በንዴት ቆሽቴ ደበነ ሲባል እንሰማለን። ቆሽት በንዴት እንደተባለው ለጉዳት ይዳረግ ይሆን? «ሥጋ ቁጠር ቢሉት ጣፊያ» ተብሎም ይተረታል። ይህን የውስጥ አካል ክፍል ጤና የሚያቃውሰው ምን ይሆን?
በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙ አካል ክፍሎች በተፈጥሮ አቀማመጥም ሆነ በሕይወት የመኖራችን ሂደት እንዲቀጥል በማድረጉ በኩል አንዳቸው ከሌላቸው በአገልግሎት የመተባበራቸውን ያህል የአንዱ ጤና መታወክ የሌላኛውም ጉዳት የሚሆንበት አጋጣሚ ይኖራል። አንዳንዱ የሰውነት የውስጥ ክፍል በጤና እክል ተወግዶ አይደለም አገልግሎቱ ቢስተጓጎል በሕይወት መኖር ታሪክ ይሆናል። በአንፃሩ ይህ ቢወገድ ይሻላል ተብሎ የሚወሰንበት ተወግዶም ታማሚው በጤና ለመኖር የማይቸገርበት የውስጥ አካል ክፍል እንዳለ ሀኪሞች ያስረዳሉ። ከአድማጭ የተላከልንን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የጉበት፣ የሃሞት እና የቆሽት ቀዶ ህክምና ባለሙያ፤ በአዳማ ዩኒቨርስቲ የህክምና ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ይታገሱ አበራ፤ ጣፊያ የምንለውን የአካል ክፍል ቆሽት ከሚባለው ጋር እያለዋወጡ የመረዳት ነገር ሊኖር እንደሚችል ነው ያስረዱን።