1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዳግም የፕሬዚደትነቱን ዕድል ያገኙት ሀሰን ሼክ መሐሙድ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 4 2014

የምስራቅ አፍሪቃዊቷ ሶማሊያ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ የተመራጩን ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በዓለ ሲመት አክብራለች። ሶማሊያ ለአንድ ዓመት ያህል በሰበብ አስባቡ ምርጫውን ስታራዝም ከቆየች በኋላ የቀድሞ ፕሬዚዳንቷን አዲስ መርጣለች። የ66 ዓመቱ ሰው ሀሰን ሼክ መሀሙድ ከተሰናባቹ ፕሬዚዳንት መሐመድ ፋርማጅሆ በፊት ስምንተኛው ፕሬዚዳንት ነበሩ ።

https://p.dw.com/p/4CZ9R
Somalia Präsident Hassan Sheikh Mohamud
ምስል Farah Abdi Warsameh/AP/picture alliance

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ከፊታቸው ብዙ ነገር ይጠብቃቸዋል

የምስራቅ አፍሪቃዊቷ ሶማሊያ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ የተመራጩን ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በዓለ ሲመት አክብራለች። ሶማሊያ ለአንድ ዓመት ያህል በሰበብ አስባቡ ምርጫውን ስታራዝም ከቆየች በኋላ የቀድሞ ፕሬዚዳንቷን አዲስ መርጣለች። የ66 ዓመቱ ሰው  ሀሰን ሼክ መሀሙድ ከተሰናባቹ ፕሬዚዳንት መሐመድ ፋርማጅሆ  በፊት ስምንተኛው ፕሬዚዳንት ነበሩ ። የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎዛ ደግሞ የሙስና ወንጀል  ክስ ቀርቦባቸዋል። ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ሁለተኛ የስልጣን ዘመን ምርጫ አጣብቂኝ ውስጥ ናቸው ተብሏል። 
ጤና ይስጥልን አድማጮቻችን  በሁለቱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው የዕለቱ የትኩረትበአፍሪቃ ዝግጅታችን ተጀምሯል ፤ ከዝግጅቱ ጋር ታምራት ዲንሳ ነኝ መልካም ቆይታ ።
መሸጋገሪያ 
  ሀሰን ሼክ መሀመድ በ,ስልጣን ዘመናቸው ሙስና መንሰራፋቱ እና በተለይ ከአሸባብ ጋር የሚደረግ ትግል እጅጉን ሚዛን እየሳተ በመሄዱ ብዙ ርቀው መሄድ ሳይችሉ ቀርተዋል። የሆነ ሆኖ ሀሰን ሼክ መሐሙድ ታሪክ ሆነው አልቀሩም ።  በጎሳ መሪዎች የተሞላው ምክር ቤት በምርጫው እንደገና ይሁንታውን ሰጣቸው ። ከአወዛጋቢው የምርጫ ሂደት በኋላ ፕሬዚዳንትነታቸው ተረጋገጠ ። አሁን የጎረቤት ሃገራትን መሪዎች ጨምሮ የበርካታ ሀገራት ልዑካን በተገኙበት  የአዲስ ፕሬዝደንቷን በዓለ ሲመት አክብራለች። 
ፕሬዚደንቱ በበዓለሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግራቸው በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን አንስተዋል። በተለይ የአፍሪቃ ቀንድ እና የምስራቅ አፍሪቃ ሃገራትን ደህንነትን የሚፈታታነው ጽንፈኛውን የአልሸባብ ቡድን መታገል በሚገባበት ጉዳይ ላይ የአካባቢውን ሀገራት ትብብር መጠናከር ጠይቀዋል። 

« በተለይም ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ጋር በመሆን ዛሬ እንደ አልሸባብ እና አይ ኤስ ካሉ አሸባሪ ቡድኖች የሚመነጩ የጸጥታ የደህንነት ችግር ካለባቸው የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ጋር በፀጥታ ጉዳይ ላይ በጋራ መረባረብ አለብን።»

Somalia Hassan Sheikh Mohamud
ምስል Abukar Mohamed Muhudin/AA/picture alliance

የምርጫ ነገር ሲነሳ በተለይ ስልጣንን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሙጥኝ ብለው ይዘው ለሚቆዩ መሪዎች የሶማሊያ መሪዎች ስልጣን ሽግግር አስተማሪ ሆኖ ሊታይ ይችላል። ፕሬዚደንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ በዚሁ የበዓለሲመት ንግግራቸው ለህዝባቸው ባስተላለፉት መልዕክት ሀገሪቱ ከምንጊዜውም በላይ አንድነት የምትሻበት ወቅት ስለመሆኑ ነው። 

"በመሆኑም ህዝባችንን ከጠላቶቻችንን ለመከላከል ተባብረን በጋራ መስራት እጅጉን አስፈላጊ ጉዳያችን ነው"

ሶማሊያ ከጽንፈኛው አልሸባብ ከሚገጥማት የደፈጣ ውግያ ባሻገር በቀጣናው ሃገራት የተጋረጠው የድርቅ እና የረሃብ ስጋት ሰለባም ሆናለች። ይህንኑ በተመለከተ ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ያነሱትም ሃሳብ ይህንኑ የሚያጠናክር እና ትልቅ ስራ ከፊታቸው እንደሚጠብቃቸው ያረጋገጠ ሆኗል።
«የምስራቅ እና የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ከባድ ድርቅ አጋጥሟቸ,ዋል። ከእነዚህም ውስጥ አንዷ ሶማሊያ ስትሆን  አንዳንድ አካባቢዎች ለረሃብ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ብርቱ ስጋት አለ።» 

 በእርግጥ ነው አስር ዓመታትን የተሻገረው እና የተለያዩ ፕሬዚዳንቶችን እያፈራረቀ የቀጠለው የሶማሊያ መንግስት ከአሸባብ ጋር የሚያደርገው ትግል ፕሬዚዳንቶች ወደ ስልጣን ሲመጡ የሚጠብቃቸው ዋነኛ ጉዳያቸው ነው። አሸባብ ከሶማሊያ ተሻግሮ የጎረቤት ሃገራት ላይ ጥቃት ማድረ,ስ መቻሉ ደግሞ የሀገሪቱ መንግስት ከዚህ አንጻር ከጎረቤት ሃገራት ጋር ለሚኖራት ግንኙነት አንዱ ማስተሳሰሪያ አ,ድርጎ ማንሳትም ይቻላል። የምስራቅ አፍሪቃን ፖለቲካ በቅርበት እንደሚከታተሉ የሚናገሩት እና መቀመጫቸውን በሀገረ ኖርዌይ ያደረጉት አቶ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉትም የሶማሊያ መንግስት ከአልሸባብ ጋር የሚያደርገው ፍልሚያ ተጠናክሮ መቀጠሉ እንደማይቀር ነው።   

በፕሬዚዳነት ሀሰን ሼክ በዓለ ሲመት ላይ የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ፣ የኬንያ እና የጂቡቲ መሪዎችን ጨምሮ የበርካታ ሃገራት ባለስልጣናት ተገኝተዋል። 
ፕሬዚደንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ ፕሬዚዳንታዊ ቃለ መሃላ በፈጸሙበት ወቅት ካነሷቸው ሃሳቦች መካከል መንግስታቸው በዓለም ላይ ካሉ ተቀናቃኝ ጎራዎች ጋር ባለመቀላለል ገለልተኛ እና ሰላማዊ የውጪ ፖሊሲ እንደሚከተሉ ቃል የገቡበት ተጠቃሹ ነው። ከእሳቸው በፊት የሶማሊያ ፕሬዝደንቶች ከነበሩት የሀገሪቱ ፖለቲከኞች ጋርም እንደሚመካከሩ አመልክተዋል። በ,እርግጥ በሀገራት የገንዘብ እና ወታደራዊ ድጋፍ እየተውተረች ላለች ሀገር በእርግጥ ገለልተኛ ሆና መቀጠል ይቻላት ይሆን? አቶ ዩሱፍ ያሲን
በሞቃዲሾ ፕሬዚዳንታዊ በዓለ ሲመት ከመደረጉ አስቀድሞ በመዲናዋ አውሮፕላን ማረፊያ  የከባድ መሳሪያ ጥቃት መፈጸሙ ተሰምቷል። በጥቃቱ ሲቪሎች ላይ ጉዳት መድረሱ ቢነገርም ስለደረሰው ጉዳት በዝርዝር የተባለ ነገር የለም። በቀጣዮቹ ቀናት ስለሚሆነውም ነገር አይታወቅም ። የጠቅላይ ሚስትር ሹመትም ተጠባቂው  ጉዳይ ነው። ድርቅ  እና ረሃብ በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል የጽንፈኛው አልሸባብ ጉዳይ ሶማሊያ በመጻኢ ጊዜዋ የምትፋለማቸው ዐበይት ጉዳዮች ይሆናሉ። የሀሰን ሼክ ሙሐሙድ መንገድ እና ሶማሊያን አብረን እናያለን። 

ታምራት ዲንሳ 

ኂሩት መለሰ