አዲስ አበባ፤ ኢሰመኮ በአማራ ክልል በአየርንና በከባድ መሣሪያ ጥቃት ሲቪሎች መገደላቸውን ገለጸ
የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በሰው አልባ አውሮፕላን እና በከባድ ጦር መሣሪያ ጥቃት ሲቪሎች መገደላቸውን አመለከተ። ኮሚሽኑ በዛሬ መግለጫው በአማራ ክልል ወራትን ባስቆጠረው በመንግሥት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በቀጠለው ውጊያ በርካቶችም ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እና ከመኖሪያ አካባቢያቸውም መፈናቀላቸውን ገልጿል። ኢሰመኮ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ሰሜን ሸዋ ዞን በረኸት ወረዳ፤ መጥተህ ብላ በተባለ ከተማ በተፈጸመ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት አንድ ሕጻንን ጨምሮ በርካታ ሲቪሎች መገደላቸውን፤ የአካል ጉዳትም እንደደረሰ ዘርዝሯል። በዚሁ ዓመት ጥቅምት 8 ቀን ደግሞ በደብረ ማርቆስ ከተማም በተመሳሳይ ጥቃት ስምንት ሲቪሎች እንደተገደሉ፤ በደንበጫ ከተማ ደግሞ ጥቅምት 3 ቀን በከባድ መሳሪያ ድብደባ ሲቪሎች መሞታቸውን፤ የተጎዱ እንዳሉ የአካባቢውን ነዋሪዎች በዓይን ምስክርነት ጠቅሷል። በኢሰመኮ የሕግ እና ፖሊሲ ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ታሪኳ ጌታቸው ለዶቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ የአየርም ሆነ የከባድ መሣሪያ ድብደባዎች በማንኛውም ወገን ላይ ልዩነት እንደማያደርጉ ነው ያስገነዘቡት።
በአንዳንድ አካባቢዎች ጥቃት፤ አልያም ግጭትን በመሸሽ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የገለጸው ኢሰመኮ፤ የተወሰነ ድጋፍ በማኅበረሰቡ እና በአንድ ተራድኦ ድርጅት ቢደረግም በቂ ባለመሆኑ በአሳሳቢ ሁኔታ እንደሚገኙ አስታውቋል። ግጭት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የመንግሥት የጸጥታ አካላት በመንገድ ላይ ወይም ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ ከያዟቸው በርካታ ሲቪል ሰዎች ውስጥ «ፋኖን ትደግፋላችሁ፣ ለፋኖ መረጃ ትሰጣላችሁ፣ መሣሪያ አምጡ፣ የተኩስ ድምፅ ስለተሰማበት አቅጣጫ መረጃ ስጡ» በሚልና ይህንን በመሰሉ ምክንያቶች ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች መፈጸማቸውን የሚያሳዩ ተአማኒ መረጃዎች ለኮሚሽኑ እንደደረሰም መግለጫው ዘርዝሯል።
ሀዋሳ፤ ኮንታ ዞን በተከሰተ የመሬት መንሸራተት የሰዎች ሕይወት አለፈ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንታ ዞን በተከሰተ የመሬት መንሸራተት የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሦስት ሰዎች ሕይወት አለፈ። አደጋው ትናንት እሑድ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ በዞኑ አመያ ዙሪያ ወረዳ ኦፓላሸ በተባለ ቀበሌ ውስጥ መከሰቱን የኮንታ ዞን መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። በአካባቢው የጣለውን ዝናብ ተከትሎ በደረሰው የመሬት መናድ የአንድ እናትና የሁለት ልጆቿ ሕይወት ማለፍን ነው የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አበበ ጎበና ለዶቼ ቬለ የገለጹት።
የመሬት መንሸራተቱ በተጨማሪ 25 አባዎራዎችን ከቤት ንብረታቸው ማፈናቀሉን እና በ5.5 ሄክታር ማሳ ላይ የነበረ ሰብል ማውደሙንም የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ተናግረዋል። ሰሞኑን በአካባቢው እየጣለ የሚገኘው ዝናብ ጎርፍ፣ የመሬት ናዳና መሠል ጉዳቶች ሊያስከትል ስለሚችልም ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሃላፊው ማሳሰባቸውን ከሀዋሳ ሸዋንግዛው ወጋየሁ በላከው ዜና አመልክቷል።
ኻርቱም፤ የሱዳን ኃይሎች ድርድርና የጠለው ውጊያ
የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች መሪዎች ለሰላም ድርድር ሳውድ አረቢያ ውስጥ እየተነጋገሩ መሆኑ ቢገለጽም ውጊያው በሀገሪቱ መቀጠሉ እየተነገረ ነው። የሱዳን ጦር ኃይል በዋና ከተማ ኻርቱም ጎዳናዎችን የተቆጣጠረውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል በአየር ጥቃት ጭምር ከከተማዋ ማስወጣት አለመቻሉን ዘገባዎች ያመለክታሉ። የፈጥኖ ደራሹ ኃይል አውሮፕላን ማረፊያም ሆነ የባቡር መስመር እና ዋና የተሽከርካሪ መመላለሻ ያላትን ኒያላ ከተማን በቁጥጥሩ ስር ማድረጉን አስታውቋል። ባለፉት ሦስት ወራት ከማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ የሚያዋስነው የወደብ አካባቢ የያዘው ይኽ ቡድን አስፈላጊ አቅርቦቶችን የሚያገኝበት መስመር እንደሆነም ነው የተገለጸው። ከሚያዝያ ጀምሮ በሁለቱ ተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል በቀጠለው ውጊያ ከዘጠኝ ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸው፤ ከስድስት ሚሊየን የሚበልጥ ሕዝብም መፈናቀሉን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ባለፈው ሳምንት ጄዳ ላይ በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች መካከል የተጀመረው የሰላም ውይይት የተኩስ አቁም እና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ስምምነት ለማስገኘት መሆኑን ከአሸማጋዮቹ ከሳውዲ እና አሜሪካ በኩል ትናንት ይፋ ሆኗል። ከሁለቱም ሃገራት የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ድርድሩን አስመልክቶ ይፋ የሆነው መግለጫ፤ ንግግሩ ሰፋ ያሉ የፖለቲካ ጉዳዮችን እንደማይመለከት ማስታወቁን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ በዘገባው ጠቅሷል።
በርሊን፤ ሀምቡርግ ከተማ አምስት ሰዎች ሞቱ
በሰሜናዊ ጀርመን ከተማ ሀምቡርግ በሕንጻ ግንባታ ስፍራ በደረሰ አደጋ አምስት ሰዎች ሞቱ። ሌሎች በርካቶችም የገቡበት አልታወቀም። በስፍራው ሕይወት ለማዳን የደረሰው የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ብርጌድ ቃል አቀባይ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ዛሬ ጠዋት ሲሆን የአደጋው ምክንያት አልታወቀም። ቃል አቀባይ ፊሊፕ ባውም፤
«በወደብ ከተማዋ ቺካጎ ጎዳና ላይ ነው የምንገኘው። በሕንጻ ግንባታ ስፍራ ዛሬ ማለዳ ነው አደጋው የተከሰተው። ከስምንተኛ ፎቅ ነው የአሳንሰር መደገፊያው የወደቀው፤ በዚህ ስፍራ በሥራ ላይ የነበሩ በርካቶች ተቀብረዋል። በአሁኑ ሰዓት በጣም አስቸጋሪ ቴክኒክ የተከተለ የማዳን ሥራ ጥረት እየተደረገ ነው። እስካሁን ለመሞታቸው ግልጽ ምልክት ያሳዩ አምስት ሰዎችን ማግኘታችንን መናገር እንችላለን። እስካሁንም ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች ገና አልተገኙም፤ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ቴክኒካዊ የማዳን ሥራቸውን በማከናወን ላይ ናቸው።»
የሕንጻ ግንባው ሠራተኞች በወቅቱ አሳንሰር በመገንባት ላይ እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን ለግንባታው የተገጣጠመው ጊዜያዊ መደገፊያው የወደቀው ቢያንስ ስምንት በሚሆኑት ሠራተኞች ላይ ነው። 70 የሚሆኑ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በወደቀው ጊዜያዊ መደገፊያ የተጎዱትን ለማውጣት፤ ያልተገኙትንም ለመፈለግ በስፍራው መሰማራታቸው ተመልክቷል። አደጋው መድረሱን ተከትሎ በግንባታው አካባቢ በሥራ ላይ የነበሩ 700 የሚሆኑት ሠራተኞች ከስፍራው ዘወር መደረጋቸው ተገልጿል።
ጋዛ፤ የእስራኤል ጦር ወደጋዛ መግፋት፤ የጀርመን ማሳሰቢያ
የእስራኤል ወታደሮች እና ታንኮች በዛሬው ዕለት ወደ ጋዛ በሁለት አቅጣጫ ገፍተው በመግባት ላይ መሆናቸው ተዘገበ። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰራጨ ቪዲዮ የእስራኤል ታንኮች እና ቡልዶዘር ማዕከላዊ ጋዛ ውስጥ የሰሜንና ደቡብ መገናኛ ዋና መንገድን መዝጋታቸውን ማሳየቱን አሶሲየትድ ፕረስ በዘገባው ጠቅሷል። እንደዘገባው አካባቢው ቀደም ሲል የእስራኤል ጦር ኃይል ጥቃት ከመጀመሩ አስቀድሞ የአካባቢው ነዋሪዎች ከስፍራው እንዲወጡበት ያመላከተው መስመር ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለም ጀርመን በዛሬው ዕለት በተጠናከረው የጋዛ ጥቃት እስራኤል በምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ባለው አካባቢ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን ከለላ እንድታደርግ ጥሪ አቅርቧል። እስካሁን በአካባቢው በሺህዎች የሚቆጠሩ መገደላቸው እየተነገረ ነው። በተያያዘ ዜና እስራኤል ለመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ OCHA ሃላፊ ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ ዛሬ ፈቃድ መስጠቷ ተሰምቷል። የOCHA ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ ወደ እስራኤል ለመግባት ከጠየቁ ሦስት ሳምንት እንዳለፋቸው ነው የተገለጸው። የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይን ጠቅሶ የጀርመን የዜና ወኪል ዲፒኤ እንደዘገበው፤ የይለፍ ፈቃዱ የተሰጣቸው በሌሎች መንግሥታት ጥያቄ ጭምር ነው።
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ