ያልተነገረላቸዉ የአፍሪቃ አንድነት መስራችና ዲፕሎማት
ሐሙስ፣ ግንቦት 24 2015ያልተነገረላቸዉ የአፍሪቃ አንድነት መስራችና ዲፕሎማት
«ስለአፍሪቃ አንድነት ድርጅት መቋቋም ታሪኩን ከኔ በላይ የሚያዉቅ ሰዉ የለም ብል አልተሳሳትኩም። ዋናዉ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ከተቋቋመ ጀምሮ የአፍሪቃ ሃገራት ነጻ መዉጣትን በጣም ነዉ ያፋጠነዉ። ምክንያቱም በስድሳዎቹ መጀመርያ የተባበሩት መንግስታት ጉባዔ ላይ የአፍሪቃ ሃገራት አንድነት እና ህብረት ጠንካራ እንደነበር ትዝ ይለኛል። በጣም በጣም የተጠናከረ ቡድን ነበር። ለአንድ አላማም የቁሙ ነበሩ። ይህ አላማ አፍሪቃዉያን ነጻ መዉጣት አለባቸዉ የሚል ነበር። ያን ግዜ አንድ ላይ ስለሆንን እኛን መከፋፈልም አልተቻለም ነበር። ስለዚህ አንድነታችን እና ድርጅቱ አስተዋጽኦ አድርጓል። ሌላዉ ደሞ፤ የአፍሪቃ መሪዎች ሌላዉ ቢቀር በዓመት አንድ ጊዜ በጋራ ተሰባስበዉ የአህጉርዋን ችግሮች፤መወያያ መድረክ ማግኘታቸዉ ትልቅ ስኬት ነዉ። ህብረቱ ችግሩ ላይ ዉሳኔ አገኘንም አላገኘም፤ መፍትሄ ማግኘቱ ግን ያጠራጠራል፤ ቢሆንም ግን በዓመት አንድ ጊዜ የአህጉሪቱ መሪዎቹ ተሰባስበዉ መወያየታቸዉ አንድ ትልቅ ስኬት ነዉ። የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የተቋቋመዉ ብዙ ሃገራት ነጻ በወጡ በሦስተኛዉ ዓመት ነዉ »
ከ 1953 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ተጠባባቂ ሚኒስትርነት በኋላም የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነዉ ለአስር ዓመት ያገለገሉት የተከበሩ ከተማ ይፍሩ ከተናገሩት ከማህደር የተወሰደ ቃል ነዉ። በንጉሱ ዘመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነዉ ያገለገሉት አቶ ከተማ ይፍሩ፤ ባገለገሉባቸዉ ዘመናት ሁሉ ኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ የዉጭ ተቀባይነት ያገኘችበት እና ንቁ ተሳታፊ የነበረችበት ዘመን እንደነበር ይነገራል። ከዚህ ሌላ የተከበሩ ከተማ ይፍሩ የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነዉ ሲያገለግሉ የአፍሪቃ የኢኮኖሚ ኮሚሽን ብሎም የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት እና ሁለቱም ተቋማት ዋና መቀመጫቸዉ ኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ላይ እንዲሆን ቀዳሚዉን እና ጠንካራዉን ሚና የተጫወቱ ዲፕሎማት ነበሩ። ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ በዚህ ተግባራቸዉ የኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ ጀግና ሲሉ ብዙዎች ያወድሷቸዋል። ትናንት ረቡዕ አዲስ አበባ ላይ « ከተማ ይፍሩ፤ የሰላም የዕድገት እና የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ » በሚል ርዕስ የክቡር ከተማ ይፍሩን የህይወት ታሪክ ብሎም፤ በአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ምስረታ የነበራቸዉን ጉልህ ሚና የሚያሳይ መጽሐፍ ተመርቆ ለአንባቢያን ቀርቧል። የኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ ጀግና የክቡር ከተማ ይፍሩን የጽሑፍ እና የድምፅ ማስታወሻዎችን፤ የሥራ ሰነዶችን፤ የተለያዩ የቀድሞ የአፍሪቃ መንግሥታት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን እና ባለሥልጣናትን በማነጋገር በመጽሐፍ መልክ ለአንባብያን ያቀረቡት የከተማ ይፍሩ የመጨረሻ ልጅ አቶ መኮንን ከተማ ናቸዉ። አቶ መኮንን በመረጃ ላይ የተመሰረት ሰነዶችን በማሰባሰብ ይህን መጽሐፍ ለአንባብያን ለማቅረብ 23 ዓመታት ወስዶባቸዋል።
«መጽሐፉ ያዉ የአባቴ ታሪክ ነዉ። የጻፍኩበት ምክንያቶች ብዙ ናቸዉ። ዋናዉ ግን አባቴ የሰራዉ ስራና ታሪክ ለቤተሰቡ፤ ለእናቴ ወይም ለወንድሞቼ ሳይሆን ለሃገሩ ብሎም ለአህጉር አፍሪቃ ነዉ። ይህን ትልቅ ታሪክ ይዘን መቀመጥ አንችልም። የዛሬ 23 ዓመት አፍሪቃ አንድነት ምስረታ ታሪክ ላይ ሰርቻለሁ፤ ይህን ታሪክ በመጽሐፍ ለማዉጣት ስሰራም 23 ዓመታት ፈጅቶብኛል። የታሪክ ምሁራን ስለአቶ ከተማ ይፍሩ መጥተዉ ይጠይቁኛል፤ መጽሐፍም ይጻፋሉ ብዬ ጠብቄ ነበር። ግን ማንም ባለመምጣቱና ባለመጠየቁ ራሴ መጻፍ ነበረብኝ። የአፍሪቃ ህብረትም የምስረታዉን በዓል ሲያከብር አባቴን አላስታወሰም፤ እናቴም አልተጋበዘችም። ሌላዉ አባቴ ከደሐ ገበሪ ተወልዶ እራሱን አሻሽሎ፤ ይህን ሁሉ ስራ መስራት ከቻለ ወጣቱን ትዉልድ ያበረታታል በሚል አስቤ ነዉ።»
የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ህብረት ተቋቁሞ ዋና ጽ/ቤቱ የት ይሁን የሚለዉ ጥያቄ በህብረቱ አባል ሃገራት መካከል ከፍተኛ ክርክር እና ዉዝግብ ያስነሳ ሂደት እንደነበር አቶ አቶ መኮንን ከተማ አጫዉተዉናል። በዚህም የዝያን ጊዜዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከተማ ይፍሩ፤ ወደ ተለያዩ አፍሪቃ ሃገራት ድርጅቱ በመጓዝ ዋና መቀመጫዉ ኢትዮጵያ ላይ እንዲሆን ብዙ ዉይይቶችን እና የማሳመን ሥራዎችን ሰርተዋል። ከዝያም የአፍሪቃ ሃገራት የድርጅቱ ዋና ጽ/ቤት አዲስ አበባ ላይ እንዲሆን ተስማሙ፤ አቶ ከተማ ይፍሩ ቆየት ብሎ የድርጅቱን ዋና ጽ/ ቤት ወደ አዲስ አበባ ለማምጣት ያደረጉትን ጥረት በተመለከተ ሲናገሩ፣ «ከዝያ እንቅስቃሴ ብዙ የተረዳሁት ነገር አለ። የሃገራችንን ፤ መጠናከር የሚፈልጉ እንዳሉ ሁሉ፤ ደካማ ሃገር እንድትሆን የሚሹ ብዙ መሆናቸዉንም አይቻለሁ፤ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት አዲስ አበባ ላይ መሆን ምን ጥቅም እንዳስገኘ ደግሞ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የያዘቸዉን ስፍራ የሚመለከት ሁሉ የሚፈርድ ይሆናል፤ ይህ ያለፈዉ የድካም ዉጤት ነዉ። በጎዉን ነገር አጠንክሮ መቀጠል ያለበት ደግሞ የዛሬዉ ትዉልድ ይመስለኛል» ሲሉ የተከበሩ አቶ ከተማ ይፍሩ መናገራቸዉ ተዘግቧል።
አቶ መኮንን ከተማ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ላይ እንዲሆን ስለመወሰኑ ሂደት በጥቂቱ አጫዉተዉናል።
«መጀመርያ ልክ ድርጅቱ እንደተመሰረተ፤ ዋና ጽ/ቤቱ አዲስ አበባ እንዲሆን ጠይቆ ነበር። የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት በቻርተሩ ጉዳይ እና ጽ/ ቤቱ የት ይሁን በሚለው ጥያቄ ላይ የናይጀርያዉ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጃጃ ዋቹኩ እና አቶ ከተማ አልተስማሙም ነበር።
የድርጅቱ ቻርተር እሳቸው አባል በሆኑበት የሞንሮቪያ ቡድን ቻርተር ጋር አንድ መሆን አለበት ብለው ተከራክረው ነበር። ኢትዮጵያ ያቀረበችው ቻርተር ግን ፀደቀ። በኋላ ደግሞ ጽ/ ቤቱ የት ይሁን ሲባል የሴኔጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዱዱ ቲያም ሴኔጋልን፤ የኮንጎ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኮንጎን፤ ናይጄሪያም እንዲሁ፤ አቶ ከተማ ደግሞ ኢትዮጵያን አቀረቡ። በመጨረሻ በጎርጎረሳዉያኑ 1964 ዓ.ም ላይ ዳካር ሴኔጋል ላይ የተሰበሰቡት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ከብዙ ልፋት በኋላ ኢትዮጵያን እንዲመርጡ ተደረገ። በሚቀጥለውም ግብፅ በተደረገው የመሪዎች ጉባዬ መሪዎቹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹን ውሳኔ አፀደቁ። ይህ ዉዝግብ መንግሥቱን በተለይም ንጉሱን በጣም አስጨነቋቸዉ ነበር። የኢትዮጵያዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማለትም አባቴ አቶ ከተማ ፤ ሁሉንም ለማሳመን ከፍተኛ ስራን ሰርቷል። ጥሩ ወዳጆችም ነበሩት። ለምሳሌ የአልጀርያዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኋላ የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት የሆኑት አብደል አዚዝ ቡቲፍሊካ ፤ የሴራሌዮን እና የጊኒ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ በተለይ የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ የነበሩት የጊኒዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲያሎ ቴሊን ሁሉን አሳምኖ ነዉ ከብዙ ትግል በኋላ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ጽ/ቤት አዲስ አበባ ላይ ለመሆን የበቃዉ። የአፍሪቃ ህብረት እስከዛሬ መቀመጫዉ አዲስ አበባ ላይ በመሆኑ እስከዛሬም ኢትዮጵያ እየተጠቀመች ነዉ።»
አቶ መኮንን ፤ የተከበሩ ከተማ ይፍሩ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሉ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ የአፍሪቃ ሃገሮች ከቅን ግዛት እንዲላቀቁ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸዉም ይነገራል?
«እዚህ ጉዳይ ላይ አባቴን የኢትዮጵያ ሬድዮ ጠይቆት አንድ የተናገረዉ ነገር አለ። አፍሪቃዉያን ወንድምና እንህቶቻችን ናቸዉ፤ የኛ የብቻ ነጻነት ዋጋ የለዉም ብሏል። አባቴ ለሃገሩ ብቻ ሳይሆን ለአህጉር አፍሪቃ የሚያስብ ፓን አፍሪካኒስት ነበር። የአፍሪቃን አንድነት ነበር ይዞ የሚጓዘዉ። አፍሪቃ ዉስጥ የሚታየዉ የዘር መድሎ ያበሳጫዉ ነበር። ያንን ነጻ ለማዉጣት ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረዉ ይህን ተፈጻሚ ለማድረግ ይሰራበት ነበር። ንጉሱም የአባቴን ሥራ አይተዉ ተቀየሩ። በኋላም አባቴን ይከተሉ ጀመር። እነ ኔልሰን ማንዴላ እንደ ኬኔት ካዉንዳ ያሉ የአፍሪቃ ታጋዮች እና ነፃ አዉጭዎችን ኢትዮጵያ እንድትረዳ ያደረገም አባቴ ነዉ። እነሱም መጨረሻ ላይ ከልብ አመስግነዋል።»
የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት መመስረት በቅኝ ግዛት ስር ለነበሩ ሃገሮች ነጻነት በአፋጣኝ እንዲመጣ እና እንዲቀዳጁ ረድቷል ሲሉ የተከበሩ ከተማ ይፍሩ ቀደም ብለዉ ተናግረዉ ነበር።
«የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ከተመሰረተ ጀምሮ የአፍሪቃ ሃገሮች ነጻ መዉጣትን በጣም ነዉ ያፋጠነዉ። ትዝ ይለኛል በ 60ዎቹ መጀመርያ ላይ በተባበሩት መንግስታት ጉባዔ ላይ፤ የአፍሪቃ ሃገራት አንድነት በጣም የተጠናከረ ነበር። ለአንድ አላማ ቆመን ነበር። ይህ አላማችን የነበረዉ አፍሪቃዉያን በሙሉ ነጻ መዉጣት አለባቸዉ የሚል ነበር። አንድ ላይ ስንሆን ሊከፋፍሉ የፈለጉ ሃገሮች መከፋፈል አልተቻለም ነበር። ስለዚህ ያ አንድ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።»
(ከተማ ይፍሩ፤ የሰላም የዕድገት እና የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ) ሲሉ አቶ መኮንን ላንባቢ ያቀረቡት መጽሐፍ ረቡዕ ግንቦት 23 ቀን 2015 ዓ.ም ሲመረቅ፤ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ በሻህ ከተጋባዥ እንግዶች መካከል አንዱ ነበሩ። ስለ አቶ ከተማ ይፍሩ የሚተርከዉንም መጽሐፍ አንብበዉታል።
«አዎ መጽሐፉን አንብቤያለሁ። ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸዉ ብርቅዬ ልጆች አንዱ ናቸዉ። በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስርያ ቤት ለአስር ዓመታት ነዉ ያገለገሉት። የከተማ ይፍሩ የመጨረሻ ልጅ አቶ መኮንን፤ « ከተማ ይፍሩ፤ የሰላም የዕድገት እና የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ » በሚል ርዕስ በቁጭት ግሩም መጽሐፍ ጽፏል። ሰነዶችን አገላብጦ ይህን መጽሐፍ ለአንባቢ ለማቅረብ 23 ዓመታት ፈጅቶበታል።
ፕሮፌሰር ብሩክ መጽሐፉን እንዴት አገኙትት? በመጽሐፉ የተከበሩ ከተማ ይፍሩን የህይወት ታሪክ ብሎም ያራመዱትን ፓን አፍሪካኒዝምን አገኙበት?
«አዎ አግንቼበታለሁ፤ ታሪኩ የሚጀምረዉ የከተማ ይፍሩን ትዉለድ እድገት እና የትምህርት ደረጃን በመተረክ ነዉ። . . . »
አቶ መኮንን ከተማ እና ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ በሻህ ለሰጡን ቃለ ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም በማመስገን ፤ ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን!
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ