1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቀደም ሲል በተለያዩ የትግራይ ክልል ዩንቨርስቲዎች የነበሩ ተማሪዎች ቅሬታ አሁንም አላበቃም።

ልደት አበበ
ዓርብ፣ መጋቢት 16 2014

ቀደም ሲል በተለያዩ የትግራይ ክልል ዩንቨርስቲዎች የነበሩ ተማሪዎች ምንም እንኳን መንግሥት በሌሎች የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች መድቧቸው ትምህርታቸዉን እየተከታተሉ ቢሆንም ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ግን እስካሁን የምረቃ ማስረጃቸውን አላገኘንም ሲሉ ትምህርት ሚኒስቴርን ይወቅሳሉ። የዛሬው የወጣቶች ፕሮግራም ለተማሪዎቹ ወቀሳ ምላሽ አፈላልጓል። 

https://p.dw.com/p/492Om
Äthiopien Studierende Tigray Universität
ምስል Solomon Muchie/DW

አለምነህ መስፍን በአክሱም ዩንቨርስቲ የአራተኛ ዓመት የጂዎሎጂ ተማሪ ሳለ ነው ትምህርቱን ለማቋረጥ የተገደደው። መጀመሪያ በኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ቀጥሎም ትግራይ ክልል ውስጥ በነበረው ጦርነት ምክንያት ከበርካታ ወራት ትምህርቱን ካቋረጠ በኋላ  ተማሪዎቹ ለመንግሥት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ድሬደዋ ዩንቨርስቲ ደርሶት ትምህርቱን መቀጠል ችሏል። ወጣቱ ተማሪ አክሱም ዩንቨርስቲ ሳለ የመጨረሻ ዓመት ተመራቂ ተማሪ ስለነበረም ከተወሰኑ ወራት በኋላ ከድሬደዋ ዩንቨርስቲ የቀሩትን ትምህርቶች ወስዶ ጨረሰ። ይሁንና መመረቁን የሚያረጋግጥ ወረቀት እስካሁን አላገኘሁም ይላል።  « ትምህርታችንን እንዳጠናቀቅን ድሬደዋ ጊቢም ትምህርት ሚኒስቴርም ያውቃል። ድሬደዋ ጊቢ ግሬድ ሪፖርት ሰጥቶናል። ምንም ማድረግ አይችልም። ትምህርት ሚኒስቴር ግን ቴምፖ አልሰጠንም።» ይላል።  ይህ ድሬደዋ የተመደቡ ተማሪዎች ችግር ብቻ አይደለም። ዲላ ዮንቨርስቲ የተመደበው አስራት ወልዴም ተመሳሳይ ወቀሳ ያነሳል።  « የቀረችንን ሴሜስተር ጨረስን። ከዛ ስለ ውጤታችን ስለ ቴምፖ እየጠየቅን ነበር» ይላል መፍትሄ የሚጠይቀው አስራት።

ናሆም አህመድ ጠቅላላ ከትግራይ ክልል ዩንቨርስቲዎች የተመለሱ ተማሪዎችን ወክለው ከሚከራከሩ  ተማሪዎች አንዱ ነው።  እሱም ትግራይ ክልል ይማር የነበረ ምሩቅ ተማሪ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ ይኖራል።  « ከ 2500 በላይ ተመራቂ ተማሪ ነው 2013 ዓ ም የነበረው።  እነዚህ ሁላችንም ተማሪዎች በ23 ዩንቨርስቲዎች ተመድበን ገብተን እየተማርን ነበር።  አሁን ላይ በ አምስት ዮንቨርስቲዎች ይማሩ የነበሩት አጠናቀዋል። የተቀሩት ደግሞ በአንድ ወር ውስጥ ይጨርሳሉ» ያኔ የቴምፖን ጉዳይ አነሳን ይላል ናሆም። «ትምህርት ሚኒስቴርም ለማንኛውም ስራ ለመወዳደር የሚያበቃቹህ ቴምፖ ይሰጣችኋል ብሎን ነበር» ይላል ናሆም።

Äthiopien | Ehemalige Studenten der Tigray-Universität
ቀደም ሲል በተለያዩ የትግራይ ክልል ዩንቨርስቲዎች የነበሩ ተማሪዎች እና ወላጆቻቸው ቅሬታቸውን ለትምህርት ሚኒስቴር አሰምተው መንግሥት በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በሌሎች የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች መድቦ ትምህርታቸዉን እየተከታተሉ ይገኛሉ።ምስል Solomon Muchie/DW

ተማሪዎቹ „ቴምፖ“ የሚሉት ማንኛውም ምሩቅ ተማሪ የሚያገኘው ቴምፖራሪ ዲግሪ ወይም ጊዜያዊ የዲግሪ ማስረጃ ወረቀትን ነው።  ይሁንና ተማሪዎቹ እንደሚሉት ትምህርት ሚኒስቴር ለሁሉም የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኃላ ላይ አስተላለፈ የሚሉት መመሪያ ሌላ ነው። ናሆም ወቀሳ የቀረበበት አካል በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጠን ጠይቀናል። በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት ዶክተር ኤባ ሚጀና ወቀሳውን አጣጥለው አሁንም ተማሪዎቹን ወደ ስራ ዓለም ከመግባት የሚያግዳቸው ምንም ነገር የለም ይላሉ። « ማስረጃውን ወስዶ ይኼ ተቋም እምቢ ብሎናል ያለን እስካሁን የለም። ሊሆን ይችላል ተብሎ አይሰራም።  ከገጠማቸው ደግሞ እንዴት ይፈታል የሚለውን እናያለን።» የሚሉት ዶክተር ኤባ  « ተማሪዎቹ አጠቃላይ «ስቱደንት ኮፒ» ነው የሚሰጣቸው። ያ ነው የሚሰጣቸው ለሌላ ተማሪም የሚሰጠው። » ስለሆነም መረጃው ወይም ፎርሙ ዲግሪውን ማጠናቀቃቸውን ያሳያል ይላሉ።

በትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ መሠረት ይህንን ማስረጃ ለማግኘት ተማሪዎቹ ቀድሞ ይማሩ ከነበሩበት ዩንቨርስቲዎች  የተሰጣቸውን ውጤት ወይም « ግሬድ ሪፖርት» ማቅረብ ግድ ይላቸዋል። የተማሪዎቹ ተወካይ ናሆም እንደገለጸልን ግን ተማሪዎቹ ውጤታቸውን ያገኙ የነበረው በኦንላይን ስለነበር ሁሉም ተማሪዎች በአሁኑ ሰዓት ይህ ማስረጃ የላቸውም። እንደ ዶክተር ኤባ ሚጀና ከሆነ ተማሪዎቹ ይህንን የመያዝ ግዴታቸው ነበር።  « ታድያ አንድም ነገር ማስረጃ ሳይዙ በምንድን ነው ተመርቋል የሚል ማስረጃ የሚሰጣቸው።» በማለት ዶክተር ኤባ ተማሪዎቹ መረጃውን የማግኘት የተለያዩ አማራጮች እንደነበራቸው ይናገራሉ። 

ለዲግሪ ማስረጃችን መፍትሄ ለማግኘት ስንል ረዥም ጊዜ በተማርንበት ከፍተኛ ተቋማት ድሬደዋ እና ዲላ ዩንቨርስቲዎች ቆይተናል የሚሉት አለምነው እና አስራት ተቋሙን ለቀው ለመሄድ ተገደዋል።አለምነው እንደገለጸልን እስከ ዛሬ አርብ ድረስ እነዚህ ተማሪዎች ለቀው እንዲወጡ ተነግሯቸዋል። አስራትም ከዲላ ዮንቨርስቲ ተማሪዎቹ ወደየቤታቸው እየተመለሱ ነው ብሎናል።

የትግራይ ክልል ዩንቨርስቲዎች ይማሩ ከነበሩ ተማሪዎች ለቀረበ ወቀሳ ምላሽ ያፈላለገው የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት በድምፅ ዘገባም ያገኛሉ።

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ