ያደገው የአፍሪቃ ወታደራዊ ወጪ
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 28 2014ያደገው የአፍሪቃ ወታደራዊ ወጪ
የፀጥታዋ ጉዳይ እጅግ የሚያሳስባት ናይጀሪያ በቅርቡ የጦር መሣሪያ ለመሸመት ወደ ቻይና ጎራ ብላ ነበር። ከቻይና የገዛቻቸው የውጊያ ታንኮችም በመርከብ ተጭነው ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሌጎስ ወደብ ደርሰዋል። ከዛሬ ሁለት ዓመት አንስቶ መንግሥት የናይጀሪያን ጦር ኃይል ለማዘመን ከቻይና የገዛቸውን 15 ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች መጠቀም ጀምሯል። በጎርጎሮሳዊው 2021 ከሰሀራ በረሀ በታች ከሚገኙ ሀገራት ናይጀሪያ ለጦር መሣሪያ ግዥ ብዙ ገንዘብ አውጥታለች። የስቶክሆልም የሰላም ጥናትና ምርምር ተቋም በምህጻሩ ሲፕሪ እንደመዘገበው ናይጀሪያ በጎርጎሮሳዊው 2021 ዓም የመከላከያ ወጭዋ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ነበር።ይህ ገንዘብም ከቀደመው ዓመት በ56 በመቶ ከፍ ያለ ነው። የናይጀሪያ መንግሥት የመከላከያ ወጭ በዚህ ዓመት ይበልጥ መጨመሩን «ግሎባል ፋየርፓወር ኢንዴክስ »የተባለ የዓለም የጦር ኃይሎች ዓመታዊ ወጪን የሚያነጻጽረው የዩናይትድ ስቴትስ ድረ ገጽ አስታውቋል።ድረ ገጹ እንዳስነበበው መንግሥት በጎርጎሮሳዊው 2022 ለመከላከያ የሚወጣው ገንዘብ 5.9 ቢሊዮን ዶላር ነው።የናይጀሪያ በመከላከያ ወጪ ከሰሀራ በታች ካሉ የአፍሪቃ ሀገራት የመጀመሪያውን ቦታ ትይዛለች። በድረገጹ መሠረት የደቡብ አፍሪቃ ወጭ ደግሞ 2.9 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የኬንያ ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር ያንሳል።ዴረን ኦሊቨር«አፍሪቃን ዲፌንስ ቪው»የተባለው በአፍሪቃ ግጭቶችና መከላከያ ላይ የሚያተኩረው ነጻ መገናኛ ብዙሀን ሃላፊ ናቸው። በተለይ የደቡብ አፍሪቃ ወታደራዊ ወጪ ከፍ ማለቱን ከወታደሩ ደሞዝ መረዳት አያዳግትም ይላሉ።
«ደቡብ አፍሪቃ በአጠቃላይ ለሠራተኛ የምትከፍለው ደሞዝ ከፍተኛ ነው።ይህንንም ወታደሩና የመንግሥት ሠራተኞች በሚያገኙት ደሞዝ ማወቅ ይቻላል።ይህ ማለት ሁሉም እኩል ተመሳሳይ ደሞዝ ያገኛሉ ቢባል እንኳን በናይጀሪያ አንድ መካከለኛ ደረጃ ያለው ወታደር ከሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች በሁለትና በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ደሞዝ ያገኛል።ይህም በሌሎች በርካታ ሀገራት ወታደሮች ከሚያገኙት በአምስት እጥፍ ያህል የሚበልጥ ነው።»ምንም እንኳን በኮሮና ምክንያት የኤኮኖሚ ዝግመት ቢከተለም ባለፉት ዓመታት የበርካታ የአፍሪቃ ሀገራት ወታደራዊ ወጪ አድጓል፤ ይላሉ ዴረን ኦሊቨር /በሲፕሪ ዘገባ መሠረት በአፍሪቃ የመከላከያ ወጭ ከ2021 ጋር ሲነጻጸር በ2022 ዓም በ1.2 በመቶ ጨምሯል። ያም ማለት በክፍለ ዓለሙ ወታደራዊ መሣሪያዎች 39.7 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓባቸዋል ።ከዚህ ውስጥም 20.1 ቢሊዮን ዶላሩ ወጪ የተደረገው ከሰሀራ በረሀ በታች በሚገኙት በናይጀሪያ በደቡብ አፍሪቃና በኬንያ ነው ።አንዳንድ ትንሽ የሚባሉ ሀገራት ሳይቀር ለመከላከያ የሚያወጡት ገንዘብ ከፍተኛ ነው ለምሳሌ ቦትስዋና በ2021 ከአጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ሽያጭ ገቢዋ ሁለት ነጥብ ዘጠኝ በመቶውን ለመከላከያ ነው ያዋለችው። ዳራን ኦሊቨር እንደሚሉት ደቡብ አፍሪቃ በ2021 ለመከላከያ ያወጣችው ገንዘብ ከአጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ሽያጭ ገቢዋ 2.2 በመቶው ነው ። ሦስቱ ሀገራት ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ገቢያቸው አብዛኛውን ለወታደራዊ ወጪ አውለዋል እንደ ኦሊቨር ።ናይጀሪያ በ2021 ከአጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ገቢዋ 1.02 በመቶውን ለመከላከያ መድባለች ።በቀደመው ዓመት ግን 0.6 በመቶውን ነበር ለመከላከያ ያዋለችው። ኦሊቨር ናይጀሪያ ከምትገኝበት የፀጥታ ችግር በመነሳት ይህ ገንዘብ ብዙ የሚባል አይደለም ብለዋል። የፀጥታ ችግሩ ሊባባስ የቻለበትን ምክንያትም ተናግረዋል።«ሀገሪቱ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር የማይቻል ሰፊ መሬትና ረዥም ድንበር ስላላት ለጸጥታ ቀውስ ተጋልጣለች። ከዚህ ጋር በህዝቡ በኩል የሚደረግ ድጋፍ፣ የሃይማኖት ልዩነት፣ሙስና እና የኤኮኖሚ እድገት አለመኖርና የመሳሰሉት ችግሩን ያባብሳሉ። »
ከጎርጎሮሳዊው 2009 ዓ.ም. አንስቶ አሸባሪው «ቦኮ ሀራም» በየጊዜው የሚጥላቸውን ጥቃቶች በተለያየ ጊዜ የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶችንና ግጭቶችንም መከላከል መንግሥትን ብዙ ገንዘብ ያስወጣሉ። በናይጀሪያ ምክር ቤት የጦር ሠራዊት ጉዳዮች ኮሚቴ ከጥቂት ቀናት በፊት በናይጀሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ጠይቀው ነበር። የፓርላማ አባሉ የናይጀሪያ ጦር ሠራዊት የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለመቋቋም በቂ በጀት የለውም ሲሉም አሳስበው ነበር።የሽብር ጥቃቶች በምስራቅ አፍሪቃም አሳሳቢ ናቸው።በኬንያና ሶማልያ መካከል የተፈጠረው ውጥረት ኬንያ ባለፉት 10 ዓመታት የጦር ኃይልዋን እንደገና እንድታዋቅር አድርጓታል። የዚህም ምክንያቱ በጎርቤት ሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው አማጺው አሸባብ ነው። ኬንያ ወታደሮችዋን በሶማሊያ ወታደራዊ ተልዕኮ ስር አዝምታለች። ከጎርጎሮሳዊው 2011 ዓ.ም. አንስቶ ወታደሮችዋ ሶማሊያ ጁባላንድ ድንበር ላይ ይገኛሉ።ጦር ሠራዊትዋን ይበልጥ ውጤታማና ዘመናዊ ለማድረግም ተጨማሪ ገንዘብ እያወጣች ነው።
ጀርመን ከናሚብያ ማኅበረሰብ የቀረበላትን አዲስ የድርድር ጥያቄ ውድቅ አደረገች
ጀርመን፣ ናሚብያን ቅኝ በገዛችበት ወቅት ለተፈጸሙ ግድያዎችና ለደረሱ በደሎች እውቅና የሰጠችበት ረቂቅ ሰነድ እስካሁን አልተፈረመም። በጎርጎሮሳዊው ግንቦት 2021 ሁለቱ ወገኖች በተስማሙበት ረቂቅ ውል ፣ በያኔዋ ቅኝ ገዥ ጀርመን ፣ ከ100 ዓመታት በፊት በናሚብያ ወይም በያኔው አጠራር በ«ጀርመን ደቡብ ምዕራብ አፍሪቃ» በ10 ሺህዎች በሚቆጠሩ በሄሬሮና ናማ ጎሳ አባላት ላይ የተፈጸመውን ግድያ የዘር ማጥፋት በማለት ጀርመን እውቅና ሰጥታለች።ከስድስት ዓመታት በፊት ከተጀመረ ድርድር በኋላ ባለፈው ዓመት በግንቦት ፣ጀርመንና ናሚብያ የተስማሙበትን ይህን ውል ግን ሁለቱም መንግሥታት እስካሁን አልፈረሙም። ረቂቁ ሰነድ ከመጀመሪያው አንስቶ ከፖለቲከኞችና አዲስ ድርድር ይካሄድ ከሚሉ ከሰለባዎቹ ወገኖች በኩል ጠንካራ ትችት ሲሰነዘርበት ቆይቷል።በአሁኑ ጊዜ የጀርመን መንግሥት አዲስ ድርድር ይካሄድ የሚለውን የሰለባዎቹን ወገኖች ጥያቄ ውድቅአድርጓል። የቀድሞ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ አምና በግንቦት ወር ድርድሩ ማብቃቱን ተናግረው ነበር ።መንግሥት በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫም«ምንም እንኳን የውሉ አተገባበር ላይ አንዳንድ የሚካሄዱ ንግግሮች ቢቀጥሉም በመንግሥት በኩል ግን ከናሚብያ ጋር በጉዳዩ ላይ የተካሄደው ድርድር ፍጻሜ አግኝቷል።»ብሏል። በጀርመን ፓርላማ የግራዎቹ ፓርቲ ተወካይ ስቤም ዳግዴለን መንግሥት ያወጣውን መግለጫ አምረው ተቃውመዋል።
«የፌደራል መንግሥት ካሳ መስጠት አይፈልግም። ካሳ እንዳይከፍል እየተከላከለ ነው።ይህን የሚያደርገው ደግሞ በቅኝ ግዛት ዘመን እንደነበረው ጀርመን በናሚብያ ላይ ያላትን የበላይነት በመጠቀም ነው። ይህ በትራፊክ መብራት የሚመሰለው የጀርመን ጥምር መንግሥት ከናሚብያ ፓርላማ የተሰነዘረበትን ጠንካራ ትችትና የቅኝ ግዛት ዘመን ሰለባዎች ቤተሰቦችን ከፍተኛ ቁጣ መናቁን ነው የሚያሳየው። በቀላሉ እነዚህ ተቃውሞዎች እንደሌሉ ተቆጥረው ወደ ናሚቢያ ተገፍተዋል።»
በርካታ የሄሬሮና የናማ ማኅበረሰብ ተወካዮችም የመንግሥትን ውሳኔ የሚቀበሉ አይመስልም። እነዚህ ወገኖች ቀጥተኛ ንግግር እንዲካሄድ ግፊት ለማድረግ በዚህ ዓመት በታኅሳስ ወር ከጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አና ሌና ቤርቦክ ጋር ለመነጋገር ጠይቀው ነበር።እነዚህ የሰለባዎቹ ወገኖች ጀርመን ለዘር ማጥፋቱ ፖለቲካዊ ሃላፊነትዋን ብቻ እንጂ ሕጋዊ ሃላፊነትዋን ለመወጣት ዝግጁ አይደለችም በማለት ቁጣቸውን ገልጸዋል።ከዚህ ሌላ ጀርመን በ30 ዓመታት ለናሚብያ መልሶ ግንባታና ለልማት ልታውል ያቀደችው የ1.1 ቢሊዮን ዩሮ መርሃ ግብርንም ይተቻሉ።የናማ ማኅበረሰብ ማኅበራዊ አንቂ ሲማ ልዊፐርት ባለፈው ሰኔ ዴር ሽፒግል ለተባለው የጀርመን ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ውሉ የልማት ትብብርና ፕሮጀክቶችን በገንዘብ መደገፉ ጥሩ ነው ይሁንና ውሉ ዋናውን ጉዳይ ፍትህና እርቀ ሰላምን የሚመለከት አይደለም በማለት ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል። በድርድሩ ላይ ሌሎችም የማኅበረሰቦቹ ተወካዮች በተለይ አዲስ ድርድርን ይቃወማሉ። ከመካከላቸው አንዱ ከዚህ ቀደም በተካሄደው ድርድር ሂደት ላይ ማኅበረሰቡን ወክለው የተሳተፉት ኡሪዩካ ትጂኩዋ ናቸው።
«አንድ የውጭ መንግሥት በሌላ የውጭ ሀገር ካሉ ዜጎች ጋር ስምምነት ላይ የሚያደርስ ድርድር የሚያካሂድበት ስርዓት የለም።ስለዚህ በነርሱ ፍላጎት መነሻነት በዘረ ማጥፋት ጉዳይ ላይ እንደገና ድርድር ማካሄድን መንግሥታችን አይቀበለውም።»
ምንም እንኳ ረቂቅ ስምምነቱ ቢያወዛግብም የጀርመን መንግሥት ግን ለተግባራዊነቱ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል። በዚህ ዓመቱ የፌደራል ጀርመን በጀት ለልማት ፕሮጀክቶች 35 ሚሊዮን ዩሮ ያኔ ለተፈጸመው የዘር ማጥፋት መታሰቢያ ለታቀደ ድርጅት ደግሞ 4 ሚሊዮን ዩሮ መድቧል። ገንዘቡ ጀርመን በካሳ መልክ ልትሰጥ ካቀደችው 1.1 ቢሊዮን ዩሮ የሚወሰድ ነው። የጀርመን የኤኮኖሚ እና ልማት ትብብር ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት የፕሮጀክቶቹ ትኩረት የዘር ማጥፋቱ ወንጀል ሰለባዎች ዝርያዎች ናቸው።በዚህም የመሬት ይዞታ ማሻሻያ እርሻ ውሀ የኃይል አቅርቦት እና የሙያ ስልጠናዎችንም ተካትቷል።ሆኖም ፕሮጀክቶቹ መቼ ስራ ላይ መዋል እንደሚጀምሩ ግን ግልጽ አይደለም።የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ እንዳሉት ግን እነዚህ እቅዶች የጋራ መግለጫው በሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከተፈረመ በኋላ ተግባራዊ ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል። አተገባበሩን በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተጨባጭ መረጃ ያልሰጡት ቃል አቀባይዋ ሆኖም መንግሥት በየጊዜው ከናሚብያ መንግሥት ጋር ውይይት በማካሄድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።የናሚቢያ መንግሥት የአሁኑ አቋሙ ደግሞ ግልጽ አይደለም።ከረቂቅ ስምምነቱ በኋላ በመስከረም 2021 በናሚብያ ፓርላማ በድርድሩ ውጤት ላይ ስሜታዊ ተቃውሞች ታይተዋል።መንግሥትም የረቂቅ ስምምነቱን ሰነድ ፓርላማው ድምጽ እንዲሰጥበት አላቀረበም። የጀርመን ፓርላማ በበኩሉ በሰነዱ ላይ ድምጽ የመስጠት እቅድ የለውም።መንግሥት ባወጣው መግለጫ ረቂቅ ሕጉ በዓለም አቀፍ ሕግ ስር የተደረገ ስምምነት አይደለም፤በጀርመን ፓርላማም መጽደቅ አያስፈልገውም ብሏል። የፓርላማ አባሉ ዳግዴለን ግን በመንግሥት አቋም ደስተኛ አይደሉም ።
«የጀርመን ፌደራል መንግሥት ፣የጀርመን የቅኝ አገዛዝ ዘመን ወታደሮች በዛሬይቱ ናሚብያ በሄሬሮና ናማዎች ላይ የፈጸሙትን ወንጀል፣ «ዘር ማጥፋት» ነው ሲል ከ100 ዓመታት በኋላ እውቅና መስጠቱ በጣም ዘግይቷል። ሆኖም ይህ ታሪካዊ ውሳኔ ከተደረገ በኋላ ከሕግ አንጻር ያን ያህል አስፈላጊ ባይሆንም ፓርላማው በዚህ ታሪካዊ ውሳኔ ላይ መነጋገሩ ከፖለቲካ አንጻር ከሚጠበቀውም በላይ ተገቢ ነው።ከፍተኛ ተምሳሌታዊ ኃይልም ይኖረዋል። »
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ