1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስአፍሪቃ

ዳግም እና ዘመናዊ የጫማ መጥረጊያው ማሽን

ዓርብ፣ ግንቦት 26 2014

ዳግም አበበ ዘመናዊ የጫማ መጥረጊያ የሰራ የዩንቨርስቲ ተማሪ ነው።የፈጠራ ስራው ዋና አላማ «በመንገድ ላይ ጫማ የሚያፀዱ ወጣቶችን ለመርዳት ነው» ይላል። ስለ ሰራው የጫማ መጥረጊያና እንዴት ሊስትሮዎችን ይረዳል ብሎ እንዳሰበ ገልጾልናል። በድምፅ ዘገባው ላይ ዳዊት አበበ የሚለው ዳግም አበበ እንደሆነና በስህተት መሆኑን ከይቅርታ ጋር እንገልፃለን።

https://p.dw.com/p/4CEcR
Äthiopien | Dawit Abebe baute eine Schuhputzmaschine
ምስል privat

ዳግም እና ዘመናዊ የጫማ መጥረጊያው ማሽን

ብዙውን ጊዜ ስለ ሊስትሮዎች ስናስብ ወዲያው አዕምሮዋችን ውስጥ የሚመጣው  በአስራዎቹ እድሜ የሚገኙ ወንድ ልጆች መንገድ ዳር ቁጭ ብለው ጫማ ሲጠርጉ ሊሆን ይችላል። ይህንን እንዴት በዘመናዊ መልክ መቀየር ይቻላል?ዳግም አበበ ከዚህ ቀደም የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች ላይ የተካፈለ ሲሆን በቅርቡ የሰራው ደግሞ ዘመናዊ የጫማ መጥረጊያ ነው። ለዚህም ምክንያት የሆነኝ «አንድ ደንበኛዬ ነው» ይላል። « ጠራጊው ልጅ ስለቤተሰቡ ፣ስለ ራሱ ያጫውተኝ ነበር። ያኔ እሱ የማታ የ7ኛ ክፍል ተማሪ ነበር። በቀን 600 ብር አግኝቶ ማታ ለቤተሰቡ እራት ይዞ ይገባ ነበር። እና እኔም ያኔ በትምህርት ቤት ደረጃ የፈጠራ ስራዎች ላይ እወዳደር ነበር እና እሱን የሚጠርግበትን ዘዴ ለምን መማሽን እንዲሰራ አላደርግም ብዬ ወሰንኩ። » ከዛም የፊዚክስ መምህሩን አናገረ።
የፊዚክስ መምህሩ ግን በትላልቅ ሆቴሎች ውስጥ በማሽን የሚሰሩ ጫማ መጥረጊያዎች እንዳሉ እና ዳግም ሌላ የፈጠራ ስራ ላይ እንዲያተኩር ነገሩኝ ይላል። እሱ ግን ሌላ ነገር ለመስራት ፍቃደኛ አልነበረም። 
የ 24 ዓመቱ ዳግም በአሁኑ ሰዓት በቅድስተ ማሪያም ዩንቨርስቲ ኮሌጅ የ3ኛ ዓመት የማኔጅመንት ወይም የአስተዳደር ተማሪ እና በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የማታው መርኃ ግብር የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ነው። እናቱን በሞት ያጣው ዳግም በአንድ ጊዜ በሁለት ከፍተኛ ተቋማት ትምህርቱን የሚከታተለው ጥሩ ደረጃ ደርሶ አባቱን እና ቤተሰቦቹን ለማስደሰት እንዲሁም ህይወታቸውን መቀየር ስለሚፈልግ እንደሆነ ይናገራል። ምናልባት ይኼ ጫማ መጥረጊያ በር ከፋች ይሆንለት ይሆናል። ነገር ግን ይህንን ለመስራት ምክንያት ሆነኝ የሚለውን ሊስትሮ በምን መልኩ ይጠቅመዋል? ይልቁንስ ገበያ መጋፋት አይሆንበትም? አይ ይላል ዳግም ! « የሱን ህይወት ለማቅለል እና እሱ ወደ ትምህርት ገበታው እንዲመለስ ነው ሀሳቤ። ማታ ከትምህርት ቤት ሲመለስ ልክ እንደ ATM ማሽን ገንዘቡ ተጠራቅሞ እንዲጠብቀው ነው። » ዳግም ይህንን ማሽን ሲሸጥላቸውም ሊስትሮዎቹ በማህበር ተደራጅተው እንዲገዙ መንገድ እንዲመቻች ይፈልጋል። 

Äthiopien | Dawit Abebe baute eine Schuhputzmaschine
ምስል privat
Äthiopien | Dawit Abebe baute eine Schuhputzmaschine
ምስል privat

ዳግም ይህንን ጫማ መጥረጊያ ለመስራት የተወሰኑ አመታት ፈጅቶበታል። ለመጓተቱ አንዱ ምክንያት ዳግም በአክሱም ዩንቨርስቲ ይማር በነበረበት ወቅት በአካባቢው በነበረው አለመረጋት እና ጦርነት ምክንያት እቃዎቹ እዛው መቅረታቸው ነው። « በመሀል ለአንድ ውድድር ወደ አዲስ አበባ በመጣሁበት ወቅት እዛ ብጥብጥ ተነሳ።  ሻንጣዬ ፣ ላፕቶፔም እዛ ነበር።  አባቴ ግን መሄድ አትችልም ብሎ አስቀረኝ። »በመጨረሻም ዳግም ህልሙን አሳክቶ ለሰራው ማጫ መጥረጊያ የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት አገኝቷል።  ይህም አንድ ዓመት ያህል ፈጅቶበታል። ዳግም እስካሁን ከወዳደቁ እቃዎች ለናሙና የሰራው ጫማ መጥረጊያን ብቻ ነው የሰራው። በታሰበው መንገድ በተሟላ መሣሪያ ለመስራት ብዙ ወጪ ስላለው እንዳልተሳካለት ይናገራል።
ዳግም ከዚህ የፈጠራ ስራ በፊት የሀይስኩል ተማሪ ሳለ በፀሀይ የሚሰራ ባቡር እና እቤት ውስጥ ሰው ባይኖር ከውጭ ደውሎ ሻይ ማፍላት የሚችልበት ማፈያ እንደሰራ ይናገራል። ወደፊትም በፈጠራ ስራው መቀጠል ይፈልጋል። «ሊስትሮዎች ጫማ በእጅ እንይጠርጉ እና ለትምህርታቸው በቂ ሰዓት እንዲኖራቸው በማሰብ ነው ዘመናዊ ጫማ መጥረጊያ የሰራሁት ከሚለው ዳግም አበበ ጋር የተደረገውን ቃለመጠይቅ እና ሙሉ ዘገባ በድምፅ ያገኙታል።

በድምፅ ዘገባው ላይ ዳዊት አበበ የሚለው ዳግም አበበ እንደሆነና በስህተት መሆኑን ከይቅርታ ጋር እንገልፃለን።

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ