1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የገጠማቸው አዲስ ፈተና

ልደት አበበ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2016

በደቡብ አፍሪቃ የሀገሬው ሰዎች የሥራ ዕድል ይነጥቃሉ ብለው በሚከሷቸው የውጭ ሀገር ሰዎች ላይ የሚያነጣጥረው ጥላቻ አሁንም ይስተዋላል። ይህ አይነቱ ጥላቻ እና በደል ደግሞ አሁን ላይ «አይነቱን ቀይሮ መጥቷል» ይላሉ ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው በደቡብ አፍሪቃ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ።

https://p.dw.com/p/4aIln
Südafrika I Proteste gegen Ausländer
ምስል Milton Maluleque/DW

ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ችግር

በደቡብ አፍሪቃ በሌሎች ሀገር ዜጎች ላይ ባነጣጠረ ጥላቻ ወይም ዜኖፎቢያ ጋር በተያያዘ ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት ብቻ  117 ሱቆች ተዘርፈዋል። 38 ሰዎች ተገድለዋል። የሀገሬው ሰዎች የሥራ ዕድል ይነጥቃሉ ብለው በሚከሷቸው የውጭ ሀገር ሰዎች ላይ የሚያነጣጥረው ጥላቻ አሁንም ይስተዋላል።  ባለፉት አመታት ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሚሰደዱት የውጭ ሀገር ዜጎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ በጎርጎሮሲያኑ 2020 ዓ ም  2,9 ሚሊዮን ዓለም አቀፍ ስደተኞች ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ተሰደው ይኖራሉ። ከአፍሪቃ በኢኮኖሚ ወደ በለፀገችው ሀገር የሚሰደዱትም በተለይ ለተሻለ የስራ እና የኑሮ እድል ሲሉ ነው።  በዚህ ምክንያት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ የሀገሪቱ ዜጎች በውጭ ዜጎች ላይ ያላቸው ጥላቻ ወይም  ዜኖፎቢያ  ከፍተኛ ነበር። ኢትዮጵያውያንም የዚህ ሰለባ ነበሩ፣ አሁንም እንደሆኑ ይናገራሉ።

በደቡብ አፍሪቃ መልኩን የቀየረው የውጭ ዜጎች ጥላቻ

ይህ ጥላቻ አሁን የሚፈፀምበት መንገድ መቀየሩን አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ  እና የማህበረሰብ ደህንነት ላይ ከመንግሥት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅት ጋር የሚሰሩ ኢትዮጵያዊ ለዶይቸ ቬለ  ሲናገሩ «ትልቅ ችግር ያለው ወረቀት የሌላቸው ላይ ቢሆንም ወረቀት ያላቸውም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ነው ያሉት። ያም ችግር እየተፈጠረ ያለው ከመንግሥት አካል ነው።»

በተለይ በደቡብ አፍሪቃ በሚመጣው ግንቦት ወር የሚካሄደውን አጠቃላይ ምርጫ ምክንያት በማድረግ « ስደተኞች  መጠቀሚያ ሆነዋል» ይላሉ ኢትዮጵያዊው። ለዚህም ተጠያቂ የሚያደርጉት ገዢው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ)ፓርቲን እና የመንግሥት ተቋማትን ነው።

የስደተኞች ጉዳይ ለምርጫ ዘመቻ


«ድምፃቸው ተሰሚነት እንዲያገኝ በእኛ ላይ የበለጠ ያልተገቡ ነገሮች ያደርጋሉ።  ለደህንነት ሊቆሙ የሚገቡ እንደ ፖሊስ ያሉ ክፍሎች  ማህበረሰባችንን እያሰሩ፣ ሱቅ እየገቡ ህገ ወጥ የሆኑ እቃዎች አሉ እያሉ  ኦፕሬሽን የሚያደርጉ መስለው ዝርፊያ እና ያልተገባ ዛቻእያደረጉ ነው ያሉት» ይላሉ።

ክብሩ ግርማ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው። ከአንድ ወር በፊት ጓደኛቸው በሚሰራበት ሱቅ በሶስት ሌቦች ተገድሎ ተጠርጣሪዎቹን ለፍርድ እንዲቀርቡ ቢደረግም በህግ ተሰሚነት እንዳላገኙ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። « ፖሊስ ፤ በሰፈሩ የማህበረሰብ መሪዎች እና እዛ የምንኖረው አበሻ ጭምር ሌቦቹን አገኘናቸው እና ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር። ነገር ግን ፍርድ ሳይሰጣቸው ሌቦቹ በፍርድ ቤት ቀጠሮ ወዲያው ተለቀቁ » ሲሉ ይወቅሳሉ።

ሌቦቹ ገዳዮቹም ስለመሆኗቸው ክብሩ ጥርጥር የላቸው። «ለምን እና እንዴት እንደገደሉ አምነው ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት» ይላሉ። እንደእሳቸውም ገለፃ ችግሩ ያለው የህግ አስፈፃሚዎቹ ጋር ነው። በተለይ ምርጫ ቅስቀሳው ከወር በፊት ከጀመረ አንስቶ ተጠናክሯል ይላሉ።  « ለዛ ምርጫ ብለው የህግ አካልም የህግ አካል ውጪ የሆኑም የሆነ ነገር ሰበብ እያደረጉ ብዙ ጥቃት እያካሄዱ ነበር» የሚሉት ክብር ግርማ «ይህም ጥቃት ሶየቶ እና ጆሀንስበርግ አካባቢ በብዛት ተስተውሏል» ይላሉ ።

Xenophobie in Südafrika
የተናደዱ የዙሉ ተቃዋሚዎች በጆሃንስበርግ የውጭ ስደተኞችን በመቃወም ሰልፍ ወጥተውምስል AFP/Getty Images/M. Longari

 ኢትዮጵያውያን ስለሚደርስባቸው በደል ተቃውሞ ሰልፍ አዘጋጅተው ለመግለፅ ያሰቡ የነበረ ቢሆንም ባላቸው ስጋት እስካሁን እንዳልተካሄደ በደቡብ አፍሪቃ የማህበረሰብ ደህንነት  ላይ የሚሰሩት ኢትዮጵያዊ ገልፀውልናል። « ከመንግሥት ጋር የተያያዘ ነገርም ስለሆነ ፣ ትንሽ መንግሥትን የመቃወም ስሜት እንዳያመጣ በሚሉ ትንሽ ገፍቶ የመሄድ ሁኔታ አይታይም» ይላሉ። ይልቁንም ትኩረታቸውን መንግሥታዊ ካላሆኑ ድርጅቶች ጋር አድርጓል።  ይህ በደቡብ አፍሪቃ የሚገኘው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጥረት ሲሆን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዜጎችን ደሕንነት ለማስጠበቅ ምን አይነት ጥረት እያደረገ ይገኛል? ይህንን ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ፕሪቶሪያ የሚገኘው ኢትዮጵያ ኤምባሲ ብንደውልም ስልኩ አልተነሳልንም።

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ