላሞችና አምስት አህያ እንደሞተባቸው ተናግረዋል።"በአጠቃላይ በእንስሶቻችን ላይ የገጠመን ጉዳት ተከፋፍሎ የሚታይ ነው። በላሞች ፣ በግ እና ፍየል እንዲሁም አህያ እና ግመል። ከእነዚህ ከግመል በስተቀር የተረፈ የለም ። የእኔን ቤተሰብ ብንወስድ ከድርቁ በፊት ሃያ ስድስት ላሞች እና ስድስት አህዮች ናቸው የነበሩኝ።አሁን ግን ሀያ አራቱ ላሞች ሞተው የተረፉት ሁለት ብቻ ናቸው። ከስድስቱ አህዮችም አንድ ብቻ ነው የቀረኝ። እንስሳቶች በንዛት ሞተዋል። ላሞች እና ፍየሎችን ጨርስል።አሁን መሞት የጀመረው ግመል ነው። እናም ለመንግስትም ሆነ ለረጂዎች የእንስሳት መኖ ፣ ለህብረተሰቡ የሚሆን ምግብ እና ውሀ በተሻለ መልኩ እንድያቀርቡልን እንጠይቃለን።"

Dürre in Äthiopien Somali Region
ምስል Mesay Teklu/DW

ሌላኛው የሸቤሌ ዞን ነዋሪም ተመሳሳይ ጉዳት በእንስሳቶቻቸው መድረሱን ለDW ገልፀዋል።

Dürre in Äthiopien Somali Region
ምስል Mesay Teklu/DW

"ያለው ሁኔታ በጣም የሚያሳዝን ነው ። እንስሳት እያለቁ ነው። እኔ ለምሳሌ ከድርቁ በፊት የነበሩኝ ላሞች ስልሳ ነሽበሩ ዛሬ አርባው ሞተው የቀሩት ሃያዎቹ ናቸው። መኖ ባለመኖሩ ሃያዎቹም ቢሆን በሞት መንገድ ላይ ናቸው። የቀሩኝ ሃያዎቹን እንክኋን አውጥቼ ልሽጥ ብል የሚገዛ የለም።ከዚያ ውጭ አሁን መሞት የጀመረው ግመል ነው።
በባርጉን መንደር ያለን ሰዎች ከእንስሲቻችን ውጭ እርሻ እናከናውን የነበረ ቢሆንም ባለፉት ጊዜያት ዝናብ ባለመጣሉ የሰራነው እርሻም የለም ። ችግሩ የከፋ ነው። "

በዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ፅ/ቤት የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ አስተባባሪ አቶ አብዲ አህመድ ለተጎጂዎች ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን ጠቁመዋል። በክልሉ ካሉ አስራ አንድ ዞኖች በዘጠኙ በተከሰተው ድርቅ ከሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ በላይ እንስሳት መሞታቸው ተገልፆል።መሳይ ተክሉ

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ