1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥምቀት በአል ዝግጅትና ሥጋቱ በጎንደር

ረቡዕ፣ ጥር 8 2016

በዓሉ በድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች መካከል የጎንደር ከተማ አንዱ ነው፡፡ የዘንድሮውን የጥምቀን በዓል እንደተለመደው በጎንደር ከተማ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ቢሆንም አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ግን ወቅታዊው የፀጥታው ሁኔታና ሌሎች ሰሞናዊ ጉዳዮች በዓሉ በአደባባይ እንዳይከበር ሊያደርጉት ይችላሉ የሚል ስጋት አድሮባቸዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4bN37
የ2012 ጎንደር ከተማ ዉስጥ የተከበረዉ የጥምቀት በአል በከፊል
የጥምቀት በአል ጎንደር ከተማ ዉስጥ ከዚሕ ቀደም በደማቅ ሥርዓት ባደባባይ ይከበራልምስል DW/T. Endalamaw

የጥምቀት በአል በጎንደር ዝግጅትና ሥጋቱ

የዘንድሮዉየጥምቀት በዓል ጎንደር ከተማ በሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ዘንድ በድምቀትና በአደባባይ እንደሚከበር የሐይማኖት መሪዎችና የመንግስት ባለስልጣናት አስታወቁ።የከተማይቱ ባለሥልጣናት እንደሚሉት በዓሉን ከዚሕ ቀደም በሚደረገዉ ሥርዓት ለማክበር ዝግጁቱ ተጠናቅቋል። ይሁንና ከጎንደር ከተማ ነዋሪዎች አንዳዶቹ በከተማይቱና ባካባቢዋ ባለዉ የፀጥታ መታወክ ምክንዓት በዓሉ በአደባባይ ላይከበር ይችላል የሚል ስጋት አሳድሮባቸዋል፡፡

የጥምቀት በዓል እየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጥምቁ ዮሐንስ የተጠመቀበትን እለት ምክንት በማድረግ በየዓመቱ ጥር 11 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስተያን አማኞች ዘንድ በመላ አገሪቱ ይከበራል፡፡

በዓሉ በድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች መካከል የጎንደር ከተማ አንዱ ነው፡፡ የዘንድሮውን የጥምቀን በዓል እንደተለመደው በጎንደር ከተማ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ቢሆንም አንዳንድ የከተማዋ  ነዋሪዎች ግን ወቅታዊው የፀጥታው ሁኔታና ሌሎች ሰሞናዊ ጉዳዮች በዓሉ በአደባባይ እንዳይከበር ሊያደርጉት ይችላሉ የሚል ስጋት አድሮባቸዋል፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎች አንዱ እንዲህ ብለዋል፣

“ሰው ለማክበር ፈፅሞ ዝግጅት አላደረገም፣ መንግስት ግን ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር እንግዳ የለም፣ ሰውም ለማክበር ሙሉ ፍላጎት የለውም፣ እንደማይከበር ነው የሚያሳየው ብዙ የምትጠይቀው ሰው እንደማይከበር ነው የሚነግርህ”

ሌላ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የጎንደር ከተማ ነዋሪም፣ ብዙ በዓሉን የሚመለከቱ ነገሮች በከተማው አይታዩም፣ አውዱም ቢሆን የዓመት በዓል አውድ አይመስልም ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል በዓሉ እንደ በፊቱ ሁሉ አሁንም በድምቀት እንደሚከበርና በዓሉን የተመለከቱ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ደግሞ ሌላ የከተማዋ ነዋሪ አመልክተዋል፣ ሆቴልች ሙሉ ዝግጅት አድርገዋል፣ ወጣቶች በኮሚቴ እተዋቀሩ ስራዎችን እየሰሩ እንደሆነ ነው የገለፁት፡፡፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ተከታዮች ዘንድ የሚከበረዉ ጥምቀት ጎንደር ዉስጥ በድምቀት ይከበራል
የጥምቀት በአል አከባበር በጎንደር ከተማ 2011ምስል picture-alliance/Bildagentur-online/AGF-Masci

የፀጥታ ስጋት እንዳለ የሚገልፁ ሌላ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ሰላም ከሆነ በዓሉ ሊከበር ይችለል፣ ካልሆነ ግን አከባበሩ በየቤተ ክርስቲያናቱ አውደ ምህረት ይከበራል የሚል ሀሳብ እንዳላቸው ገልጠዋል፡፡

የጎንድር ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ ላቀው የጥምቀትን በዓል በጎንደር ከተማ እንደተለመደው በድምቀት ለማክበር ሁሉም ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ለዶይቼ ቬሌ በስልክ ተናግረዋል፡፡ በከተማው አሁን አስተማማኝ ሰላም አለ የሚሉት አቶ አበበ፣ የፀጥታ ዘርፉም እንግዶች በሰላም በዓሉን እንዲያከብሩ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል  ብፁዕ   አቡነ ዮሐንስ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙሐን በሰጡት መግለጫ በዓሉ በአደባባይ እንደሚከበር አመልክተዋል፡፡ በዓሉ አይከበርም እየተባለ የሚነገረው ውዥንብር ሀሰት ነው በዓሉ በአደባባይ ይከበራል ሲሉ ለዶይቼ ቬሌ ገልጠዋል፡፡

ጥምቀት በኢትዮጵያ በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት አንዱ ሲሆን ከጥቂት ዓመታት በፊት በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ድርጅት (UNESCO)  በማይዳሰሱ የዓለም ቅርስነት መዝግቦታል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ