የጠናው የሙቀት ማዕበል
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 16 2016
ከ40 ዲግሪ በላይ የተመዘገበው ሙቀት
የደቡባዊ አውሮጳ ሃገራት ሙቀቱ ካየለባቸው ሳምንታት ተቆጥተዋል። ስፔን እና ግሪክን ጨምሮ አብዛኞቹ ከ40 ዲግሪ በላይ የደረሰውን ሙቀት እያስተናገዱ ነው። የስፔን ብሔራዊ የአየር ትንበያ አገልግሎት እንደሚለው ከሆነ ከወደ አፍሪቃ የመጣው ሞቃት አየር ነው የአካባቢውን የበጋ ሙቀት ያባባሰው። በዚህም ምክንያት ባለፈው ዓርብና ቅዳሜ ሳራጎሳን ጨምሮ በአንዳንድ የስፔን ከተሞች የሙቀት መጠኑ 44 ዲግሪ በላይ መድረሱን አመልክቷል። ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት ሙቀቱ ማድሪድ ከተማ ላይ 47 ዲግሪ ደርሷል። በዕለቱ እኩለ ቀን አልፎ ከተማዋን እየጎበኘት ሳለች የምትጠጣውን ቀዝቃዛ ውኃ የገዛችው ቱሪስት ሊዳ ሳላዛር ሙቀቱ የፈጠረባትን እንዲህ ትገልጻለች።
«በጣም ይሞቃል፤ ማድሪድን በመጎብኘት ላይ ነኝ። የቀለጥኩ ያህል ይሰማኛል! ቦረዶ ነገር እፈልጋለሁ። በዚያ ላይ የማታው ስላለቀቀኝ ዞሮብኛል። የሁለት መጥፎ ነገሮች ውህድ ተጫጭኖኛል።»
ከፔሩ የመጣው ሌላኛው የ19 ዓመቱ ሀገር ጎብኚ ኮሲዮሲዮ ሜዛም ሙቀቱን መቋቋም አለመቻሉን ይናገራል።
«ሙቀቱ በጣም ከባድ ነው። ውኃ ባለበት ቦታ በደረስኩ ቁጥር ጠርሙሴን እሞላለሁ።»
ጣሊያንም እንዲሁ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ሙቀት እያስተናገዱ ካሉ የደቡብ አውሮጳ ሃገራት አንዷ ናት። የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ባለፈው ዓርብ ዕለት በቀጣዩ ቀን ቅዳሜ 11 ከተሞች የሙቀቱ መጠኑ በጣም ከፍ እንደሚል አስጠንቅቆ ነበር። ደቡባዊ ጣሊያን ውስጥ የሚኖሩ አንዲት ኢትዮጵያ በጽሑፍ በላኩልን መልእክት እሳቸው የሚኖሩበት አቅራቢያ ባሕር በመኖሩ የሙቀት መጠኑ 37 እና 38 ዲግሪ ቢሆንም በሌሎች አካባቢዎች ከ40 እስከ 45 ዲግሪ መድረሱን ገልጸውልናል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከፍተኛው የአየር ግፊት ጣሊያን ውስጥ የሙቀቱን መጠን ከፍ ከማድረጉ በተጨማሪ እርጥበት አዘሉ ሞቃት አየር ተጨማሪ ጫና ፈጥሯል።
በተመሳሳይ ከ40 ዲግሪ በላይ ከሆነው የሙቀት መጠን ጋር እየታገለች በምትገኘው ግሪክ መሰንበቻውን ከነበረው አንጻር ሲታይ ዛሬ በመጠኑ መለስ ማለቱን ያነጋገርናቸው አቴንስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገልጸውልናል። ግሪክ አብዛኛው ከተሞቿ ደሴቶች በመሆናቸው ከከበባቸው ባሕር የሚነፍሰው አየር ሙቀቱን ለመቋቋም እንዲችሉ ማገዙንም ይናገራሉ።
የኃይለኛው ሙቀት ጫና
በርካታ ሀገር ጎብኚዎች በሚጎርፉባት ዋና ከተማ አንቴን ባለፉት ሳምንታት የጠናው ሙቀት አንዳንድ የቱሪስት መስህብ የሆኑ ስፍራዎች ባልተለመደ ሁኔታ ቀን ተዘግተው ለጎብኚዎች ማታ እንዲከፈቱ አስገድዷል። እንዲያም ሆኖ ምንም እንኳን የሙቀቱ መጠን ከረፋዱ አንስቶ እስከ ቀትር በኋላ ባሉት ሰዓት ቢብስም ማምሻውን ጭምር አለመቀነሱ በተለይ በዕድሜ የገፉ እና ሕጻናትን ለጉዳት መዳረጉን ዘገባዎች ያመለክታሉ። በደቡባዊ አውሮጳ በተለይ በሜዲትራንያን ባሕር ካሉት ሃገራትም ግሪክ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ እንደጠናባት ነው የሚገለጸው። በግሪክ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የደን ቃጠሎ፣ የውኃ እጥረት፤ የማያቋርጥ ድርቅ እንዲሁም ጎርፍ እየተከሰተ ነው።
አቴንስ የሚኖሩ የመረጃ ምንጫችን እንደገለጹልን በተለይ ያለፈው የክረምት ወቅት ከዚህ በፊት የተለመደው ዓይነት ቀዝቃዛ አልነበረም። ክረምቱ መውጣቱን ተከትሎም ሙቀቱእየጨመረ መሄዱን ነው የነገሩን። በተለይ ባለፉት ሳምንታት የሙቀቱ መጠን ከ40 ዲግሪ በላይ እንደነበርም ገልጸዋል።
ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የግሪክ የአየር ሁኔታ አገልግሎት ኃላፊ ቴዎዶሮስ ኮሊዳስ እንደሚሉት በሀገራቸው እንዲህ ያለ የሙቀት ማዕበል ከተከሰተ ቆይቷል፤ በጎርጎሪዮሳዊው 1987 ዓ,ም። ባለፉት ቀናት ከ40 ዲግሪ በላይ ከፍ ያለው የሙቀት ማዕበልም ለቱሪስቶች ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት ሆኗል።
ድንገተኛው ሙቀትና ጤና
እዚህ ጀርመን የዘንድሮው የበጋ ወቅት ከገባበት ጊዜ አንስቶ ለቀናት ሙቀቱ እስከ 30 ዲግሪ ደርሶ እጅግ ከሞቀ በኋላ መለስ ብሎ ኃይለኛ ዝናብ እያስከተለ እያስተዋልን ነው። ባሳለነፍው ሳምንት ግን የሙቀት መጠኑ ከ30 ዲግሪም ከፍ ያለባቸው በርካታ ቦታዎች ነበሩ። በደቡባዊ ጀርመን ግዛት ባየር ሙቀቱ ከፍ ካለባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ዴሊንገን ነዋሪ የሆነችው ትውልደ ኢትዮጵያዊት ወ/ሮ ትዕግሥት፤ እንደምትለው ከአምናው የዘንድሮው ሙቀት አይሏል። ዘንድሮ ለቀናት ከፍተኛ ሙቀት ቢኖርም ዳግም የሙቀት መጠኑ ይቀንሳል።
እርግጥም ከሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ይልቅ ከትናንት ጀምሮ ኃይለኛው ሙቀት በመጠኑ ቀንሷል። በአንዳንድ አካባቢዎችም ዝናብ አለ። የውስጥ ደዌ የህክምና ባለሙያ የሆነችው ዶክተር ሰብለወንጌል ይመኔ የሙቀቱ መጠን ቀስ በቀስ የሚለወጥ እንዳልሆነ ታዝባለች። ይህን መሰሉ የሙቀት መጠን ለውጥ ደግሞ የዕድሜ ገደብ ሳይኖረው ጤና ላይ ጫና ይኖረዋል ነው የምትለው።
ባለፉት ቀናት የነበረው ሙቀት ለረዥም ወራት በኃይለኛ ብርድ ውስጥ የከረመውን ሰውነት ከማፍታታት ይልቅ የሚያዝልና ድቅቅ የሚያደርግ ዓይነት መሆኑ ነው የታየው። እንዲህ ያለ ኃይለኛ ፀሐይና ሙቀት ሲኖር ሰዎች ጤናቸውን ለመጠበቅ ውኃ መጠጣትን፣ ጥላ ቦታ መሆንን፤ ፀሐይ ላይ ብዙ አለመቆምን የመሳሰሉ ጥንቃቄዎችን ማድረግ የእንደሚገባ ጠቁማለች።
ሁሉን ያዳረሰው ኃይለኛ ሙቀት
ሙቀቱ በአውሮጳ ብቻ አልተወሰነም። በጃፓን ሀገሪቱን ያዳረሰው ኃይለኛውሙቀቱየጤና መዛባት ሊያስከትል እንደሚችል ትናንት ለሕዝቡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል። የሙቀቱ መጠን ከፍተኛነት ሰዎች አቅላቸውን ስተው እንዲወድቁ ሊያደርግ እንደሚችል ነው ማሳሰቢያ የተነገረው። ቻይና ውስጥ በተለይ የሻንጋይ ነዋሪዎች ኃይለኛውን ሙቀት ለመከላከል አብዛኞቹ ውኃ ወዳለበት የመናፈሻ ስፍራ እንዲሰባሰቡ አስገድዷል።
በመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራትም የተባባሰው ሙቀት ኅብረተሰቡ ጤና ላይ ካሳደረው ጫና በተጨማሪ በአትክልት ገበያው የዋጋ ጭማሪም አስከትሏል። በአብዛኛው የአረብ ሃገራት የምግብ ዝግጅት ውስጥ የማይጠፋው ቲማቲም ዋጋው በመወደዱ ምክንያት ሸማቾች ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው። እንደ ቲማቲም ያሉ አትክልቶች በሙቀት ምክንያት እንደልብ ወደ ገበያው ባለመቅረባቸው ዋጋቸው ለመናሩ ምክንያት መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ። አፍሪቃዊቱ ኮትዴቩዋርም ኃይለኛው ሙቀት በገበያው ላይ ግሽበትን ካስከተለባቸው ሃገራት አንዷ ናት። እንደቲማቲም፤ ቃሪያ፤ ደበርጃንና የመሳሰሉትን አትክልቶች ለመሸመት በዋና ከተማ አቢጃን ወደ ገበያ የወጡ ዜጎች የያዝነው በጀት ልንሸምተው ካሰብነው ጋር አልተገናኘም እያሉ ነው።
ከዚህም ሌላ ባለፈው ሰኔ ወር ሳውድ አረቢያ ውስጥ ኃይለኛው የሙቀት ማዕበል ለሃይማኖታዊ ሥርዓት ወደ መካ ከተጓዙ ተሳላሚዎች ለ1,300 ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑ አይዘነጋም። ምንም እንኳን ለበራሃማዋ ሳውዲ አደገኛ ሞቃት አየር እንግዳ ባይሆንም ያባባሰው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መሆኑን የዘርፉ ተመራማሪዎች ያመለክታሉ። የአየር ንብረት ለውጡ የሙቀት ማዕበልን ከማስከተሉም ሌላ ክስተቱ እንዲደጋገምና ለረዥም ጊዜም እንዲቆይ እያደረገው እንደሆነም እየገለጹ ነው። ከሙቀቱ ጎን ለጎን ቻይናን ጨምሮ በአንዳንድ ሃገራት ኃይለኛ ሞገድ የሚገፋው ዝናብ እና ጎርፍም የዘንድሮው የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የአየር ሁኔታ ገጽታ ነው። ሰደድ እሳቱም በአንድ ወገን አለ።
የተለያዩ ሃገራት በሙቀት ማዕበል በተጨነቁበት በዚህ ወቅት በዉኃ ላይ የተሠራችው ሀገር የጀርመን ጎረቤት ኔዘርላንድ ባለፈው ሳምንት ነው የበጋው ሙቀት የመጣላት። አምስተርዳም ላይ ከ23 ዲግሪ ያልበለጠው የሙቀት መጠን ወትሮም ቱሪስት የማታጣውን ከተማ የጎብኚዎች ማግኔት አድርጓታል።
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ