1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጊዜው ወደ ህክምና መሄድ፤ የጡት ካንሰርን የተቋቋሙ እናቶች ምክር

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 20 2016

ካንሰር ስሙ ብቻ ሰዎችን እያስደነገጠ የብዙዎችን ተስፋ በቀላሉ አትንኖ ከህመሙ ባሻገር በስነልቡና ኹከት ለጉዳት መዳረጉን በውስጡ ያለፉት እማኝ እንግዶቻችን ይናገራሉ። ዛሬ እነሱ ሌሎችን በምክር እያገለገሉ ብዙዎች ሊያደርጉት የሚገባውን አስቀድመው መንገድ ለማመላከት በፈቃደኝነት ተሰማርተዋል።

https://p.dw.com/p/4YFZ1
ፎቶ ከማሕደር የጡት ካንሰር ምርመራ
ስለጡት ካንሰር ሰዎችን የማንቃቱ ሃሳብ የተጀመረው በጎርጎሪዮሳዊው 1985 ዓም በአሜሪካ የካንሰር ማኅበረሰብ እና የኢምፔሪያል ኬሚካል ኢንዱስትሪ የመድኃኒት ቅመማ ዘርፍ በጋራ በጀመሩት የትብብር ሥራ ነው። ፎቶ ከማሕደር የጡት ካንሰር ምርመራ ምስል Monique Wuestenhagen/Themendienst/dpa/picture alliance

የእማኞች ተሞክሮ እና ምክር

በየዓመቱ በጥቅምት ወር በመላው ዓለም ስለጡት ካንሰር ሰዎች በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ የማንቂያ ዝግጅቶች እና እንቅስቃሴዎች ይከናወናሉ። ስለጡት ካንሰር ሰዎችን የማንቃቱ ሃሳብ የተጀመረው በጎርጎሪዮሳዊው 1985 ዓም በአሜሪካ የካንሰር ማኅበረሰብ እና የኢምፔሪያል ኬሚካል ኢንዱስትሪ የመድኃኒት ቅመማ ዘርፍ በጋራ በጀመሩት የትብብር ሥራ ነው። ዓላማው ሰዎች ስለህመሙ ምንነት፤ አስቀድሞ ሊወሰድ ስለሚገባው እርምጃ እና የመሳሰሉትን እንዲረዱ እና በየበኩላቸውም ለከፋ ሁኔታ ከመጋለጣቸው አስቀድመው እንዲጠነቀቁ ማንቃት ነው። 

ስለጡት ካንሰር ታክመው የዳኑት የበጎ ፈቃደኞች እማኝነት

ወ/ሮ እመቤት አስፋው የጡት ካንሰርን አሸንፈው ለሌሎች አርአያ የሆኑ የሦስት ልጆች እናት። ወይዘሮዋ ስለካንሰር ህመም በተለይም ስለጡት ካንሰር ቅድመ ጥንቃቄና የመሳሰሉ መረጃዎችን ከመገናኛ ብዙሃን የማድመጥ አጋጣሚው ቢኖራቸውም፤ ከግል ልምዱ ሊያጋራቸው የሚችል ሰው ግን ማግኘት አልቻሉም ነበር። ከመገናኛ ብዙሃን በሰሙት መረጃ መሰረት ግን በየጊዜው ጡታቸውን ይፈትሹ ነበርና ያልተለመደ ነገር አጋጠማቸው፤ ወደ ሀኪምም ሄዱ። ህክምናውን ለመጀመርም አላመነቱም።

በዚህ ውስጥ ማለፉ ዛሬ ላይ ቆመው ወደ ኋላ መለስ ብለው ሲተርኩት ቀላል ይምሰል እንጂ በወቅቱ ያሳለፏቸው ቀናት የሚያልፉ እንደማይመስሉ ነው የሚያስታውሱት። ህክምናውን ደረጃ በደረጃ አጠናቀው፤ በሀኪማቸው አማካኝነት ለካንሰር ታማሚዎች የመረጃ መለዋወጫ ወደሆነው መድረክ ወይም ስብስብም ገቡ። በየወሩ የጡት ካንሰር ህሙማን እየተሰባሰቡም ከመረጃ መለዋወጥ በተጨማሪ የምክር አገልግሎት ያገኛሉ። ለዚህም በአዳማ ሆስፒታል የህክምና ኮሌጅ የካንሰር ህክምና ከፍተኛ ባለሙያና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ቢንያም ተፈራ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ነው ወ/ሮ እመቤት የሚናገሩት።

ፎቶ ከማሕደር፤ በግል የሚደረግ የጡት ካንሰር ፍተሻ
የጡት ካንሰር ቁጥሩ ይለያይ እንጂ ወንዶችንም ሊያጠቃ እንደሚችል የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለዚህም ሁሉም በየጊዜው በየግሉ ፍተሻ ማድረግ እንደሚኖርበት ይመክራሉ። ፎቶ ከማሕደር፤ በግል የሚደረግ የጡት ካንሰር ፍተሻምስል Bo Valentino/Zoonar/picture alliance

ወ/ሮ እመቤት እንደገለጹልን እሳቸው ለጡት ካንሰር መጋለጣቸውን ባወቁበት አጋጣሚ የራሱን ልምድ ሊካፍላቸው የሚችል ከዚህ ህመም የዳነ ሰው አላገኙም ነበር። በመገናኛ ብዙሃን ስለጡት ካንሰር የሚተላለፉ መረጃዎች እና ምክሮችን ግን የማዳመጥ ዕድሉ ነበራቸው። በዶክተር ቢንያም አማካኝነት የካንሰር ህሙማን እርስ በርስ መረጃ መለዋወጥ እንዲችሉ የተመሰረተው ስብስብ አሁን ለብዙዎች ትርጉም ያለው አገልግሎት የሚያገኙበት መድረክ መሆን ችሏል።

በዚህ ማኅበር  አማካኝነት የመረጃ እና የምክር አገልግሎት ከሚያገኙት አብዛኞቹ ህመሙ ከጠናባቸው በኋላ ወደ ህክምና የመጡ ናቸው። እንዲህ ባለው የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት በተለያዩ መንገዶች ሰዎች ስለጡት ካንሰር ያላቸው ግንዛቤ እንዲዳብር ከሚያግዙት አንዷ ወ/ሮ መሠረት ዳባ ሲሆኑ ዘግይተው ወደ ህክምናው ከሄዱት አንዷ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ለካንሰር ህሙማን የምክር አገልግሎት የሚሰጠው ማኅበር

በሙያቸው መምህርት የሆኑት የ57 ዓመቷ ወይዘሮ፤ እሳቸው በህክምናው ሂደት ያሳለፉትን አስቸጋሪ ጊዜያት ሌሎችም እንደሚያጋጥማቸው በመረዳት፤ ሰዎች የጡት ካንሰር ስር ሳይሰድ ወደ ህክምና መሄድ እንዳለባቸው በዕድርም ሆነ በተለያዩ የመሰባሰቢያ መድረኮች ከልምዳቸው በማካፈል ላይ ናቸው። እነዚህ የራሳቸውን የሕይወት ተሞክሮ ለሌሎች መማሪያ ለማድረግ እየተጉ የሚገኙ እናቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የካንሰር ህክምናን በተመለከተ ያሉ ችግሮችን ጠንቅቀው በመረዳታቸው የተሰባሰቡበት ማሕበር አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ወ/ሮ እመቤት ገልጸዋል።

ወ/ሮ እመቤት ከጡት ካንሰር ከዳኑ አምስት ዓመት ሊሆናቸው እንደሆነ ይናገራሉ። በዚህ ማህበር ውስጥም ላለፉት አራት ዓመታት በአስተባባሪነት በበጎ ፈቃድ እያገለገሉ ነው። በየቀኑ ሀኪም ቤት በመታከም ላይ ያሉትን እየጎበኙ ማበረታታት የየዕለት ተግባራቸው ሆኗል። ማኅበሩ በየወሩ በሚያካሂደው ስብሰባ እስከ መቶ የሚደርሱ በዕድሜም ሆነ በኑሮ ደረጃ የተለያዩ ወገኖች በየጊዜው እንደሚመጡና መረጃ ይለዋወጣሉ። የችግሩን ስፋት በማሰብም በየክልሉ ተመሳሳይ ማህበራን ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑንም ገልጸውልናል።  ወ/ሮ መሠረት ሌሎችን ለማስተማርና ለማንቃት የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ ይበልጥ ብዙ መሠራት አለበት ባይ ናቸው።

 ፎቶ ከማኅደር፤ አዳማ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል
የጡት ካንሰር ታማሚዎች ስለህመሙ በቂ መረጃ ማግኘት እንዲችሉ ማኅበር መመስረት ያስቻሉት የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ከፍተኛ የካንሰር ህክምና ባለሙያ እንደሆኑ እማኖቹ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። ፎቶ ከማኅደር፤ አዳማ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታልምስል Biruck Habtamu/Adama University Hospital

ለሁሉም የሚሆን ምክር

ወ/ሮ እመቤትም ሆኑ ወ/ሮ መሠረት ምክራቸው ተመሳሳይ ነው። የሰውነታችሁን ለውጥ ተከታተሉ፤ የተለየ ነገር ስታስተውሉም ፈጠን ብላችሁ ወደ ሀኪም ሂዱ የሚል። እነዚህ ሁለት ከጡት ካንሰር ለመዳን ችለው የየግላቸውን ተሞክሮ በበጎ ፈቃደኝነት ለሌሎች በማስረዳት ተግባር የተሰማሩ እናቶች ደጋግመው እያመሰገኑ ስማቸውን ያነሷቸው የካንሰር ከፍተኛ የህክምና ባለሙያው ዶክተር ቢንያም ከዚህ ቀደም የዚህ ዝግጅት እንግዳ ነበሩ። ሙያዊ አስተዋጽኦና ድካማቸው ፍሬ ማፍራት መጀመሩ ተስፋ የሚሰጥ ነው። የመገናኛ ብዙሃን ቅሰቃሳም ያለው ሚና ሳይዘነጋ። እርግጥ ነው ካንሰር ለዘመናዊው ህክምናም ቢሆን ፈታኝ መሆኑ ይነገርለታል፤ ችግሩ የሚባባሰው ግን ለህክምናው በመዘግየት መሆኑን በመረዳት ቢያንስ በሰው እውቀት እና አቅም ሊደረግ የሚችለውን አስቀድሞ ማድረጉ ይመከራል። አድማጮች ለሌሎች መልካም አርአያ በመሆን የግል ተሞክሯቸውን ያካፈሉንን የዕለቱን እንግዶቻችንን በማመስገን ስለጡት ካንሰር ያጠናቀርነውን በዚሁ አበቃን። ጥያቄም ሆነ ተመሳሳይ ተሞክሯችሁን ብትልኩልን ለማስተናገድ ዝግጁ ነን።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ